Saturday, 16 January 2021 12:02

የሩሲያ ፎቶግራፎች

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(7 votes)

  በልጅነቴ “Russian Doll” በተባለው አሻንጉሊት ተጫውቻለሁኝ፡፡ ግን በጣም ህፃን ሳልሆን አልቀርም፣ ምክኒያቱም ትዝ የሚለኝ ቅርፁና ሲወድቅ ደረቅ እንጨታማ ኳኳታ እንደነበረ ብቻ ነው፡፡ ቁም ነገሩ ግን አይገባኝም ነበር፡፡ በቦውሊንግ ከባድ ኳስ ለመምታት ከሚደረደሩ ድፍን ብርሌ መሳይ ቅርፆች ጋር አሻንጉሊቱ ይመሳሰላል፡፡
የአሻንጉሊቱ ቅርፅ ፊት አለው፤ ፊቱ የሴት ነው፡፡ የፊቱ ምስል የብርሌው ቅርፅ ጭንቅላት አካባቢ ሲሆን፣ ከጭንቅላቱ ወረድ ሲል አንገቱ አካባቢ ቀጠን ይልና መልሶ ይወፍራል፡፡ የብርሌ አንገት ነው ግን የሰው ፊት ስለተሳለበት ሴትዮ ትሆናለች። ይኼ ሁሉ ግን ልጅ ሆነን አይገባንም፡፡ አሻንጉሊቱ ከሩሲያ መምጣቱም ሆነ የተለየ ነገር እንዳለው አናውቅም፡፡ መሬት ላይ እየወረወርን እናንኳኳዋለን፡፡
በመሰረቱ አሻንጉሊቷ ከባህር ማዶ የተላከላት ለታናሽ እህቴ ነበር፡፡ በወቅቱ ገና አራስ ስለነበረች እኔና ወንድሜ ተጫወትንበት፡፡ ተወራወርንበት ብል ይቀላል፡፡ አሻንጉሊቷን ልዩ የሚያደርጋት በሆድ እቃዋ ውስጥ ብዙ አምሳያዎቿን መያዝ በመቻሏ ምክኒያት ነበር፡፡ ግን ያኔ ይኼም አይደንቀንም፡፡ የእናትየዋ ጭንቅላት እንደ ክዳን በማዞር ይከፈታል። ከውስጧ ትንሽ በመጠን አነስ የምትል እናት አሻንጉሊት ትወጣለች፡፡ “ልጅ ወለደች” እያሉ የጨዋታውን ቁም ነገር ሊያስረዱን ሳይሞክሩ አይቀርም፡፡ ከአንዷ ውስጥ ሌላ ሲወጣ እያሳዩ አዋልደዋቸው ጨረሱ። ጎን ለጎን ደርድረው በትልቋ እናትና በሚጢጢየዋ መሃል ያለውን የንፅፅር ዝርዝር አሳዩን፡፡
መጀመሪያ ጠፍተው ያለቁት ትንንሾቹ ናቸው፡፡ ትልልቆቹ ደግሞ ማህፀናቸው ክፍት ስለነበር በቀላሉ ሲወረወሩ ተሰበሩ። በመጠኑም ቢሆን ቅርፃቸውና ሲወረወሩ የሚያወጡት ደረቅ የሚንኳኳ ድምፃቸው ትዝ ይለኛል፡፡
ሩሲያ ለትምህርት የሄደ ዘመድ ያለው ከአሻንጉሊቱ በበለጠ የሚላክለት የሩሲያ ፎቶግራፍ ነበር፡፡ የሰው ጉርድ ፎቶግራፍ ወደ ሩሲያ በፖስታ ቤት ይላክና በጣውላ እንጨት ላይ መስታወታማ የመሰለ፣ የተወለወለ ምስል ታትሞ ተመልሶ ይመጣል። የታናሽ እህቴ፣ የወንድሜና የእኔ ምስልም በዚህ መልክ ተሰርቶ እዛው ቤተሰቦቼ ቤት አሁንም ተቀምጦ ይገኛል። ፎቶግራፎቹ ከፍ ብለው ስለሚሰቀሉና ልጆች እንዲጫወቱበት ከተሰቀለበት ወርዶ ስለማይሰጥ፣ እድሜው መርዘም ችሏል። አለበለዚያ እሱም እንደ አሻንጉሊቱ፣ እድሜው አጥሮ ከህልውና ተፍቆ በቀረ ነበር፡፡
አሻንጉሊቱ ትዝ የሚለኝ፣ የሆነ ፊልም ላይ እንዳጋጣሚ የታየ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ በልጅነቴ ሊገባኝ የማይችለው የአሻንጉሊቱ እንቆቅልሽ ለበስ ባህሪ፣ በእድሜ ከፍ ካልኩኝ በኋላ ግልጽ እያለ እየታየኝ መጣ። በተቃራኒው የራሴው ምድራዊ አምሳያና ምትክ መሆኑ የማያጠራጥረኝ ከጠፍጣፋ እንጨት የታነፀው የልጅነቴ ፎቶግራፍ ደግሞ ምንም ትርጉም የሌለው ምስል ሆኖብኛል። ያ በፎቶው ላይ የሚታየው ህፃን እኔ ራሴ ስለመሆኔ ምንም ማረጋገጫ ማቅረብ አቅቶኛል፡፡
ሦስቱም ፎቶግራፎች እርስ በራሳቸው ዝምድና እንዳላቸው ያስታውቃሉ፡፡ የተሰሩበት ዘመንና ጥሬ እቃ ያመሳስላቸዋል። አሁን በተጨባጭ በተለያየ ስፍራና የህይወት ጎዳና ላይ ካሉት ወንድማማቾችና እህት ጋር ፎቶግራፎቹ ያላቸው ዝምድና ግን ግልፅ አይደለም፡፡ አሁን ግልፁ ነገር ሁሉም ማናቸውንም አለመምሰላቸው ብቻ ነው፡፡ “ ይሄ እኔ ነኝ” እል ነበር፤ ድሮ ልጅ እያለሁኝ። ወይም ደግሞ፣ ሌሎች “ይሄ ቶቲ ነው” ይሉ ነበር፡፡ በምስሉና በአምሳያው መሃል ያንን ያህል ልዩነት አልነበረም፡፡ በፎቶግራፍ ሳይሆን በአካል ያለች ከእሷ በወቅቶች ልዩነት የተወለደች እህቷን በስጋና በደም የምትንቀሳቀስ ፎቶግራፍ መስላት “እሷ እኔ ናት” ያለችም ህፃን መኖሯን ሰምቻለሁኝ፡፡
“ይሄ ማነው?” ብለው የሚጠይቁ ሰዎች የሚመጡት በሂደት ነው፡፡ ከብዙ አመታት በኋላ  በሀገረ ሩሲያ የሚሰሩ ምስሎችና የሩሲያው ሃያል መንግስት እንደ አሻንጉሊቷና እንደ ልጆቿ ተበታትነውና ተሰባብረው ጠፉ፡፡
ድሮ እኔ ልጅ እያለሁኝ “ይሄ አንተ ነህ" እያሉ የእኔን ማንነት ከሩሲያ ስሪቱ ፎቶግራፍ ጋር ለማስተሳሰር ይተጉ የነበሩት ሰዎች ዞር ብለው ሲመለሱ፣ እኔ አድጌ ነበር የጠበቅኋቸው፡፡ እነሱ ራሳቸው ለእኔ በልጅነቴ ያስጠኑኝን ስለረሱት፣ እኔ መልሼ ፎቶግራፉ እኔ ስለመሆኔ ማሳመን ይጠበቅብኝ ጀመር፡፡
አሁን ማንም ያ ፎቶግራፍ እኔ መሆኔን አያምንም፡፡ በሙሉ የማይናወጥ እምነት የምታምነው ምናልባት እናቴ ብቻ ነች፡፡ ለእሷ ፎቶግራፉ የተለየ ትርጉም ነበረው። ምናልባት ወደ ራሷ ትዛታ የመግቢያ በርን ወለል አድርጎ ስለሚከፍትላት ሊሆን ይችላል፡፡  እኔ አሁን በተጨባጭ ሆኜ ከምታያት የበለጠ እኔን መወከል ያቆመው የሩሲያ ስሪት ፎቶግራፍ የበለጠ ይገባታል። አሁን በአካል ስላለሁት እኔ ብዙም የምታውቅ አይመስለኝም፡፡ እሷ ወልዳ ከሰራችኝ የቀድሞው እኔነት አፈንግጫለሁ። ስለ እኔ ብዙም የምታውቅ አይመስልም፡፡ ትንሽ ሳላስፈራትም አልቀርም፡፡ ድሮውንም መሃል ላይ የተወለደ ልጅ አስቸጋሪ ስለመሆኑ እየደጋገመች ትናገር ነበር፡፡
በግራና በቀኝ እጇ ታላቅ ወንድሜንና ታናሽ እህቴን  አጥብቃ ይዛ፣ እኔን ግን ሦስተኛው እጇ ሊይዘኝ ስለማይችል ለብቻዬ አመልጣለሁኝ፡፡ አንዳንድ ጊዜ በጣም ለመታወስ ስለምፈልግ ሊሆን ይችላል እዛው እፊታቸው ቆሜ ከእናካቴው የሚረሱኝ፡፡ ግን እንደዛ እየረሱኝም፣ አሁን አድጌ እራሴን ፈፅሞ ከረሳሁት በተሻለ እነሱ ሳያስታውሱኝ የሚቀሩ አይመስለኝም፡፡ የተሻለ ያስታውሱኛል፡፡ ከእድገቴ የበለጠ ልጅነቴን ያስታውሳሉ፡፡ በተለይ እናቴ። ስለ ወንድምና እህቴ አሁን አሁን ብዙም አላውቅም፡፡
የእንጨቶቹ ፎቶግራፎች፣ ቢያንስ በእንጨታዊ ርዝመትና ወርዳቸው ከተለኩ ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ቢያንስ የወላጆቼ ጥንታዊ ሳሎን ቤት ውስጥ ከእሳት ማንደጃው በላይ ባለው መደርደሪያ ላይ ጎን ለጎን ሆነው ተኮልኩለው ዘወትር በአንድ አይነት ቅርፅና ይዘት ይገኛሉ፡፡ ሁሌ ጎን ለጎንና ሁሌ ቅደም ተከተላቸውን ሳያዛንፉ፡፡ታላቅና ታናሽ ልጆች ዳርና ዳር፤ መሃከለኛው መሃል ላይ፡፡
የትኛዋም ሰራተኛ እዛ ቤት ስትቀጠር ከምትመራባቸው የማይናወጡ የስራ መርሃ ግብሮች መሃል፣ ፎቶግራፎቹን በንፁህ ጨርቅ መወልወል ዋነኛው ነው፡፡
ፎቶግራፎቹ ራሳቸውን አይጠብቁም፣ ግን ደግሞ ራሳቸውንም አይጥሉም፡፡  ፎቶግራፎቹ በአሁኑ ቅፅበት የት እንደሚገኙ ጠንቅቄ አውቃለሁኝ፡፡ ነገር ግን፣ በተቃራኒው ታላቅ ወንድሜ የት ሃገር እንደሚገኝ መረጃው የለኝም፡፡ ፎቶግራፎቹንም የት እንደሚገኝ ብጠይቃቸው የሚመልሱልኝ አይመስለኝም። ስለማይመስለኝ፣ ባገኛቸውም እንደዚህ አይነቱን መረጃ አልጠይቃቸውም።
ባለፈው፣ አንድ ከታላቅ ወንድሜ ጋር የተማሪ ቤት ገበታ ተጋርቻለሁኝ የሚል ሰው፣ መንገድ ላይ አስቁሞ ጠየቀኝ፡፡ ምንም መልስ ልሰጠው ግን አልቻልኩኝም። “ወንድምህ የት ሀገር ነው ያለው?” የሚል ጥያቄ ነበር ያቀረበልኝ፡፡ አይኔ ፈጦ ቀረ፡፡ “የሆነ እስካኒዴቪያን ሀገር መሰለኝ ያለው” ብዬ በጥርጣሬ የተቻለኝን መልስ ልሰጠው ብሞክርም፣ የእሱ አይን ብቻ ሳይሆን የፈጠጠው አፉንም ከፍቶ ቀረ፡፡
በኋላ ግን በራሱ ደግሞ መልሶ አፈረ፡፡ ምክኒያቱም ሁሉም ሰው ድሮ የት እንደነበረ እንጂ አሁን የት እንዳለ በትክክል ማወቅ እያቃተው ስለመጣ ነው፡፡ እሱ ራሱ የት እንዳለ በእርግጠኝነት እንደማያውቅ አኳኃኑ ያሳብቅበታል፡፡ ድሮ ምን እንደነበረና ምን እንደሚሰማው እንጂ የዛሬውን በእርግጠኝነት ላያውቅ ይችላል፡፡ የወንድሜን አድራሻ እኔን መጠየቁ ተገቢ እንዳልሆነ በአጭሩ ከገለፀልኝ በኋላ ይቅርታ ጠይቆኝ ተለየኝ፡፡ እኔ ግን ፀፀቴን ይዤ ብቻዬን ቀረሁኝ፡፡
እርግጠኝነት፤ ወደ ድሮ ጊዜ ይቀርባል። ወደ ፎቶግራፎቹ፡፡ ወደ ጥንቱ ደረቅ እንጨትነት፡፡ የሩሲያዋ አሻንጉሊት መሬት ላይ በደረቅ አካሏ ወድቃ ስትንኳኳ የምትፈጥረው ቅላፄ፣ አሁን በዙሪያዬ ከምሰማቸው እውን ድምፆች የበለጠ ይጎሉብኛል፡፡ ትርጉምም ይሰጡኛል፡፡ ምናልባት የቅርቡን ማስታወስ የማልችለው፣ የሩቁ የበለጠ ጮክ ብሎ ስለሚሰማኝ ሊሆን ይችላል፡፡
እናቴ ከእኔ የበለጠ ወንድሜ እንደሚናፍቃት ይገባኛል፡፡ የሚገባኝ እርግጠኛ ስለሆንኩኝ ነው፡፡ ታናሽ እህቴ አሁን ሦስት ልጆች ወልዳለች፡፡ እናቴን እንደ ትልቋ የሩሲያዋ አሻንጉሊት እመስላታለሁኝ። ትልቋ ተከፍታ ከውስጧ የሚወጡትን ደግሞ እንደ እኔና ሁለቱ ወንድምና እህቶቼ፡፡ እህቴ አሁን ከውስጧ ሌሎች ትንንሾች ማውጣት ቀጥላለች፡፡ የእህቴ መልክ የእናቴን ቁርጥ መሆኑ ራሱ ከእኔ የተሻለ ለሩሲያ አሻንጉሊታዊ ጨዋታ ይቀርባል፡፡
የእኔ ጭንቅላት ቢከፈት ከውስጡ ምን እንደሚወጣ አላውቅም፡፡ ሞክሬ ማየትም አልፈልግም፡፡ ሚስትም አላገባሁም ልጅም አልወለድኩም፡፡ እናቴ፣ በቀኝ የአዕምሮዋ ጎን የጠፋውን ወንድሜን መመለስ እየናፈቀች፣ በግራው በኩል ደግሞ የሴት ልጇ ዘንድ አዘውትራ ትደውላለች፡፡ በቀኝና በግራ ልክ እንደ ድሮው  ስትወጠር  እኔ በመሃል ቤት እረሳለሁኝ፡፡
ግን እናቴ ረስታኝ እንዳትቀር ቶሎ ቶሎ እየተመላለስኩኝ እጠይቃታለሁኝ። ብዙ ጊዜ ልጠይቃት የምሄደው ጠኔ የራሴን ከርስ ሲጠይቀኝ ስለመሆኑ ማመን አልፈልግም፡፡ ለራሴ ፍላጎት ቅድሚያ ሰጥቼ ቢሆንም፣ ብቻ ግን እጠይቃታለሁኝ። ምናልባት ራሴንም ማስታወስ ስለምፈልግ ሊሆን ይችላል፡፡ ራሴን የተሻለ ማስታወስ የምችለው ድሮ ባደግሁበት ቤትና ባሳደጉኝ ሰዎች አማካኝነት ነው፡፡ ወይም ነው ብዬ አስባለሁኝ፡፡ ብቻ አዘውትሬ እሄዳለሁኝ፡፡
በሄድኩኝ ቁጥር ግን፣ እናቴ የበለጠ እየረሳችኝ የመጣች ለምን እንደሚመስለኝ አላውቅም፡፡ እየረሳችኝ ከመጣችም በአዲሱ እኔነቴ ምክኒያት ነው፡፡ አዲሱን እኔነቴን ነው እንደ አዲስ ማስተዋወቅ የሚሰለቸኝ። ግዴለሽ እኔነቴን፡፡ ወንድምና እህቶቹን የረሳውን እኔነቴን፡፡ እናቴ እሷንም ጨምሬ እንዳልረሳ ከምትሰጋው ይበልጥ፣ ራሴን በጥንቱ መንገድ መልሼ እንዳስታውስላት የምትጓጓበት የምኞት ጉልበት ይበረታል። እኔ ግን የማስታወስ ክህሎቴ እየተዳከመ የመርሳት ብቃቴ ደግሞ እለት በእለት እየጠነከረ መጥቷል፡፡ አላፊና ጠፊዎቹን አጋጣሚዎች፣ በነባሮቹና ዘላቂ መሆን በነበረባቸው ላይ በመወጠር የምጫወተው ዥዋዥዌ፣ አንዳንድ ጊዜ፣ በንዴት ድንገት እንድትጦፍ ያደርጋታል፡፡
አንዳንድ ጊዜ ትንሽ ልቀልድባት ስፈልግ ሆነ ብዬ አበሽቃታለሁኝ፡፡ የማበሽቃት በፎቶግራፎቹ አማካኝነት ነው፡፡
ድሮ አባቴ በጎረመሰበት ዘመን የቴክኖሎጂው ደረጃ መጠነኛ ቴሌቨዥን የሚያክል ካሜራ አንጠልጥሎ፣ በሌላ ተመሳሳይ ካሜራ ሌላ ሰው እንዲያነሳ ማድረግን እንደ ፋሽን የያዘ ነበር፡፡ ከእጅ ካሜራ በተጨማሪ፣ ብዙ ክምችት ያሉ ቁልፎችን በቀበቶ ላይ በሚቆለፍ ማንጠልጠያ ማንገብም የዘመኑ ሀሪፍነት መገለጫ ነበር፡፡
ስለዚህ አባቴ ልጆች ሳለን ከከተማ ወጣ ወዳለ ስፍራ ወስዶን የማይታጠቡ ብዙ ፊልሞች ያነሳን ነበር፡፡ ፊልሞቹ መረገዛቸው እንጂ ተወልደው ነፍስ መዝራታቸው ያን ያህል አያሳስበውም ነበር፡፡ የዛ ዘመን ፊልም ነፍስ እንዲዘራ  በኬሚካል ውሃ አጥቦ፣ በደረቅ የፊልም ወረቀት ላይ አትሞ፣ በአልበም ተሰንዶ ቤት ውስጥ መቀመጥ ነበረበት፡፡ የፊልሞች ባህሪ ራሱ የሰዎችን ይመስል ነበር፡፡ ምግብ ልብስና መጠለያ ካላገኙ የፎቶግራፎቹም እድሜ ያጥር ነበር፡፡
አባቴ የብዙ ሰዎችን ፎቶ አንስቷል። ከሚያውቃቸው ሰዎች ይበልጥ የማያውቃቸውን፡፡ የሆነ የተደበቀ አርቲስትነት በውስጡ ሳይበቅልበት አልቀረም፡፡ ሳይኮተኩተውና ሳያርመው እዛው ተውጦ መከነበት እንጂ፡፡ ፎቶ ለማንሳት ሲል በርከክ የሚለው ነገር ነበር። በርከክ በማለቱ ምክኒያት የሚነሱት ሰዎች ፎቶ ቀረፃ ውስጥ ሊካተቱ እንደሆነ ስለሚነቁ ምራቃቸው በጉሮሮአቸው ሳይዋጥ ደርቆ ይቀራል፡፡ እንጨት የዋጡ ይመስላሉ፡፡ መንበርከክ በእርጅና ምክኒያት እስኪያቅተው ድረስ፣ የማያውቃቸውን ሰዎች ፎቶ ሲያነሳ ይውል ነበር፡፡ የስራ ዘርፉ ከካሜራ ጋር ፈፅሞ የሚያገናኘው እንዳልሆነ መጥቀስ አያስፈልግም፡፡ አንዳንድ ጊዜ የግድ ሲሆንበት ፎቶግራፎች ያሳጥባል፡፡ ከእጥበቱ የሚገኙት ፊቶች ቢታጠቡም ጉስቁልናቸው የማይለቃቸው አይነቶቹን ናቸው፡፡ በዚህ ድርጊቱ እናቴ አብዝታ ትበሳጭበት ነበር፡፡ እሷ በካሜራ እንዲያዙና ዘመን እንዲያስታውሳቸው ሆነው እንዲቀመጡ የምትፈልጋቸው ፊቶች የቤተሰቡን አባላት ብቻ ነው፡፡ የእርሷ የጥበብ ትርጉም ይሄ ብቻ ነው፡፡
ልጠይቃት ስሄድ ከዚህ የሚነሳ ቀልድ ወደሷ እወረውራለሁኝ፡፡ ወደ ሶስቱ የሩሲያ ስሪት የእንጨት ፎቶግራፎች እጄን እየጠቆምኩ፡-
“እነዚህ የእነ ማርክስ፣ ኤንግልስና ሌኒን የልጅነታቸው ፎቶግራፍ ነው፤ አይደለም?” እላታለሁኝ፡፡
“ልክ ነህ!... የአንተ ግን የትኛው ነው?” ትለኛለች፡፡
“እኔማ የለሁበትም፡፡ ድሮ የመሃከለኛው የአንተ ፎቶግራፍ ነው ብላችሁ የተጫወታችሁብኝ ይበቃል፡፡ እንዲያውም እነዚህን ፎቶዎች አባባ ዝም ብሎ መንገድ ላይ ያገኛቸውን ህፃናት አንስቶ ያሳጠባቸው እንደሚመስለኝ መችም ከዚህ ቀደም አጫውቼሻለሁኝ…”
እኔ እንደ ቀልድ ብወስደውም እሷ ግን ድንገት ሆድ ይብሳታል፡፡ ብዙ ነገሮችን በአንድ ላይ አስሬ ስለወረወርኩባት ሳይሆን አይቀርም፡፡
አግባብቼ፣ ቀልዴን እንደሆነ አብብዬ ነግሬ ተሰናብቻት ስወጣ በሩ ላይ ቆማ እስክርቅ ቆማ ትመለከተኛለች፡፡ ወደ ኋላ ዞሬ ሳስተውላት፣ እይታዋ እኔ ላይ ሳይሆን  በራሷ ውስጥ ተውጣ የቀረች ትመስላለች፡፡
ቅርጿ ራሱ የሩሲያዋን አሻንጉሊት ነበር የሚያስመስላት፡፡ ግን ጭናቅላቷ ቢከፈት ከውስጧ ማውጣት የሚቻሉ ልጆች የሏትም፡፡ ከውስጧ የሚወጡትን ሳይሆን ውስጧ ተቀብረው የቀሩትን ነበር በር ላይ ቆማ የምታያቸው፡፡ የተሻለ የሚታዩዋት፣ በውን ካሉት ይበልጥ ውስጧ ተቀብረው የቀሩት ናቸው፡፡ እኔ አልታያትም፡፡ አይኗ ላይ ያስታውቃል፡፡
ከእኔ የበለጠ የሞተውን አባቴንና እንደወጣ ሳይመለስ የቀረውን ታላቅ ወንድሜን ነበር እዛ በር ላይ ቆማ ማዶ ማዶ አሻግራ የምታያቸው፡፡ በራቅሁ ቁጥር በቦውሊንግ ከባድ ኳስ ተጨርፎ እየተንገዳገደ ግን በመውደቅና ቆሞ በመቀጠል መሃል መወሰን እንዳልቻለ ብርሌ ነበር የምትመስለው፡፡
ከራሴ የበለጠ እሷ ትዝ ትለኛለች። ከወንድሜና ከአባቴ፣ ከአባቴና መዐት ቁልፎቹ፣ ከእህቴና ከሴት ልጆቿ የበለጠ እሷ ትዝ ትለኛለች፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ ፈራሁኝ፡፡ ራሴን ላለማጣት ፈራሁኝ፡፡ ከሁሉም ነጥብ ጋር የምታገናኘኝ እሷው ናት፡፡ ተመልሼ አንደገና ሳስተውላት በሩን ዘግታ ገብታለች፡፡ ግን አለች፡፡ ብትንገዳገድም ገና አልወደቀችም፡፡ ነገ በድጋሚ አያታለሁኝ፡፡
ምናልባት የሩሲያዎቹ አሻንጉሊቶች አልጠፉም፡፡ ስራዬ ተብለው ቢፈለጉ የጠፉት ተመልሰው ይገኙ ይሆናል፡፡ ምንም ነገር አኮ በመሰረቱ አይጠፋም፡፡ ጨክኖ ያለ-መፈለግ ወይም ያለመፈለግ ይሆናል እንጂ ምንም ነገር አይጠፋም፡Read 1811 times