Monday, 18 January 2021 00:00

መላው አሜሪካ በአመጽ ሊናጥ እንደሚችል ኤፍቢአይ አስጠነቀቀ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ትራምፕን ከስልጣን ለማውረድና በወንጀል ለመክሰስ ታስቧል

           ባሳለፍነው ሳምንት በታሪኳ አይታው የማታውቀውን ምርጫ አመጣሽ አመጽና ብጥብጥ ያስተናገደቺው አሜሪካ፣ በቀጣዮቹ ቀናትና በተመራጩ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በዓለ ሲመት ሰሞንም ታጥቀው በሚወጡ የትራምፕ ደጋፊዎችና ጽንፈኛ ቡድኖች ከዳር እስከ ዳር በአመጽ ልትናጥ እና ከፍተኛ ጥፋት ሊከሰት እንደሚችል ኤፍቢአይ አስጠንቅቋል፡፡
የጆ ባይደን በዓለ ሲመት እስከሚፈጸምበት ጥር 12 ቀን ድረስ በ50 የአገሪቱ ግዛቶች ውስጥ በሚገኙ የመንግስት መቀመጫዎች እንዲሁም በዋሺንግተኑ የፌዴራል መንግስት መቀመጫ ካፒቶል ሂል በትጥቅ የታገዙ አመጾች በትራምፕ ደጋፊዎችና በጽንፈኛ ቡድኖች ሊቀሰቀሱ እንደሚችሉ የፌዴራሉ ምርመራ ቢሮ ኤፍቢአይ ያስጠነቀቀ ሲሆን፣ በዓለ ሲመቱ በትራምፕ ደጋፊዎች አመጽና ብጥብጥ እንዳይስተጓጎል ለመከላከል ካፒቶል ሂል ዙሪያውን እየታጠረ እንደሚገኝም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የአሜሪካ ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት የተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች ከፈጸሙት የአመጽ ድርጊት ጋር በተያያዘ ፕሬዚዳንቱን በ25ኛው የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ማሻሻያ መሰረት ከስልጣን ለማውረድና ምክትሉ ስልጣኑን እንዲረከብ ለማድረግ ያሳለፈው ውሳኔ በምክትል ፕሬዝዳንት ማይክ ፔንስ ተቀባይነት ማጣቱን ተከትሎ፣ የአገሪቱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ ትራምፕን በኢምፒችመንት ከስልጣን ለማውረድና አመጽ በመቀስቀስ ወንጀል ለመክሰስ መዘጋጀቱ ተነግሯል፡፡
ትራምፕ ባላመኑበትና ባልተቀበሉት የምርጫ ውጤት ተሸንፈው ከነጩ ቤተ መንግስት ሳይወዱ በግድ ሊወጡ የቀራቸው የቀናት እድሜ ቢሆንም፣ ምክር ቤቱ ግን በአገሪቱ መንግስት መቀመጫ ህንጻ ላይ ደጋፊዎቻቸው የፈጸሙትን ህገወጥ ድርጊት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በኢምፒችመንት ከስልጣን ለማስወገድ መጣደፍ የጀመረው ሰውዬው በቀጣይ ምርጫዎች እንዳይሳተፉ ለማድረግ ነው መባሉን ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል፡፡
ዲሞክራቶች ፕሬዝዳንት ትራምፕን ጥቂት ቀናት ከቀረው ሥልጣናቸው ለማባረር የሚያደርጉት ጥረት ከሪፐብሊካን ፓርቲ አባላትም ድጋፍ እያገኘ መሆኑን የዘገበው ቢቢሲ፣ ትራምፕ ከሥልጣን እንዲባረሩ የሚጠይቀው ክስ እንዲመሰረትባቸው ድጋፋቸውን ከገለጹት መካከል ከፍተኛዋ የሪፐብሊካን ፓርቲ እንደራሴ ሊዝ ቼኒ እንደሚገኙበትም አመልክቷል፡፡
የትራምፕ ደጋፊዎች ባለፈው ሳምንት ረቡዕ በታላቁ የአገሪቱ ተቋም ካፒቶል ሂል ላይ በፈጸሙትና አምስት ሰዎችን ለሞት በዳረገው አጉራ ዘለል የአመጽና የብጥብጥ ድርጊት ተሳታፊ እና ተባባሪ ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ በርካታ የፖሊስ አባላት ከስራ መታገዳቸውንና በ15 ያህል ፖሊሶች ላይ ምርመራ እየተደረገ እንደሚገኝ የዘገበው ቢቢሲ፣ ጥፋተኛ ሆነው በተገኙት ላይ ከስራ እስከማባረር የሚደርስ እርምጃ ይወሰዳል መባሉን ገልጧል፡፡
ከአመጽ ድርጊቱ ማግስት ጀምሮ የተለያዩ ማህበራዊ ድረገጾች ትራምፕን በቋሚነትና በጊዜያዊነት ማገዳቸውን የገፉበት ሲሆን፣ ፌስቡክ፣ ኢንስታግራምና ትዊተር የትራምፕን አካውንቶች ከዘጉ ከቀናት በኋላ ሰሞኑን ደግሞ ዩቲዩብ ሰውዬውን ለአንድ ሳምንት አዲስ ቪዲዮ እንዳይለቅቁ ማገዱ ተነግሯል፡፡

Read 2966 times