Tuesday, 19 January 2021 00:00

ሙሴቬኒ ስልጣናቸውን ወደ 40 አመት ለማራዘም ቆርጠው ተነስተዋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  ላለፉት 35 አመታት ኡጋንዳን ያስተዳደሩት ዩሪ ሙሴቬኒ ትናንት በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለ6ኛ ጊዜ ለመመረጥና የስልጣን ዘመናቸውን ወደ 40 አመታት ለማራዘም ቆርጠው መነሳታቸው ተነግሯል፡፡
አገሪቱን ወደ ውጥረትና ብጥብጥ እያስገባት የሚገኘው የዘንድሮው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ነጻና ፍትሃዊ ይሆናል ብሎ እንደማይጠብቅ የተባበሩት መንግስታት በይፋ ማስታወቁን ተከትሎ፣ የውጭ አገራት መንግስታት በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባታቸውን እንዲያቆሙ ቀጭን ትዕዛዝ ያስተላለፉት ሙሴቬኒ፣ ፌስቡክን ጨምሮ የተለያዩ ማህበራዊ ድረገጾችን ማስዘጋታቸውንም አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡
ከስልጣን መውረድን እንደሞት እንደሚፈሩት የሚነገርላቸው ሙሴቬኒ፣ ከአራት አመታት በፊት ባደረጉት የህገ መንግስት ማሻሻያ የአገሪቱን መሪ የ75 አመት ዕድሜ ገደብ ማንሳታቸውን ያስታወሰው ቢቢሲ፣ በዘንድሮው ምርጫ ከሚወዳደሩት 10 ዕጩዎች መካከል የ76 አመቱን አዛውንት ዩሪ ሙሴቬኒን ያሰጋቸዋል ተብሎ የሚጠበቀው መንግስት ደጋግሞ ሲፈታ ሲያስረው የከረመው ቦብ ዋይኒ የተባለው ታዋቂ የአገሪቱ ድምጻዊ አንዱ ነው ብሏል፡፡
በአፍሪካ አህጉር ለረጀም ጊዜ በስልጣን ላይ የቆዩ 10 መሪዎችን ዝርዝር ይፋ ያደረገው ሮይተርስ በበኩሉ፣ የኢኳቶሪያል ጊኒው ቴዎዶሮ ኦቢያንግ 41 አመታት ከ5 ወራት፣ የካሜሩኑ ፖል ቢያ 38 አመታት ከ2 ወራት፣ የኮንጎ ሪፐብሊኩ ዴኒስ ሳሱ ኑጌሶ 36 አመታት ከ9 ወራት፣ የኡጋንዳው ሙሴቬኒ 34 አመታት ከ11 ወራት፣ የኢስዋቲኒው ንጉስ ሳዋቲ 34 አመታት ከ8 ወራት፣ የቻዱ ኢድሪሲ ዴቢ 30 አመታት ከ1 ወር፣ የኤርትራው ኢሳያስ አፈወርቂ 27 አመታት ከ7 ወራት፣ የጅቡቲው ኢስማኤል ኦማር ጌሌ 21 አመታት ከ8 ወራት፣ የሞሮኮው ንጉስ ሞሃመድ 6ኛ 21 አመታት ከ5 ወራት፣ የሩዋንዳው ፖል ካጋሜ 20 አመታት ከ8 ወራት በመግዛት እንደቅደም ተከተላቸው ከአንደኛ እስከ 10ኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውን አመልክቷል፡፡

Read 2889 times