Saturday, 23 January 2021 11:08

በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ ላይ ከቀረቡ ክሶች ስድስቱ እንዲቋረጡ ተወሰነ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

  በእነ አቶ ጃዋር መሃመድ ላይ ከቀረቡ ተደራራቢ አስር ክሶች ስድስቱ እንዲቋረጡ ፍርድ ቤት ውሳኔ አስተላልፏል።
የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ፤ የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል አዋጅ ፤ የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ የመተላለፍ ክሶች ከተመሰረቱባቸው ክሶች መካከል ሲሆኑ፣ በፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲቋረጡ የተደረጉት ክሶች ከጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ጋር የተያያዙ መሆናቸውም ተገልጿል።
ፍርድ ቤቱ ጥር 4 ቀን 2013 ዓ.ም በነበረው ችሎት፣ አቃቤ ሕግ ክሶቹን አሻሽሎ እንዲያቀርብ ማዘዙ ይታወሳል። ነገር ግን አቃቤ ሕግ ሌሎቹን ክሶች እንዳሻሻለ ጠቁሞ፤ የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ መሰረት በማድረግ የተከፈቱትን ክሶች ማሻሻል እንደማይፈልግ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።
ፍርድ ቤቱም፤ክሶቹ በተጠቀሰው አዋጅ ስር መታየት እንደማይችሉ በመጥቀስ፣ እንዲቋረጡ ውሳኔ አስተላልፏል።
የቀሩት አራት ክሶች “ብሔርንና ሐይማኖትን መሰረት ያደረገ የእርስ በርስ ግጭት በመቀስቀስ፣አንዱ ወገን በሌላው ወገን ላይ እንዲነሳሳ በማድረግ”፣ የፀረ ሽብር አዋጅና የቴሌኮም ማጭበርበር አዋጅን የሚመለከቱ ናቸው።
ፍርድ ቤቱ እነዚህን ማሻሻያዎች ጨምሮ ክሱን ለተከሳሾች ካነበበ በኋላ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሲጠይቅ፣ ጠበቆች የእምነት ክህደት ከመስጠት በፊት ክሱ በተገቢው መንገድ መሻሻሉን ለማየት ቀነ ቀጠሮ ይሰጠን ሲሉ ጠይቀዋል። በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ ለጥር 19 ቀን 2013 ዓ.ም ቀጠሮ ይዟል።
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አመራር አባል የሆኑት አቶ ጃዋር መሐመድ እና አቶ ደጀኔ ጣፋ ለፍርድ ቤቱ ምንም አይነት ወንጀል እንዳልፈፀሙና የቀረበባቸው ክስ በመጪው አገራዊ ምርጫ ላይ እንዳይሳተፉ ሆን ተብሎ የተደረገ እንደሆነ አስረድተዋል።
“ምንም ወንጀል እንዳልፈፀምን አቃቤ ሕግ ራሱ ያውቃል፤ እኛ ብንወጣና ምርጫው ላይ ብንሳተፍ ለአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ጥቅም ይኖረዋል” ብለዋል፤አቶ ጃዋር፡፡

Read 12632 times