Print this page
Saturday, 16 January 2021 11:40

ከታላቅ ወንድም እስከ ‘ፍሪ ላንች’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ...‘የእሱና የእሷ’ ነገር ከትላንት እስከ ዛሬ እንዴት አሪፍ ‘ጎን ዊዝ ዘ ዊንድ’ ምናምን አይነት ነገር ይወጣው መሰላችሁ! ያኔ...መጀመሪያ ምን አለ መሰላችሁ... ‘እሺ’ ማሰኘት፡፡ እንደ ዛሬው ‘የፋስት ፉድ’ ሽያጭ ስትራቴጂ ወደ ‘ፋስት ፍቅር’ የሚባል ‘ሾርትከት’ ነገር አልነበረም፡፡ ሁሏም ነገር የምትገኘው በላብና በጥረት ነው፡፡ ልክ ነዋ...እስከሚሳካ ድረስ ስንትና ስንት መሳቀቅ አለ፡፡ እኛ እንኳን ትንሽ ጫፍ አግኝተው ሳያገኙ እንኳን መግቢያ፣ መቅድም፣ ቅድመ ታሪክ፣ ድህረ ታሪክ፣ ምናምን ጨማምረው የሚያወሩት እትዬ እንትና ዓይን ከተገባ...ፕሮጀክት ተበላሸ ማለት ነው፡፡ (አዎ፣ በዛ ጊዜ ነገርዬው ሁሉንም የፕሮጀክት መመዘኛዎች የሚያሟላ ነገር ነበር፡፡ ፒያሳ ተጀምሮ አራት ኪሎ ላይ “ሁሉም ነገር ዓለምን ሊያስደንቅ በሚችል ፍጥነት ተሳክቷል፣” ብሎ ነገር የለም፡፡ የምር እኮ...ዘንድሮ ሁሉም ነገር እጅ በእጅ ሆነና፣ እሷዬዋን ለማግኘት ከጎጃም በረንዳ ቅምብቢት በእግሩ ይኳትን የነበረ... “ምን ጊዜ ተጩሆ፣ ምን ጊዜ ደረሱ” የሚባልለት ሁሉ ከጨዋታ ውጪ ሆነ! “ኸረ ተሳታፊነቱ ቢቀርብን እንኳን ድምጽ የመስጠት መብት የሌለው የተመልካችነት ወንበር ስጡን!” የሚል አይጠፋም ለማለት ያህል ነው፡፡ (በአንዳንድ ሀገራት በእነሆ በረከት ጉዳይ ...አለ አይደለ...ዝም ብሎ ‘የሚፈጠጥበት’ እንደ ‘ዊንዶው ሾፒንግ’ አይነት ነገር አለ ሲባል ስለምንሰማ ነው፡፡)
እናማ... እኛ የሰፈር እትየ እንትና እንዳያዩ በምናምን ቁጥር አንበሳ አውቶብስ አገር አቆራርጦ መሄድ ነው፡፡ በነገራችን ላይ... እንደው የፈለገ ነገር ቢረሳ፣ የፈለገ ነገር ቢዘነጋ፣ እንደፈለገ ‘ዘመናዊ’ ለመሆን ቢሞከር የ‘ነጠላ’ን ውለታ መርሳት ግን ‘ፌይር’ ነው!
“ማነሽ አንቺ! አንቺን እኮ ነው የምጠራው!”
“እመት እማዬ...”
“ስጠራሽ ጆሮሽ ላይ ተቀምጠሽበታል እንዴ!”
“ሥራ ላይ ሆኜ እኮ ነው...”
"ሰረሰርሽ ይውለቅ! ባለሰማያዊ ጥለት ነጠላዬን ማን ወሰደው?”
“ማሚቱ ነች፡፡” በአምስት ዓመትም፣ በሀያ አምስት ዓመትም ማሚቱ ማለት ይቻል ነበር፡፡
“ከመቼ ወዲህ ነው ደግሞ እሷ ነጠላ መልበስ የጀመረችው?”
“የጓደኛዋ አክስት አርፈው ለቅሶ ልድረስ ብላ ነው፡፡”
 “ጎሽ!” ማዘር ደስ አላቸው፡፡ “አሁን ገና ለቁም ነገር በቃች፡፡”
በትክከል ተመልሷል! አሀ...ነጠላ እንደሁ አያሳብቅ...እሱዬው ቅበጥ ብሎት ‘ሊፕስቲክ’ ካልተለቀለቀ በስተቀር! ቂ...ቂ...ቂ... እኔ የምለው... እንግዲህ ጨዋታም አይደል... ግን የዘንድሮ ‘ሊፕስቲክ’ እንትናዬዎቹ ላይ ቦግ ብሎ፣ ወደ እንትናዎቹ ሸሚዝ ሲሸጋገር ‘ኢንቪዝብል ይሆናል እንዴ! ግራ ስለገባን እኮ ነው፡፡ የ‘ኪሶሎጂ አርት’ እንዲህ በተስፋፋበት እንዴት የሚጣበቅ የሊፕስቲክ ዓይነት ጠፋ ብለን ነው፡፡
እናላችሁ... አሁን በ‘ፕሮፋይል ፒክቸር’ ብቻ አነጣጥሮ የሚጣልበት ዘመን አልነበረም፡፡ ስሙኝማ... እንግዲህ ጨዋታም አይደል፣ የ‘ፕሮፋይል ፒክቸር’ ነገርማ ራሱን የቻለ ሲዝን ፋይቭ ድረስ የሚሄድ ተከታታይ ድራማ ሊሠራለት ይገባል፡፡ አሀ... ከትናንት ወዲያ የእኛ ቢጤ ከወጪ ቀሪ፣ ማለትም እንደው ሁሉም ነገር ድንገት የጠፋ እንደሆነ ተብሎ ለ‘ምናልባቱ’ ብቻ የተቀመጠ የሚመስለው ሁሉ ‘አፕዴት’ የተደረገ ፕሮፋይል ፒክቸሩ ላይ... አለ አይደል...“አንጀሊና ጆሊ ብራድ ፒትን የፈነገለችው በዚህ ሰውዬ የተነሳ ነው እንዴ!” ሊያሰኝ ምንም አይቀረው፡፡ ከ‘ፕሮፋይል ፒክቸር’ በፊት አሪፍ የሚባለው ሩስያ ተልኮ በእጅ ይሁን በምናምን ነካ፣ ነካ ተደርጎ ‘ባለ ቀለም ስእል’ ሆኖ የሚመጣው ነበር፡፡ (እናላችሁ...ለጥቆማ ያህል፣ “እኔ እኮ ሲያዩኝ ትልቅ ሰው እየመሰልኩ ነው እንጂ ገና አንዲት ፍሬ ልጅ ነኝ፣” የምትለዋን ሁሉ በማስረጃ ለመሞገት ቢፌው ላይ ያለው ፎቶ፣ የእጅ ሥራ መሆን አለመሆኑን ማየት ይበቃል፡፡
ስሙኝማ...ከዚህ በፊት እንዳወራነው እዚህ ሀገር ሊዘመርለት ሲገባ ‘ኢግኖር’ የተደረገ ማን አለ መሰላችሁ...ታላቅ ወንድም፡፡
እናማ...አለ አይደል... በታላቅ ወንድም ‘ታሪካዊ ሚና’ ላይ የሚሰጠው ድምጽ እኩል ለእኩል ሳይሆን አይቀርም። ልጄ... “ተው ይቅርብህ፣ ታላቅ ወንድሟ የሰማ እንደሆነ አንስቶ እንዳያፈርጥህ (ያኔ ‘አፐርከት’ ‘ሌፍት ሁክ’ ምናምን ብሎ ነገር ሳይሆን ዳኛው የ‘ኖክአውት’ ውሳኔ የሚሰጠው “ማን አንስቶ አፈረጠ!” በሚለው ነበር። የእንትናዬዎቹ ‘የምንጊዜም አንስቶ አፍራጮች’ ታላቅ ወንድሞች እንደነበሩ ታሪክ ይመዝግበው ለማለት ያህል ነው። (ቂ...ቂ..ቂ..)  “ምን እንዳያመጣ ነው!” እያለ ሲያስቸግር መንጋጭላው ሱናሚ ያናጋው ይመስል ቦታውን የለቀቀ ሁሉ “ታላቅ ወንድሞች ለዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ይቅረቡ!” ባይ ነው። ራሳቸው ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ሊቀርቡ ይገባቸው የነበሩና ስንት መንጋጭላዎች የተፈጥሮ ስፍራቸውን ከመልቀቅ ጀርባ ያሉ እንትናዬዎች ደግሞ ለታላቅ ወንድሞች “የሆነ የተባበሩት መንግሥታት ሽልማት ይገባቸዋል፣” የሚሉ ይመስለናል፡፡  
ስሙኝማ... ሌላ ደግሞ እዚህ ሀገር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገው ያልተዘመረላቸው እነማን መሰሏችሁ...በእሱና በእሷ መሀል የፍቅር ደብዳቤዎች ሲያመላልሱ የኖሩ የየሰፈሩ ህጻናት፡፡ (ታሪክ ለባለታሪኮች ይመለሳ! የምን ማዳላት ነው! (ቂ...ቂ...ቂ...)
ድሮ... ድሮ ነው፡፡ (ሂሳቡን አስሉትና... ሁሉም ሰው ልክ ነው፡፡) እሱዬው እንትን ሀይ ስኩል ተማሪ ነው፡፡ (ስሙ አስፈላጊ ስላልሆነ ነው፡፡) እናላችሁ... አንድ ቀን ከትምህርት ቤት ሲመለስ እንደ ጉድ ተናዶ ነበር፡፡ እና የሰፈር ልጆች ደግሞ የአንዱ ንዴትም፣ ሳቅም የጋራ ጉዳይ ስለሆነ  ሰብሰብ ብለው ይከቡታል፡፡
“ምን ሆነህ ነው?” ይባላል፡፡ ተቧቅሶ መጣ እንዳይባል ፊቱ ላይ የተጫረ ነገር፣ ወይም የጎደለ የጃኬት ቁልፍ የለም፡፡
እሱዬው መልስ ሳይሰጥ እንዲሁ ብቻ ይንተከተካል፡፡  
“ምን ሆነህ ነው?”
ምን ሆኖ መሰላችሁ...ለካስ አንዱ ጎረምሳ ‘ገርልዬውን’ ነጥቆት ነው፤፡ (ያን ጊዜ ‘ገርል’ ሲባል ‘ከእነሙሉ ትርጉሙ’ ነበር፡፡ ታሪክ መመዝገብ አለበታ!) እናላችሁ... ነጠቃው ደግሞ ዝም ብሎ...አለ አይደል... ‘አካሄድ አይቶ ጭብጦ እንደ መቀማት’ አይነት አልነበረም፡፡ ...ነጣቂው የእንትን ሰፈር ልጅ ነው፡፡ ይኸው ‘እንትን ሰፈር’ ደግሞ ከዚህኛው ልጅ ሰፈር ጋር “ታሪካዊ ለመባል ምን ይጎድለዋል!” የሚባልለት አይነት ባላንጣነት ነበር፡፡
እናማ ነገርዬው “የተረት ሰፈሯ ብትሄድ የገዳም ሰፈሯ ትመጣለች” ተብሎ የሚታለፍ አልነበረም፡፡ (እነኚህ ሰፈሮች የተጠቀሱት የ‘ኖስታልጂያ ምናምን ነገር ሳይሆን አፍ ላይ ስለመጡ ብቻ እንደሆነ ይመዝገብልንማ!) እናላችሁ... የልጁ ሳይሆን የሰፈሩ ‘ክብር’ ነበር የተዋረደው! ምን ቢሆን ጥሩ ነው... ንዴቱ ሁሉም የሰፈር ልጆች ላይ ተዛመተ። ክብር ተነካ! እናላችሁ መፈክሩ...“የእንትን ሰፈር ልጅ የሰፈራችንን ልጅ ነጥቆ፣ እጃችንን አጣጥፈን ልንቀመጥ! ሞተናላ!” አይነት ነበር! በማግስቱ የዚህ ሰፈር ልጆች ለአጸፋዊ ምላሽ ወደዛ ትምህርት ቤት ዘመቱላችኋ! እናማ... ምድር ቀውጢ ሆነች።  
እንዲህ ነበር ያኔ፡፡ የዛን ዘመን የከተማ ጀግንነት እንትናዬዋን የነጠቁ፣ ያስነጠቁና ስትነጠቅ ዝም ብለው ያዩ፣ እንዲሁም በነጠቃው አሳበው የ‘ሰፈርን ክብር’ ያዋረዱ ላይ ‘ተገቢውን’ ምላሽ መስጠት ነው። (‘ተመጣጣኝ’ ቅብጥርስዮ ብሎ ነገር የለም!) ስሙኝማ... ኮሚክ አይደል...ድሮ ጊዜ እንትናዬዎች ሰውና ሰውን ሳይሆን ሰፈርና ሰፈርን ያደባድቡ ነበር... (እንደውም ሼክስፒር የሮሚዮና የጁሊየት ቤተሰቦችን ያፋለመው ከድሮ ጊዜ የሰፈር ልጆች ሀሳቡን አግኝቶ መሆን አለበት! በፕሪሚየር ሊግ አባብለው የባለቤትነት መብት ጥያቄ እንዳናነሳ አደረጉን እንጂ!) እናላችሁ... ያኔ ስንትና ስንት ‘ፍስፍስ’ (እንዲህ የሚባል ቃል አለ አይደል!) ነበር ለማለት ነው፡፡ ነገሩ ሁሉ እንዲህ ‘ፍሪ ላንች’ ዘመን ሊደረስ! ቂ...ቂ...ቂ...  ዘንድሮ ደግሞ ራሳቸው በኩንግ ፉ ጸጥ ሊያደርጉ ይችላሉ የሚል ሀሜታ አለ።
“ሲሱ...”
“ምን ሆንክ! እንተዋወቃለን?”
“አይ እንደው ሳይሽ ደስ አልሽኛና...”
“ደስ አልኩህ! ሂድና የለመድከበት ተለፋደድ!”
“እንዲህ ነች ቀዮ! ምን ታካብጂያለሽ... አናውቅሽምና ነው...” ክንድ ለመያዝ ይሞከራል፡፡ ምን መብረቅ እንደወረደበት ሳያውቅ ምንጣፍ ይሆናል፡፡ (ከወራት በፊት ፒያሳ መሀል ሞባይሏን ነጥቆ ሊያመልጥ የሞከረውን ጎረምሳ፣ አንድ እህታችን፣ ምን መብረቅ እንደወረደበት ሳያውቅ አንጥፋው ነበር፡፡) (የዚችን አይነት እህቶች ያብዛልንማ!)
እናማ... ከታላቅ ወንድም እስከ ‘ፍሪ ላንች’ የተጓዘው ባቡር መንገዱን ቀጥሏል ለማለት ያህል ነው፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ! 

Read 1908 times