Sunday, 17 January 2021 00:00

የአዲስ አድማስ የ20 ዓመት ጽኑ ወዳጅ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

"በየሳምንቱ ሳላቋርጥ በማንበብ ላይ ነኝ"


           አቶ መስፍን ወልዴ መሃል ኮልፌ ላይ የሚገኝ “አጋዝ ካፌና ሬስቶራንት” ባለቤት ነው። መተዳደሪያው ንግድ ነው፡፡ የዛሬ እንግዳችን ያደረግነው በንግድ ሥራው አይደለም፡፡ በአንባቢነቱና በአዲስ አድማስ የረጅም ዘመን ወዳጅነቱ ነው፡፡ ከጋዜጣችን ጋር ዝምድና አለው፤ ያቆራኘው ኪዳን፣ የሳበው እውነት አለ።  ከ20 ዓመት በላይ የአዲስ አድማስ ጋዜጣ አንባቢ ነው። ፍቅሩም እስከ ዛሬ ዘልቋል፣ በጊዜ ርቀት አልተነነም፣ … ዘወትር ቅዳሜን በናፍቆትና በጉጉት እንደሚጠብቅ ይናገራል። ከራሱም አልፎ ለካፌ ደንበኞቹ ከቡና ጋር አዲስ አድማስን እንዲያነቡ ያቀርብላቸው ነበር።  ለመሆኑ ከጋዜጣው ጋር መቼ ተዋወቀ? የፍቅሩስ ምስጢር ምን ይሆን? …እንዲህ አውግቶናል፡-


                     እንደምታየው ስራዬ ንግድ ነው። አዲስ አድማስ ጋዜጣን ማንበብ የጀመርኩት ገና ሲጀመር፣ በምስረታው ነው፤ ሃያ ዓመት አልፎኛል። እስካሁን በየሳምንቱ ሳላቋርጥ በማንበብ ላይ ነኝ፡፡ አሁን ሁኔታው ከልክሎኝ እንጂ ሌሎች ሰዎችም  (ደንበኞቼ) እንዲያነብቡ ገዝቼ በየጠረጴዛው ላይ አስቀምጥ ነበር።
ጋዜጣ ወይም መጽሄት ሳታቋርጥ የምትከታተለው፣ አንዳች የወደድከው ነገር ሲኖር ነው። አዲስ አድማስን በምን ወደድካት?
አዲስ አድማስን የወደድኩበት የመጀመሪያውና ዋናው ምክንያት፣ ሚዛናዊ መጣጥፎች ይዞ መውጣቱ ነው። በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሚጽፉትን ዐምደኞች ሀሳብ እወድደዋለሁ። በጎና ጠቃሚ ሀሳብ የሚያስተላልፉ ናቸው። በዋናነት ርዕሰ አንቀፁ በጣም የምወደውና የሚመቸኝ ነው፡፡ ለሀገራችን ኢትዮጵያ የሚበጅ፣ ሚዛናዊ የሆነ መልዕክትና ቁምነገር የሚያስተላልፍ ፅሁፍ  ነው። … በሀገራዊ ስነ-ቃልና ተረቶች ጀምሮ፣ መደምደሚያው ላይ የሚቋጭበት መንገድ፣ ከተጨባጩ ህይወት ጋር የሚዛመድና ገላጭ ነው። ያ በጣም ይገርመኛል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ውስብስብ ነው ሲሉ እሰማለሁ፤ … አጣጥመህ ካነበብከው ግን በጣም አስተማማኝ፣ የሀገሪቱን ተጨባጭና ወቅታዊ ሁኔታ የሚያንፀባርቅ ነው። ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ጉዳዮችን  አዋዝቶ በማራኪ ቋንቋ ያቀርባል።
ከጋዜጣው አምዶች የትኞቹን በቅድምያና በትኩረት ታነባለህ--?
በሚገርም ሁኔታ ሁሉንም አነብባለሁ፤… ፖለቲካ ይመስጠኛል፤ ምክንያቱም የሁሉም ነገር መነሻ እርሱ ነውና፡፡ ፖለቲካው ካልተስተካከለ ብትነግድም ዘለቄታው አስተማማኝ አይሆንም፤ ፖሊሲዎችና ህጎች ለችግር ሊዳርጉህ ይችላሉ። የአዲስ አድማስ ፖለቲካ ደግሞ ሚዛናዊ ነው፤ ጽንፈኛ አይደለም፤ ከሚነቅፈውና ከሚደግፈው ጎን አይቆምም፤ ሀሳብን  ብቻ ሞጋች ነው። በመቀጠል ኢኮኖሚውን አነብባለሁ። ለምሳሌ የንግዱን ማህበረሰብ ተሞክሮዎች አነብባለሁ። ቀደም ሲል ብርሃኑ ሰሙ የሚያቀርባቸውን ንግድ ተኮር ጽሁፎች ስከታተል የስራ መንገዴንም ያሳየኛል። እንደ ዘምዘም ያሉትን የመርካቶ የንግድ መሰረቶች ታሪክ ሳነብ የምማረው ነገር አለ። እርሳቸው በሴትነት በዚያ ዘመን የሰሩትን ጠንካራ ስራ ሳይ እደነቃለሁ፤ የምወስደውም ተሞክሮ ይኖራል። ሌላው የጥበብ ዓምድ ነው፡፡ በጥበብ አምድ መፃሕፍት ላይ የሚሰጡትን አስተያየቶች፣ ሂሳዊ መጣጥፎች ማንበብ ደስ ይለኛል። እነ ገዛኸኝ ጸ.  የመሳሰሉት ፀሐፍት የሚያቀርቡትን እከታተላለሁ፡፡
ከቃለ ምልልሶች በአእምሮህ ተቀርፀው የቀሩ ይኖራሉ ብዬ እገምታለሁ---
በንግዱ ዘርፍ፣ የአስፋወሰን ሆቴል ባለቤት የነበሩት ወ/ሮ ዘምዘም ጥንካሬ ይደንቀኛል፡፡ መርካቶ ውስጥ፣ በዚያ ዘመን ይህን የሚያህል ሕንፃ መገንባታቸው የሚያስደስትና ፈለጋቸውን ለመከተል የሚያስመኝ ነው። በፖለቲካው በኩል፣ በሃያ ዓመታት በርካታ የፖለቲካ ሰዎች ቃለ ምልልስ አድርገዋል። በገዢውም  ወገን ሆነ በተፎካካሪዎች ቃለ ምልልስ ያልተደረገለት ስመጥር ፖለቲከኛ የለም። ዶክተር ብርሃኑ ነጋ፣ አቶ ልደቱ አያሌውና ፕ/ር መስፍን ወልደማርያምን የመሳሰሉ ቀርበው ሃሳባቸውንና መንገዶቻቸውን ገልፀውበታል። ሁሉንም አንብቤያቸዋለሁ ማለት እችላለሁ። የሚቀርበው ቃለ ምልልስ ሚዛናዊ ነው፡፡ አጠቃላይ ግቡ ኢትዮጵያ ተኮር ነው። ጋዜጣው የሚሰራው ኢትዮጵያዊነት አሸናፊ እንዲሆን ነው።
ተከታታይ መጣጥፎችስ ታነባለህ--? ለምሳሌ "የኛ ሰው በአሜሪካ"---?  
ነቢይ መኮንን ትልቅ ገጣሚ ነው፤ አዲስ አድማስም ላይ ብዙ አንባቢ ያለውና ጋዜጣዋን ተወዳጅ ካደረጉት ፀሐፍት መካከል ተጠቃሽ ነው፡፡ ጋሽ ነቢይን አመሰግነዋለሁ። “የኛ ሰው በአሜሪካ” በጣም የሚወደድ፣ ጥሩ ፍሰት ያለው፣ ማራኪና የስደት ሀገር የሕይወት ገጽታዎችን የሚያሳይ ነበር። መነሻውን፣ መድረሻውን የሚያውቅ፣ አሜሪካንና ኢትዮጵያን የሚያነጻጽርና የሚያስተሳስር አስደሳች ጽሑፍ ነው። የአሜሪካን ሀገር ሰዎች ሕይወትና አኗኗርን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ትረካ በመሆኑ ሳምንት እስኪደርስ የሚናፍቅ ነበር። እኔ ብቻ ሳልሆን ብዙ ሰዎች ጋዜጣውን ሲያገኙ ዘለው ጉብ የሚሉት እሱ ላይ እንደነበር አስታውሳለሁ። እውነት ለመናገር በጣም የተነበበ ጽሁፍ ነው። እዚያ ያሉት ኢትዮጵያውያን አኗኗር፣ ሀገር ቤት ያለው ምኞትና በእውን ያለው ሕይወት፣ መስተጋብር -- ሁሉ የሚገርም ነበር። እዚህ የናቁትን ስራ እዚያ እንዴት እንደሚሰሩት…  እዚህ ያሰቡት ዶላር እዚያ በቀላሉ እንደማይገኝ፣ ዝቅ ካለ ቦታ ተነስተው፣ ትልቅ ቦታ የደረሱ ጠንካሮችንም ያየንበት ነው።
ከአዲስ አድማስ የሃያ ዓመት ወዳጅነትህ ምን ተጠቀምኩ ትላለህ?  
እውነት ለመናገር ከሁሉ በላይ የንባብ ፍላጎቴን አጎልብቶልኛል፡፡ እንደምታውቀው የንግድ አገልግሎት፣ በተለይ ካፌ ጊዜ ይፈልጋል። ሠራተኞችን ማስተዳደሩም ቀላል አይደለም፤ ከደንበኞች ምቾት ጋር የሚያያዝ ስለሆነ ስራው ከባድ ነው። ሆኖም ግን አዲስ አድማስ ይዛ የምትወጣው ነገር ሳቢ ስለሆነ እኔም በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚው፣ በጥበቡ ዘርፍ --- ብዙ ዕውቀት እንድጨብጥ አድርጎኛል። ከመጻሕፍት በላይ ጠቅሞኛል። ምክንያቱም አንድ መፅሐፍ የሚነግርህ ስለ አንድ ነገር ይሆናል። አዲስ አድማስ ላይ ግን ባንድ ቀን እትም ስለ ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ፣ ስለ ጥበብ መጠነኛ ግንዛቤ የምትጨብጥበትን ሀሳብ ታገኛለህ። በአጠቃላይ በጋዜጣው የማይዳሰስ ነገር የለም። በዚያ ላይ የብዙ ፀሐፍት የሃሳብና የዕውቀት ክምችት ይገኛል። የአስርና ከዚያ በላይ ሰዎችን እውቀትና ምልከታ ትካፈላለህ፤ ይህ ቀላል አይደለም። በሁሉም አቅጣጫ በዕውቀት ትታጠቃለህ። ስለዚህ ብዙ ዕውቀት አግኝቻለሁ፤ በሌላ በኩል መፃሕፍትም እንዳነብ አግዞኛል። በአጠቃላይ፡- በሕትመቱ ዘርፍ ወገንተኝነት የሌለበት፣ ዛሬ አንብበህ ነገ የማትጥላቸው፣ የሃሳብ የበላይነት የሚንፀባረቅባቸውን መጣጥፎች አግኝቻለሁ።…  ለሀሳብና ሀሳብ ብቻ ቦታ ያለው ጋዜጣ ነው። አንዳንድ ሰዎች “ለዘብተኛ ነው” በሚሉት አልስማማም። ትክክለኛ ዘገባ ስታቀርብ ከሚያስጮሁት ግን ቶሎ ከሚጠፉት ወገን አትሆንም።... ማስጮህ ያጠፋል!... ምክንያቱም ቋሚ የሃሳብ ልዕልና አይኖርህምና!
በዚህ አጋጣሚ የጋዜጣውን መስራች አቶ አሰፋ ጎሳዬን ላመሰግን እፈልጋለሁ። እሱ በጥሩ መሰረት ላይ ስላቆመው ይኸው ዛሬም ድረስ ቀጥሏል። እርሱ ባይኖርም ስራው ዛሬም ለሀገር እየጠቀመ ነው።
በኛ አገር የንባብ ባህል አልዳበረም። አንተ በተለይ ነጋዴ ሆነህ እንዴት ወደ ንባብ ገባህ ?
እኔ ንባብ የለመድኩት እዚሁ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ነው። በአንድ ወቅት  "ሙሉ ሰው እንድትሆን አንብብ!” የሚል አባባል ጋዜጣው ላይ ይወጣ ነበር። ያ - ነገር በጣም ሳበኝ። በርግጥም አንድ ሰው ሙሉ ሊሆን የሚችለው ሲያነብ ብቻ ነው። እኔ እንኳ ብዙ የተረፈ ጊዜ ኖሮኝ አነብባለሁ ባልልም፣ መታገሌ በራሱ ጥሩ ነገር ነው። መፃሕፍትን አነብባለሁ። እንደምታየው ባሁን ጊዜ ንባብ የወደቀ ይመስላል። ቢሆንም ሰው ያለ ንባብ ሙሉ አይደለም፤ ምክንያቱም፤ ሰው ኢኮኖሚክስ ቢማር፣ የሚያውቀው ስለዚያ ዘርፍ ብቻ ነው። ያው በንድፈ ሀሳብ ደረጃ! ምህንድስና ቢማርም እንደዚያው ነው። በሌሎችም! ሲያነብ ግን ስለ ፖለቲካው ያውቃል፤ ስለ ኢኮኖሚው፣ ስለ ሌላው ዘርፍ ያውቃል። ስለ ምህንድስና ለማወቅ፣ የዘርፉን መፃሕፍት ማንበብ አለበት። ስለ ንግድም እንደዚሁ። አንድ ሰው ፕሮፌሰር እንኳ ቢሆን ስለተማረበት፣ ስፔሻላይዝ ስላደረገው ነገር እንጂ ሌላ ነገር አያውቅም። ከማንበብ ግን የማታውቀው ነገር የለም። በተለይ ለጋዜጠኞች፣ ለሀገር መሪዎች ሰፊ ንባብ ያስፈልጋል። ምክንያቱም ሞያቸውም ያስገድዳቸዋል። አገልግሎታቸው ሙሉ እንዲሆን ስለ ኢኮኖሚ፣ ስለ ጥበብ፣ ስለ ንግድ ወዘተ ሊያውቁ ይገባል። ጋዜጠኛም ሚዛናዊ ሊሆን የሚችለው ሲያነብብና ሲያነብብ ብቻ ነው። ካልሆነ ጥራዝ ነጠቅ ይሆናል። የተሟላ መረጃ ማቅረብም አይችልም።
ወደ እኔም ስንመጣ ማንበብ ያስደስተኛል። አዲስ አድማስ ሳምንት ቅዳሜ እስኪደርስ ይጨንቀኛል። ጠዋት ጋዜጣውን ገላልጬ ካላየሁ እንደ ቡና ሱስ ነው። ቁርስ ከመብላቴ በፊት እርሱን አያለሁ። ከሃያ ዓመት በላይ ያነበብኩት ሱስ ሆኖብኝ ነው፡፡ ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል! በሚለውም አምናለሁ። ሰው ለሌላ ነገር ገንዘብ የሚያወጣውን ያህል ጋዜጣና መፃሕፍት ገዝቶ በማንበብም ራሱን ማሻሻል አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ እኔ ከራሴ አልፌ የተለያዩ ጋዜጦችና መፅሔቶችን እየገዛሁ ለካፌ ደንበኞቼ አስቀምጥ ነበር። ሰውም ማኪያቶና ቁርስ እስኪመጣለት ድረስ ማንበቡንም ተለማምዶ ነበር። አንድ ወቅት ላይ በተፈጠረው የፖለቲካ ግለት የማይመች ሁኔታ ገጥሞኝ ለራሴ ብቻ ማንበብ ቀጠልኩ።
አዲስ አድማስ ጋዜጣ እስከ ዛሬ ብዙ ሃሳቦች አካፍሎናል።… በአካል ባይኖርም ይህን ጋዜጣ የመሰረተውን አሰፋ ጎሳዬን፣ ነቢይ መኮንንን፣ ዮሐንስ ሰን፣ ገዛኸኝ ፀን፣ ኢዮብ ካሣንና ሌሎቻችሁንም ማመስገን ይገባኛል።… ከሃያ ዓመት በላይ በህትመት መዝለቅ ማለት ትልቅ ስኬት ነው። ጋዜጠኞችንና የጥበብ ሰዎችን ሁሉ አመሰግናለሁ፤ ዕውቀት በገንዘብ አይገዛም፤ በፍላጎት የሚገኝ ነው። ስለዚህ ጋዜጣው ባለውለታችን ነው፡፡.. የዚህን ያህል ተጉዞ ለዚህ መድረሱ የጥንካሬው ማሳያ ነው…ብዬ አምናለሁ።… የመረጥኩትም ለዚያ ነው፤ ተገድጄ አይደለም፡፡


Read 1837 times