Print this page
Sunday, 24 January 2021 00:00

መፅሐፈ ሔኖክ - ኢትዮጵያ የታደገችው የሰው ልጆች አሻራ

Written by  በመኮንን ተሾመ ቶሌራ
Rate this item
(1 Vote)

     "--ታላቁ የዘመናችን የጥንታዊ ግእዝ ምሁር ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ “አከራካሪ መጽሐፍ” ያሉትን መፅሐፈ ሔኖክን፤ “ይህ መጽሐፍ ከየትኛውም የሲኖዶስ ቅጂ ውስጥ ተዘርዝሮ አይገኝም፣ ከሰማኒያ አንዱ መጻሕፍተ ሕግ አንዱ አይደለም።” ሲሉ ገልፀውታል።--"
                         
           መፅሐፈ ሔኖክ የሰዉ ልጆች በጥንት ዘመን ከፃፉአቸው መፃህፍት አንዱ ሲሆን የኖህ ቅድመ አያት በሆነዉ በሄኖክ በእብራይስጥ ቋንቋ እንደተፃፈ ይታመናል። በሔኖክ እንደተፃፈ የሚነገረው ይህ መጽሐፍ ከአለም ላይ ከ2ሺ አመታት በላይ በእብራይስጥም ይሁን በሌሎች ቋንቋዎች የነበሩት ቅጂዎቹ በሙሉ ጠፍተው ወይም እንዲጠፉ ተደርገው ስለነበር የሰው ልጅ የዚህን ታላቅ ስራ ዱካውን ማግኘት ሳይችል ቆይቶ ነበር።
ይሁንና ብርቱዎቹ የኢትዮጵያ የሃይማኖት አባቶችና መነኮሳት በነበራቸው አለማቀፍ ግንኙነት መጽሐፉን ካለበት ቦታ በማምጣት ሙሉ በሙሉ በቁም ፅሁፍ (Calligraphy) በብራና ገልብጠውት ስለነበር አለማችን መልሳ ልታገኘው ችላለች። በዚህም መፅሐፈ ሔኖክን ጠብቃ በማቆየቷ ኢትዮጵያ ለመላው አለም ታላቅ ውለታ ለመስራት ችላለች።
መፅሐፈ ሔኖክ በቅዱስ መፅሐፍ አዲስ ኪዳን ሦስት ቦታዎች ላይ ማለትም በሉቃስ 3:37 ፣ እብ 11:5 እንዲሁም ይሁዳ 1:14-15 ላይ የተጠቀሰ ታላቅ ክርስቲያናዊ የሃይማኖት መፅሐፍ ነዉ። የክርስትና ሃይማኖት ታሪክንና ትርክቶችንም የተሟላ ለማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መጽሐፍ እንደሆነ በበርካታ ምሁራን ይታመናል።
ይሁንና መፅሐፉ የአይሁድና የፕሮቴስታንት ሀይማኖቶችን ጨምሮ በበርካታ የሃይማኖት አባቶች ትኩረት ተነፍጎት ቀኖናዊ እንዳይሆን ተደርጎ ይልቁንም የኦሪት ዘመን መጽሐፍ (deuterocanonical) ነው በሚል በየቅዱስ መፅሃሐቶቻቸዉ ጥራዝ ውስጥ እንዳይካተት አድርገዋል።
የተለያዩ ሀይማኖቶች በተለያዩ ጊዜያት በተደረጉ የሲኖዶስ ውሳኔዎች መሰረት በየቅዱስ መፅሐፍቶቻቸዉ (sculptures) መካተት ያለባቸውን መፃሕፍት እንደወሰኑ ይታወቃል።
በዚሁ መሰረት የካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን 73 ቀኖናዊ መፃሕፍተን የምትቀበል ሲሆን አይሁዶች 24 መፃሕፍት አላቸው፤ በቁጥራቸዉ እጅግ ብዙ የሆኑት የፕሮቴስታንት አብያተ-ክርስቲያናት ደግሞ 66ቱን መፃሕፍት ቀኖናዊ አድርገው ይጠቀማሉ። እነዚህ የሃይማኖት ተቋማት በሙሉ ግን መፅሐፈ ሔኖክን በመፅሐፍ ቅዱሶታቸው ውስጥ አላካተቱም።
እንዳንዶች አሰተያየታቸውን ሲሰጡ፤ በአዲስ ኪዳን እዉቅና የተሰጠው የሔኖክ መፅሐፍ ቢያንስ በአይሁዶች ቀኖናዊ መፃህፍት እንኳን ተካቶ ቢሆን ኖሮ ለብዙ ዘመናት ጠፍቶ አይቀርም ነበር ይላሉ።
ይህን በተመለከተ ታላቁ የዘመናችን የጥንታዊ ግእዝ ምሁር ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ “አከራካሪ መጽሐፍ” ያሉትን መፅሐፈ ሔኖክን፤ “ይህ መጽሐፍ ከየትኛውም የሲኖዶስ ቅጂ ውስጥ ተዘርዝሮ አይገኝም፣ ከሰማኒያ አንዱ መጻሕፍተ ሕግ አንዱ አይደለም።” ሲሉ ገልፀውታል።
ፕሮፌሰር ጌታቸው ይህን ሲሉ የመጽሐፉ ሙሉ ቅጂ በግእዝ ቋንቋ ከኢትዮጵያ ከመገኘቱ በፊት ቀደም ብሎ እና የሃገራችን ሊቃዉንትም ከንጉስ ዘርዓያቆብ ዘመን ጀምሮ ክርክር አድርገው ከመወሰናቸው በፊት ይሁን አይሁን ግን ግልጽ አያደርጉም። ምክንያቱም እሳቸው እንዳሉት መፅሐፈ ሔኖክ በአለም ዙሪያ አከራካሪና በቀኖናዊነት ቅቡልነት የሌለው ቢሆንም፣ አሁን ላይ ግን መጽሐፉን ለምዕተ ዐመታት ጠብቃ ባቆየችው በኢትዮዽያና እንዲሁም በኤርትራ ሰማኒያ አንዱ መፃሕፍት ተካትቶ እናገኘዋለን።
መፅሐፉ አከራካሪ የሆነበት ምክንያት የመፅሐፉ ዋና ዋና ሀሳቦች በሌሎች ቅዱሳን መፃሕፍት መገለፃቸውና በሄኖክ ዘመን የፅህፈት ዘዴ ገና ባለመፈጠሩ እንዴት ሄኖክ መፅሐፉን ሊጽፍ ቻለ የሚል ጥያቄ ስላለ ነው (ጌታቸዉ 51፣2012)።
ፕሮፌሰር ጌታቸው “ከግእዝ ሥነ ጽሑፍ ጋር ብዙ አፍታ ቆይታ” በተሰኘዉ መፃሕፋቸው (ጌታቸዉ 50፣2012) “ከጠፋበት ምክንያት አንዱ ሲኖዶስ ውስጥ ባለመግባቱ [በሲኖዶሶች ባለመመረጡ] ይሆናል፣ ለምን አልገባም? የመፅሐፍ ቅዱስን መጠን የወሰኑ አባቶች ብዙ መፃሕፍት አስቀርተዋል፣ ወንጌላቱም አራቱ ብቻ እንዲሆኑ የወሰኑት እነሱ ናቸው።” ይላሉ፡፡
መጽሐፉ በኢትዮጵያ ቀኖናዊ መፃሕፍት ውስጥ እንዲካተት ብዙ ክርክር እንደተደረገም ፕሮፌሰር ጌታቸዉ ጽፈዋል። በተለይ ንጉስ ሀርዓያዕቆብ መፅሐፈ ሔኖክን የሚተቹትን ኢትዮጵያውያን ሊቃውንትና የሲኖዶስ አባላት በሃሳብ ክፉኛ ይሞግቷቸውና በቁጭትም ይፅፉ እንደነበረ ይገልጻሉ።
“ሔኖክን የምትክድ ከሃዲ ሰው ሆይ - ስማ፣ ኦሪትም የሄኖክን ክብር እንዲህ ስትል ትናገራለች፣ ‘ሔኖክ እግዚአብሄርን አስደሰተው፣ አልተገኘምም፣ እግዚአብሄር ደብቆታልና።’” ሲል ፅፎ መፅሐፉ ከ81ዱ መፃሕፍት ዝርዝር ውስጥ መግባት እንዳለበት መከራከሩን ጠቁመዋል። [“አልተገኘምም፣ እግዚአብሄር ደብቆታልና” ያለዉ በመፅሀፍ ቅዱስ መሰረት ሄኖክ ከጥፋት ውሃ በፊት ያረገ የመጀመሪያው ሰው በመሆኑ ነዉ። ከጥፋት በኋላ ደሞ ኤልያስና እየሱስ ክርስቶስ ስጋቸውን ነፍሳቸውንና መንፈሳቸውን ይዘው ወደ ሰማይ ተነጥቀዋል ተብሎ ይታመናል፡፡]
በመፅሐፉ ዙሪያ ካለው ክርክር ባለፈም የመጽሐፉ መገኘት ለሀይማኖት ታሪክ ጠቃሚ መሆኑን አመልክተዋል።
ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅ “The Ethiopian Orthodox Tawahidi Church” በተሰኘው መፅሐፋቸው የመጽሐፉን ጠቀሜታ በተመለከተ ሲያብራሩም፤ መፅሐፈ ሄኖክ ለግዝእ ስነ-ፅሁፍ ልክ ፑሽኪን ለሩሲያ ስነ-ፅሁፍ እና ሼክስፒር ደሞ ለእንግሊዝ ስነ-ፅሁፍ ያላቸውን ያህል ክብደት እንዳለው ፅፈዋል። “For Ethiopic literature, the Book of Enoch is like Pushkin for Russian literature and Shakespeare for English literature.” (Ephraim I. PP 66:2013)
ፕሮፌሰር ኤፍሬም እንዳሉት፤ መፅሐፈ ሔኖክ በአለም ላይ ጠፍቶ ሙሉ ጥራዙ በግዕዝ ቋንቋ እንደመገኘቱ በቋንቋው ባህሪያትና አገላለፅ ምክንያትና አሁን እንደ ኦሪጂናል ተደርጎ የሚጠቀሰው ግእዙ በመሆኑ ለሀገራችን የሚኖረው ጠቀሜታ ከፍ ያለ መሆኑ አይቀርም።
አሁን ላይ በተለያዩ አለማትና የሀገራችን ገዳማት የሚገኙት የመጽሐፉ ቅጂዎች የተፃፉበት መንገድና አቀራረብ (የምእራፍ አከፋፈል፣ ቁጥር አሰጣጥ፣ ጥረዛ፣ ህዳግና ስዕል አሳሳል) ቅጂዎቹ እንደተገለበጡበት ዘመንና ፀሀፊዎች ይለያያሉ።
ቀደም ብሎም በ18ኛው ክፍለ ዘመን የአባይን መነሻ ለማሰስ ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ አሳሾች መካከል ጀምስ ብሩስ የተባለ ስኮትላንዳዊ ሁለት ቅጂዎችን ወደ አውሮፓ ወስዶ ስለነበር እና የመጽሐፉ አንዳንድ ብጥስጣሽ ብራና ቅጂዎች/ሙት ባሕር ብራናዎች (Dead Sea Scrolls) በአረማይክ ቋንቋ በ1950ዎቹ በመገኘታቸው ምክንያት መፅሐፈ ሄኖክ በአሁኑ ወቅት በመላው አለም በሚገኙ አብዛኛው ቋንቋዎች ተተርጉሞ ለትምህርትና ለምርምር ስራ እየዋለ ይገኛል። በአማርኛ ቋንቋም በብዛት እየታተመና እየተሰራጨ ይገኛል።
በሀገራችን ባሉ ገዳማትም እንደ ማንኛውም የግእዝ ቋንቋ መፃሕፍት ከጥንት ጀምሮ በብዛት እየተባዛና እየተሰራጨ ቆይቷል። ይሁንና በየገዳማቱ የሚገኙ የግእዝ ቋንቋ መፃሕፍት ብዙ ጊዜ የተፃፉበትን ዘመንና ፀሃፊውን ስለማይጠቅሱ (አንዳንዴም የገለበጡት መፅሐፍ ላይ ስም መፃፍ ትህትናን ስለማያሳይ) ትክክለኛ ዕድሜያቸውንና ፀሀፊውን ለማወቅ አዳጋች እንደሆነ የሚታወቅ ነው።
ይሁንና ፕሮፌሰር ጌታቸው እንደሚሉት፤ የየዘመናቱ የቁም ፅሁፍ አይነቶች ስለሚገመቱና ወይም ጸሀፊው በፅሁፉ መሃል በዘመኑ የነበረውን ንጉስ ወይም ጳጳስ ጠቅሶ እንደሆነ እሱን በመፈለግ ዘመኑን ለመገመት ይቻላል።
ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ምንም እንኳን መፅሐፈ ሄኖክ አከራካሪ ቢሆንም በአጠቃላይ ለሰው ልጆች የሀይማኖት ጥናት የሚሆኑ በርካታ ጠቃሚ መልእክቶችና ታሪኮች ያሉት እንደሆነ ምሁራን ይስማማሉ።
ከመጽሐፉ ቀደምት ቅጂዎች አንዱ ከሆነውና በፈረንሳይ ብሄራዊ ሙዚዬም ከሚገኘው የአንቷን ዳባዲ (Antoine d’Abbadie) ቅጂ መረዳት እንደሚቻለው፤ አንዳንዴ የምጽአት ቀን መፅሐፍ (apocalyptic) በመባል የሚታወቀው መፅሐፈ ሔኖክ አምስት ዋና ዋና ክፍሎች አሉት።
በነገራችን ላይ አንቷን ዳባዲ (Antoine d’Abbadie)፣ እ.ኤ.አ ከ1830ዎቹ እስከ 1870ዎቹ ድረስ 234 ያህል የግእዝና ያማርኛ መፃህፍት ላይ ጥናትና ምርምር ያደረገ እንዲሁም መዝገበ ቃላትን ያሳተመና ቋንቋዎቿን (ግእዝንና አማርኛን) አቀላጥፎ የሚናገር ከመሆኑ አንጻር የዘርዓያቆብን “ሐተታ ዘርዓያቆብ” መጽሐፍ ፅፎ ሊሆን ይችላል እያሉ አንዳንድ የውጭ ፀሃፊዎች እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ “ሐተታ ዘርዓያቆብ; ያለ ጥልቀ መልእክት ያለው ፍልስፍና በዚያ ዘመን መፃፍ እንደማንችል በመግለጽ፣ የሀገራችንን ክብር ለመንካት ከሚሞክሩበት ሁኔታ ጋርም ይያያዛል።
የመፅሐፈ ሔኖክ አምስቱ ዋና ዋና ክፍሎቸም የሚከተሉት ናቸው፡-
መጽሐፈ ትጉኃን (The Book of the Watchers, 1 Enoch 1–36)
መጽሐፈ ምሳሌ (The Book of Parables of Enoch, 1 Enoch 37–71)
የሰማይ ብርሃናት መመለስን የተመለከተ (The Astronomical Book, 1 Enoch 72–82) (also called the Book of the Heavenly Luminaries or Book of Luminaries)
የሔኖክን ህልሞች የተመለከተ ክፍል (The Book of Dream Visions , 1 Enoch 83–90) (also called the Book of Dreams)
ሔኖክ መልእክት (The Epistle of Enoch , 1 Enoch 91–108)
ትንሹ ዘፍጥረት (The Little Genesis) በመባል በሚታወቀው መፅሐፈ ሄኖክ የመጀመሪያው ክፍሉ በሆነው መጽሐፈ ትጉኃን ራዕዮችን ይዘረዝራል። በወቅቱ የነበሩ ሰዎች በአመጻቸው ጽናት ከቃየል ልጆች ጋራ አብረው እንዲዋሀዱ ከደብረ ቅዱስ በወረዱበት ጊዜ ሄኖክ ገሠጻቸው ይላል። የከለሱት ልጆቻቸውም በቁመት አብልጠው ረጃጅሞች እንደተባሉ፣ እነዚህም አባቶቻቸውንና ምድሪቱን እንደ በደሉ ይናገራል።
በዘፍጥረት የተገለፀውን የግዙፎቹን ሰዎች (የኔፍሊኖችን) እና ከነሱ ጋር ስለተወዳጁት ሴቶችና ሌሎችንም ታሪኮች ይተርካል።
ይህንንም “በእማንቱ መዋእልተ ወልዳ ሎሙ አዋልድ ሠናይት ወላሕያት። ወርእዩ ኪያሆን መላእክት ዉሉድ ሰማያት ወፈተዉዎን ወይቤሉ በበይናቲሆሙ ንዑ ንኀረይ ለነ አንስተ እምዉሉደ ሰብእ ወንለድ ለነ ዉሉደ።” ሲል በግእዙ ፅፎታል።
“በእነዚህ ወራት መልከ መልካሞችና ደመ-ግቡዎች ሴቶች ልጆች ተወለዱላቸው። የሰማይ ልጆች መላእክትም እነርሱን አይተው ወደዷቸው።” እንደማለት ሲሆን መላእክቱም ከሴቶቹ ልጆችም እንውለድ ብለው ወለዱ፤ ልጆቻቸውም ከሰው ቅርፅ የተለዩ በጣም ግዙፎች ሆኑ፣ አምላክ እስከሚያጠፋቸውም ድረስ ብዙ ጥፋትና ሀጥያትም አደረሱ።
መፅሐፉ በሌሎቹ ክፍሎችም ስለ ተለያዩ ምሳሌዎች፣ ስለ ሰማይ ብርሃናት መመለስ፣ ስለ ሔኖክ ህልሞችና መልእክቶች ጥልቀት ባለው ፍልስፍና ስለሚያቀርብ ለተለያዩ ጥናትና ምርምሮች እንዲሁም ታሪክን ለመቀመር ጠቃሚ መሆኑ ይታመንበታል።

Read 4450 times