Sunday, 17 January 2021 00:00

የዶላር ምንዛሬ በጥቁር ገበያ እያሻቀበ ነው

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(3 votes)

  በመደበኛ ባንኮች  የአንድ ዶላር የመግዣ ዋጋ 38 ብር የነበረ ሲሆን ትላንት ብሄራዊ ባንክ ባወጣው መረጃ፤ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ ብር 39.3284 ሲሆን የሚሸጥበት ደግሞ ብር 40.1149 መሆኑን አመልክቷል።
ከሁለት ወራት በፊት በጥቁር ገበያ አንድ ዶላር 44 እና 45 ብር ይመነዘር  የሚገልፁት ምንጮች፤ ከአንድ ወር በፊት 50 እና 52 ብር፣ ከገና በዓል በፊት በነበሩት ቀናት ደግሞ አንድ ዶላር እስከ 55 ብር ድረስ ሲመነዘር የቆየ ሲሆን፣ ከበዓል በኋላ ወደ 50 ብር ዝቅ ማለቱን ይጠቁማሉ።
 የዶላር ምንዛሬ ማሻቀብ የሚፈጠረው ምን ሲሆን ነው የሚል ጥያቄ ያቀረብንላቸው የፋይናንስና የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ኤርሚያስ አመልጋ፤ መሰረታዊ ችግሩ የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ፍላጎትና በብሔራዊ ባንክ በኩል የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማነቃነቅ የሚቀርበው የውጭ ምንዛሬ ተመን አለመመጣጠን ነው ይላሉ።  “ብሔራዊ ባንክ የሚያቀርበው የውጪ ምንዛሬ ከፍላጎቱ ጋር ካለመመጣጠኑም በተጨማሪ መንግስት ዋጋው ይህ ነው ብሎ በመቆጣጠርና በመገደብ ዝም ብሎ ቁጭ ስላደረገው ገበያው ደግሞ ይሄንን እንደማይቀበለውና በተገኘው ቀዳዳ ወደ ጥቁር ገበያው ተመን የማሾለኩ ስራ ስለሚበዛ በባንክ ከሚመነዘረው ጋር ሲነፃፀር የጥቁር ገበያው እጅግ ያሻቅባል” ሲሉም ያብራራሉ።
“ገንዘብ ማለት አየር ነው፤ አይጨበጥም አይገደብምም፤ ይሾልካል፤ ስለዚህ በምንም አይነት በመገደብና በመቆጣጠር የውጭ ምንዛሬ ችግሩን የፈታ አገር የለም” ባይ ናቸው አቶ ኤርሚያስ።
“የአንድ አገር ፍላጎት አለ አቅርቦት አለ። ሁለቱን የሚዳኛቸውና ሚዛን የሚያሲዛቸው ዋጋ ነው፤ ስለዚህ መንግስት ከሚቆጣጠር  ይልቅ ገበያው ይተምነው ብሎ መልቀቅ ነው ያለበት”
 አቶ ኤርሚያስ በሁለተኛነት የሚያነሱት ፍላጎት፣ አቅርቦትና ዋጋን ነው፤ ዋጋን ገድቦ በመያዝ እንዳይነቃነቅ ከተደረገ ወይ አቅርቦቱ ወይ ፍላጎቱ ይሆናል ሚዛን የሚያስይዘው ይላሉ። አቅርቦቱንም ዋጋውንም መንግስት ገድቦ በመያዙ ጫናው ፍላጎት ላይ ስለሚያርፍ የውጭ ምንዛሬ ፈላጊው ሳይወድ በግድ ወደ ጥቁር ገበያ እንዲያማትር ያስገድደዋል፤ የጥቁር ገበያው ዋጋ የሚያሻቅብብትም ምክንያት በስንት ውጣ ውረድ፣ ስንት ሂደቶችን አልፎ ስለሚመጣና ከአንዱ ወደ አንዱ ሲዘዋወር ሁሉም አትርፎ ስለሚያስተላልፈው እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡
ሌላው  የውጭ ምንዛሬ እጥረት ችግር፤ ኢትዮጵያ ያለችበት የእድገት ደረጃና ከምግብ ጀምሮ አብዛኛውን ቁሳቁስ ከውጭ የምናስገባ መሆናችን ነው፤ ስንዴን ጨምሮ ሌሎች የምንፈልጋቸውን ነገሮች አገር ውስጥ የማምረት አቅም አለመገንባታችን ችግር ጋርጦብናል ይላሉ አቶ ኤርሚያስ፡፡
ኢኮኖሚያችን ቢያድግም እንኳን እድገቱ ሚዛን የሌለውና በእቅድ ያልተሰራ፣ የአገር ውስጥ ፍላጎትን እዚሁ የማምረት አቅምን ያልገነባ በመሆኑና በሌላ በኩል የሚያስፈልገውን ነገር ከውጭ ገዝቶ ለማምጣትም የሚያስችለው አቅም ያልተፈጠረ በመሆኑ ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን አቶ ኤርምያስ ያስረዳሉ።
እነዚህን ችግሮች ለማሟላት የግሉ ዘርፍ እንቅስቃሴ ያስፈልጋል ያሉት ባለሙያው፤ መንግስት ኤክስፖርተር ሊሆን አይችልም፤ ኢንቨስትመንትን መሳብም አይችልም፤ መበደር ብቻ ነው፤ የግሉ ዘርፍ እንቅስቃሴ ግን በብዙ መልኩ አገሪቱን ሊያግዝ የሚችል ስለሆነ መንግስት የግል ዘርፉን አጠናክሮ ማስቀጠል ነበረበት፡፡ አንዱ መሰረታዊ ችግራችንም፤መንግስት የግሉን ዘርፍ አጠናክሮ አለማስቀጠሉ ነው ብለዋል።

Read 13099 times