Print this page
Tuesday, 26 January 2021 00:00

የውቅሮ እና ዕዳጋ ሐሙስ የወፍ በረር ቅኝት

Written by  በተስፋለም ወልደየስ
Rate this item
(3 votes)


               ድንገት ከእንቅልፌ ባነንኩ። ተከታታይ የከባድ መሳሪያ ተኩስ የሰማሁ መስሎኛል። “በህልሜ ነው በእውኔ?” የሚል ጥያቄ ለራሴ አቅርቤ ሳልጨርስ ተከታታዩ ተኩስ ተደገመ። ከአልጋዬ ተፈናጥሬ ወረድኩና ወደ ሆቴሌ በረንዳ በረርኩ። በጨለማ ውስጥ የሚፈነዳ ነገር ይታይ እንደሁ በሚል ዙሪያ ገባውን ቃኘሁ። ምንም ነገር የለም። ሰዓቱን ተመለከትኩ – አስራ አንድ ሰዓት ተኩል ገደማ ሆኗል። ደቂቃዎች እንኳ ሳይቆይ ተኩሱ ቆመ። ወደ አልጋዬ ተመለስኩ።
ከግማሽ ሰዓት በኋላ ለጉዞ መዘገጃጀት ጀመርኩ። ከመቐለ 47 ኪሎ ሜትር ገደማ የምትርቀውን ውቅሮ ከተማን ለመመልከት አቅጄያለሁ። ዕለቱ ማክሰኞ፤ ቀኑ ደግሞ ታህሳስ 20፤ 2013 ዓ.ም. ነው። በዚያው ልደር፤ አሊያም ተመልሼ ልምጣ የሚወስነው በአካባቢው ያለው ሁኔታ ነው። በውቅሮ የስልክ አገልግሎት ስለሌለ ስለ ከተማይቱ መሰረታዊ መረጃዎችን እንኳ ለመቃረም ዕድል አላገኘሁም።
ስለ ከተማይቱ በተባራሪ የሚሰሙ ወሬዎች እርስ በእርስ የሚጣረሱ ናቸው። አንዳንዶች ከተማይቱ በከፍተኛ ሁኔታ ውድመት ደርሶባታል ይላሉ። ሌሎች ከፍተኛ ዘረፋ እንደተፈጸመባት ይናገራሉ። ጥቂቶች አሁንም በአካባቢው ሰላም እንደሌለና በአቅራቢያዋ ባሉ ቦታዎች ውጊያ እየተካሄደ እንደሆነ ያስጠነቅቃሉ። በዚያም አለ በዚህ፤ ርቃ ከምትገኘው አዲግራት ይልቅ፤ “ለክፉም ለደጉም መቐለ አቅራቢያ የምትገኘው ውቅሮ ትሻለኛለች” በሚል ነበር ወደዚያ ለመሄድ የወሰንኩት። ከአዲስ አበባ ወደ ቢሾፍቱ እንደ መሄድ በሉት።  
ከመቐለ ወደ ውቅሮ በህዝብ ትራንስፖርት ለመጓዝ ቀደም ሲል ይከፈል የነበረው ከ20 እስከ 30 ብር ነበር። ከውጊያው በኋላ ግን ዋጋው በአስር እጥፍ ጨምሮ እስከ 200 እና 250 ብር ደርሷል። የመጀመሪያዎቹ ቀናት ሰሞን 500 ብር ሁሉ ከፍለው የሚጓዙ ነበሩ። የአዲግራትም የትራንስፖርት ዋጋ እንዲሁ በተመሳሳይ ሁኔታ በከፍተኛ ሁኔታ አሻቅቧል። በደህናው ጊዜ 50 ብር ገደማ ይከፈልበት የነበረው ከመቐለ- አዲግራት ያለው መንገድ፤ “ውጊያው አልቋል” ተብሎ መንገዱ ለተጓዦች ክፍት ሲደረግ እስከ አንድ ሺህ ብር አሻቅቦ ነበር። ከሳምንት በኋላ ዋጋው ወደ 700 ብር ወርዷል። እኔ በተጓዝኩበት ቀን የነበረው የአዲግራት የህዝብ ትራንስፖርት ዋጋ 500 ብር ገደማ ነበር።    
መናኸሪያ ስደርስ ወደ ውቅሮ የሚጓዙ ሚኒባሶች እዚያ እንደሌሉ፤ የሚገኙት ሌላ ቦታ እንደሆነ ሰማሁ። የሚኒባሶቹ መገኛ የመሰለኝ እዚያው መናኸሪያ አካባቢ ስለነበር ከከተማው እየራቅን ስንሄድ ግር አለኝ። የጫነችኝ ባጃጅ በከተማ መውጪያ አካባቢ ያለውን የመስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ ፋብሪካ ስታልፍ፤ ወዴት እየሄድን እንድሆነ ጠየቅኩ። እየደረስን መሆናችንን ሹፌሩ ነገረኝ። ብዙም ሳንጓዝ በተለምዶ “ኮብራ” ተብሎ የሚጠራው ቶዮታ መኪና አጠገብ ቆምን።
ሁለት ደላላ መሳይ ወጣቶች የት መሄድ እንደምንፈልግ እና ስንት እንደሆንን በመሳሰሉ ጥያቄዎች ያዋክቡን ያዙ። የባጃጁ ሹፌር ለ“ኮብራው” አሽከርካሪ በትግርኛ ጥያቄ ሲያቀርብ፤ እነርሱም ተደርበው ምላሽ ይሰጣሉ። በማጣሪያ ጥያቄዎቹ በቂ ምላሽ ያገኘ የመሰለው አስጎብኚዬ ወደʼኔ ዞሮ፤ መኪናው ሰንቃጣ ድረስ እንደሚጓዝ ገለጸልኝ። “ፍሬወይኒ” በሚለው በሌላኛው ስያሜዋ የምትጠራው ሰንቃጣ ከተማ፤ በውቅሮ እና በአዲግራት መሃል ያለች ነች። ከተማይቱን ቀደም ሲል ወደዚያ አካባቢ ባደረግኳቸው ጉዞዎቼ ደጋግሜ አልፌባታለሁ።
የጉዞ መዳረሻዬ ውቅሮ ከተማ መሆኑን እየተናገርኩ በመኪናው ጋቢና ተደላድዬ ተቀመጥኩ። ወሬ ለመመልከት ሁነኛ ቦታ በማግኘቴ እና መኪናውም ለክፍለ ሃገር ጉዞ ተመራጭ የሆነው የቶዮታ “ፎር ዊል ድራይቭ” መሆኑ አስደስቶኛል። ከመኪናው የኋላ ወንበር አንዲት ተጓዥ ተቀምጣለች። ከከተማ ውጭ ባለ በዚህ ቦታ ላይ፤ ሌሎች ተጓዦችን ለማግኘት ያለውን አስቸጋሪነት እያሰብኩ፤ “በቃ እዚሁ ጊዜውን መፍጀታችን” ነው አልኩ ለራሴ። በጠዋት ብንወጣ፣ ውቅሮን በውሎ ገብ ለመጎብኘት ያስችለኛል በሚል ነበር ለሰዓቱ መሰሰቴ።
ያመጣኝን የባጃጅ ሹፌር ተሰናብቼ እንኳ ሳልጨርስ፤ መኪናው ከአንድም ሁለት ተጓዥ አገኘ። አንደኛው ተጓዥ አካል ጉዳተኛ ስለሆኑ፤ ቀድሜ የያዝኩትን የጋቢና ቦታ ለእርሳቸው ለቅቄ ወደ ኋላ ወንበር መዛወሬ ግድ ሆነ። ሁለተኛው ተጓዥ የእርሳቸው ረዳት በመሆኑ አብሯቸው ተቀመጠ። ጋቢናው ሞላ። ከኋላ ወንበር ግን ያለነው ሁለት ብቻ በመሆናችን፤ መኪናው ገና ሁለት ሰው ይፈልጋል።
አጠገቤ የተቀመጠችውን ተጓዥ ወዴት እንደምትሄድ ጠየቅኋት። ወደ አዲግራት ቤተሰብ ለመጠየቅ እየሄደች እንደሆነ እና በዚሁ መኪና ዛሬውኑ ወደ መቐለ እንደምትመለስ ነገረችኝ። ከሹፌሩ ጋር ቤተሰብ እንደሆኑ እና በእርግጠኝነት ይዟት እንደሚመለስ ማስተማመኛ ስትሰጠኝ ውቅሮ ድረስ ለመጓዝ የነበረውን ሀሳቤን ቀይሬ አዲግራት ደርሼ ለመመለስ እዚያውኑ ወሰንኩ።
ብዙም ሳይቆይ፤ ቅድም ሲያዋክቡን ከነበሩ “ደላላ” ወጣቶች አንዱ፤ የመኪናውን የበስተኋላ በር ከፍቶ አጠገባችን ተቀመጠ። ወጣቱ “ለሆነ ሰው ቦታ ይዞ መሆን አለበት” ስል ገመትኩ። መኪናው ወደ ፊት ከመንዳት ይልቅ ወደ ኋላ አዙሮ፤ ወደመጣንበት የከተማ አቅጣጫ ሲመለስ፤ በእርግጥም ቦታ የተያዘላቸውን ሰው ከቤታቸው ልንጭን እየሄድን እንደሆንን አረጋገጥኩ።
“ኮብራው” ቀበሌ 16 የሚባለው ሰፈር ሲደርስ ቆመ። ሹፌሩ እና ደላላ መሳዩ ወጣት፤ ከጎናችን ካለው የሴቶች ጸጉር ቤት ላይ አይናቸውን ተከሉ። የሚጠበቁት ተጓዥ “ከአሁን አሁን ይመጣሉ” ተብለው ለደቂቃዎች ቢጠበቁም ድምጻቸው ጠፋ። ተጓዦች ትዕግስታችን አልቆ ማጉረምረም ጀመርን። ወጣቱ ጉዳዩን እንዲያጣራ ተላከ። ከደቂቃዎች በኋላ ተጓዡ ብቅ አሉ። እንደጠበቅኩት ትልቅ ሰው ሳይሆኑ፤ ወጣት ሴት ናት። መቆየቷ ምንም ግድ ያልሰጣት ይህች ሴት ወጣቱን ደላላ ተከትላ ወደ መኪናው ገባች። መኪናው፤ አራታችንንም በስተኋላ መቀመጫ አጣብቦ፤ ወደ ከተማይቱ መውጫ አቀና።
እኛን መጀመሪያ የጫነበት ቦታ ላይ ሲደርስ፤ ጠዋት ላይ በአካባቢው ስለነበረው የከባድ መሳሪያ ተኩስ ጉዳይ ተነሳ። ተኩሱ ቦታው ላይ ከመድረሴ ከአስር ደቂቃ ገደማ በፊት እንደነበር እና ብዙም ሳይቆይ መቆሙ ተወራ። ለሊት ላይ ከነበረው ተመሳሳይ ተኩስ ጋር ተዳምሮ አካባቢው ሰላም መሆኑ ያጠያይቅ ጀመር። ጉዟችንም ስጋት ያዳመነበት ሆነ። ሆኖም ማናችንም፤ ይህን ሰምተን የጉዞ ዕቅዳችንን አልሰረዘንም።
አጠገቤ የተቀመጠው ደላላ መሳዩ ወጣት፤ በዚህ መንገድ ከሰሞኑ በየቀኑ እንደሚመላለሱና እስካሁንም ምንም አይነት ችግር እንዳላጋጠማቸው በመንገር ሊያረጋጋን ሞከረ። መንገዱን ካወቀው ዘንድ በሚል፤ “በየመንገዱ በጣም ብዙ ፍተሻ አለ አይደል?” ስል ጠየቅኩ – መቐለ የሰማሁትን ወሬ ተተንርሼ። “አንድ ፍተሻ ብቻ ነው ያለው። እሱን ካለፍን ችግር የለም” አለኝ ወጣቱ በተዝናና መንፈስ። አላመንኩትም። “የህወሓት ተፈላጊ ሰዎችን እያደንን ነው” በሚባልበት እና አሁንም ውጊያ መኖሩ በሚነገርበት አቅጣጫ እየተጓዝን፤ 137 ኪሎ ሜትር ሙሉ እንዴት አንድ የፍተሻ ጣቢያ ብቻ ይኖራል?
በደቂቃዎች ውስጥ፤ መቐለ መውጪያው ላይ መሰቦ የሚባለው አካባቢ ባለው ዋናው ፍተሻ ጣቢያ ደረስን። በሌሎች መኪናዎች እንዳሉ ተጓዦች ሁሉ እንድንወርድ ተነገረን። ሁሉም መታወቂያውን እየያዘ ወረደ። ተራችን እስኪደርስ የሌሎቹን ፍተሻ እያየን ቆየን። ፍተሻውን የሚያከናውኑት ወታደሮች ናቸው።
ለእኛ የደረሰን ፈታሽ በማመናጨቅ ስሜት ነው ጥያቄዎችን የሚጠይቀው። ሌሎቻችንን በዚያው ስሜት ፈትሾ ሲያበቃ፤ ያስረፈደችን ወጣት ሴት ላይ ሲደርስ ነገሮች ከረሩ። ወጣቷ በመታወቂያ ምትክ በእጇ የያዘችው የአንበሳ ባንክ የሂሳብ ደብተር ነው። የባንክ ደብተሩ ስሟን፣ ፎቶዋን እና በዛ ያለ የገንዘብ ዝውውሯን መረጃ ይዟል።
“ይሄ ምንድነው?” አላት ወታደሩ በቁጣ።
“የባንክ ቡክ” ስትል መለሰች ወጣቷ።
“የባንክ ቡክ መታወቂያ መሆን ይችላል?” በድጋሚ በቁጣ ጠየቃት።
“መታወቂያዬ ጠፍቶብኝ ነው” አለች በሚለማመጥ ቅላጼ። ወታደሩ የወጣቷ መልስ አላሳመነውም።
“ስልክሽን አምጪ” አላት በእጇ የያዘችውን የተጎሳቆለ “ስማርት ፎን” እያመለከተ። ሰጠችው። ወታደሩ ስልኩን ከፍቶ ለመመልከት ሞከረ እና ግራ የተጋባ መሰለ።  
“ፎቶዎቹን አሳይኝ” ሲል ወጣቷን አዘዛት። ወጣቷ የተባለችውን አደረገች። ሌሎችን ሲፈትሽ የነበረው ወታደር መጣና ጉዳዩ ምን እንደሆነ ጠየቀ። ይሄኛው ወታደር ትህትና የተላበሰ ነው። የእኛ ፈታሽ ስለ ጉዳዩ ነገረው። አብረው ስልኩን ሲመለከቱ ቆዩ። ‘በስልኩ ላይ ያለው የፎቶ ቁጥር እንዴት አነስተኛ ሊሆን ቻለ?’ በሚል የእኛ ፈታሽ ከወጣቷ ጋር ሲነታረክ ቆየ።  
የወጣቷ የአማርኛ ቅላጼ በጣሙኑ የትግርኛ ቋንቋ የተጫነው ነው። አንዳንድ ሀሳቦቿን በቅጡ በአማርኛ ለመግለጽ ትቸገራለች። ወታደሩ ይህንን ሁኔታዋን እንደማጭበርበር ወስዶታል። ድንገት፤ “አንቺማ የልዩ ኃይል ወታደር ነሽ” ሲል ሰማነው። ይህ አባባሉ የመቐለው አስጎብኚዬ ወጣት የነገረኝን አስታወሰኝ። “በከተማው የሚዘዋወሩ ወታደሮች እኔን የመሰሉ ወጣቶችን በተመለከቱ ቁጥር የልዩ ኃይል አባላት እንመስላቸዋለን” ብሎኝ ነበር። “አንድ ወታደር እንዲያውም የልዩ ኃይል አባላት የት እንደሚገኙ እንድነግረው ጠይቆኛል” ሲልም በገረሜታ አጫውቶኝ ነበር።
ወታደሮች፤ የትግራይ ልዩ ኃይል አባል የሆኑ ወጣቶችን ለይተው ለማውጣት ከሚጠቀሙባቸው መንገዶች መካከል፤ ትከሻ ገልጦ መመልከት እንደሚገኝበት ከተለያዩ ሰዎች ሰምቻለሁ። ነገሩ ግር ቢለኝ “ለምን ትከሻ?” በማለት መጀመሪያ ነገሩን የሰማሁ ጊዜ ጠይቄ ነበር። “የልዩ ኃይል አባላት መሳሪያ የሚያነግቱት እና ሌሎች ተተኳሾች የሚሸከሙት በትከሻቸው ስለሆነ፤ በዚያ አካባቢ ምልክት አይጠፋም በሚል ነው ወታደሮቹ ልብስ ገልጠው የሚመለከቱት ” የሚል ምላሽ ተሰጥቶኛል።
ይህ ገለጻ፤ በአዲስ አበባ የ1997ቱን ምርጫ ተከትሎ በከተማይቱ በተቀሰቀሱ ተቃውሞዎች የተሳተፉ ወጣቶችን ለመለየት በሚል የፌደራል ፖሊሶች ያደርጉት የነበረውን ነገር ወደ አእምሮዬ አመጣው። በወቅቱ ተቃውሞ በሚካሄድባቸው ቦታዎች በብዛት የተሰማሩት ፖሊሶች፤  ያገኙትን ወጣት ሁሉ እያስቆሙ “እጅህን አሳይ” እያሉ ይመለከታሉ። እጆቹ በአቧራ የተሸፈኑ አሊያም የቆሸሹ፤ ከድንጋይ ወርዋሪዎቹ ተቃዋሚ ወጣቶች አንዱ ነው በሚል ይያዝ ነበር።
የመቐለ ሰዎች፤ ወታደሮቹ የትግራይ ልዩ ሃይል አባላትን ለመለየት የሚጠቀሙበትን ሌላም ዘዴ ነግረውኛል። ይሄኛው ደግሞ ወደ ቁርጭምጭሚት አካባቢ ያለውን የእግር ክፍል ገልጦ ማሳየት ያስገድዳል። የልዩ ኃይል አባላቱ ያደርጉት የነበረው ወታደራዊ ጫማ፤ በዚህኛው የሰውነት ክፍል አካባቢ የሚተወውን ምልክት እንደ አንድ ማረጋገጫ እንደሚወሰድ ሰምቼያለሁ። በደቂቃዎች ውስጥ በልዩ ኃይል አባልነት ወደተጠረጠረችው፤ አብራን ወደምትጓዘው ወጣት ትኩረቴን አደረግኩ።  
የነገሩ መክረር ያሳሰባቸው ሹፌሩ እና ደላላ መሳዩ ወጣት ነገሩን ለማለዘብ ጣልቃ ገቡ። ወጣቷን እንደሚያውቋት እና የጸጉር ስራ ባለሙያ እንደሆነች ነገሩት። በዚህም ምላሽ ፈታሻችን አልረካም። ወጣቷን ተጨማሪ ጥያቄዎች ጠየቃት። እምብዛም ሳትደናገጥ አጠር አጠር ያለ ምላሾች ሰጠችው። በስተመጨረሻ ፈታሻችን፤ ከትሁቱ ወታደር ጋር ተነጋግሮ እንድንሄድ ፈቀደልን። ሁሉም ተጓዥ እፎይ አለ። በስተኋላ ላይ ስሰማ ወጣቷ የጸጉር ስራ ባለሙያ ብቻ ሳትሆን፤ ጠዋት የተመለከተነው ተለቅ ያለ ጸጉር ቤት ባለቤት ጭምር ናት።  
ወደ መኪናችን ተመልሰን ጉዞ እንደጀመርን ተለቅ ያለችውና አጠገቤ የተቀመጠችው ሴት፤ ወዲያውኑ ስልኳን አውጥታ ፎቶዎችን ማጥፋት ጀመረች። ለምን እንደዚያ እንደምታደርግ ጠየቅኋት። “ስልክሽን አምጪ ስትባል እናንተ እኮ ምንም አልመሰላችሁም። እኔ እየተንቀጠቀጥኩ ነበር” አለች፤ ለሁላችንም በሚሰማ ድምጽ። አሁንም ስላልገባኝ ነገሩን አንድታብራራልኝ ጠየቅኋት። “እንዴ! ስልኬ ላይ ያለው የደብረጽዮን፣ የመለስ ፎቶ ቢያዩ አይለቁኝም” አለች። ይሄ አባባሏ ከዓመታት በፊት “በስልካቸው ላይ የኦነግ ባንዲራ ተገኝቶባቸዋል” ተብሎ በፍርድ ቤት በክስ ማስረጃነት የቀረበባቸውን ሰዎች አስታወሰኝ።
* * *
ስጋት የተጫነው ጉዟችንን በዝምታ ተያይዘነዋል። ዝምታው ግን እምብዛም አልዘለቀም። በትግራይ የነበረውን የውጊያ መጠን የሚያሳዩ ቅሪቶችን መመልከት ስንጀመር በማብራሪያዎች የታጀበ የተጓዦች ውይይት ተከፈተ። በውጊያው ጉዳት የደረሰበት እና መንገድ ዳር የቆመ የመጀመሪያውን ታንክ ያየነው ከመቐለ 25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ካለቸው አጉላዕ ከተሰኘችው አነስተኛ ከተማ እንኳ ሳንደርስ ነው። ደቂቃ ሳይቆይ ሌላ ታንክ ተደገመ።
አጉላዕን አለፍ እንዳለን ደግሞ በአንድ ቦታ ላይ የተቃጠሉ እና ወደ ጎናቸው የተገለበጡ አራት ወታደራዊ እና የጭነት ተሽከርካሪዎችን ከዕይታችን ገቡ። አጠገቤ ያለችው ሴት ድንጋጤዋን “ዋይ” በሚሉ ቃላት እያጀበች ትገልጻለች። ትንሽ ፈቀቅ እንዳለን በቃጠሎ ሙሉ ለሙሉ የወደሙ ሁለት አውቶብሶችን አየን። በሁለቱ መጓጓዣዎች ላይ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ የቀደመ ቀለማችውን እና ስሪታቸውን እንኳን ለመለየት ያዳግታል። አጠገብ ለአጠገብ ካሉት ከእነዚሁ አውቶብሶች አቅራቢያ የተቃጠሉ እና የተገለበጡ ሶስት ተሽከርካሪዎች አሉ።
ውቅሮ መግባታችንን የሚያመለክተው በብረት የተሰራ የከተማይቱ በር ጋር ከመድረሳችን በፊት ባሉት ሶስት ደቂቃዎች ውስጥ እንደዚሁ ጉዳት የደረሰባቸው ሌሎች መኪናዎች ተመልክተናል። ጣሪያው የተሰረጎደ ፒክ አፕ፣ በእሳት የነደዱ እና በግራ እና በቀኝ የተፈነገሉ አራት ወታደራዊ የጭነት መኪናዎች፣ “አንደኛ ደረጃ” የሚል መለያ ከፊቱ የለጠፈ፥ መስታወቶቹ የረገፉ፥ አረንጓዴ እና ነጭ ቅብ ሜርሴዲስ ቤንዝ የህዝብ መጓጓዣ አውቶብስ፣ “ኦራል” በሚል መጠሪያቸው የሚታወቁ የተገለበጡ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች፤ በመንገድ ዳር ቆመው ለመጪ ሂያጁ ውጊያው ምን ይመስል እንደነበር ይመሰክራሉ።
በመንገዳችን ላይ የመከላከያ ሰራዊት እና የፌደራል ፖሊስ አባላትን የጫኑ ቢያንስ ስድስት ተሽከርካሪዎች ተመልክቻለሁ። በፒክ አፖች ላይ ያሉቱ፤ በተሽከርካሪው ጣሪያ ላይ የተደገነ መትረየሳቸውን ቃታ የያዙ ወታደሮች እና ፖሊሶችን ከፊት አሰልፈዋል። ሌሎቹ ወታደሮች እና ፖሊሶችም መሳሪያዎቻቸውን በተጠንቀቅ ይዘው ዙሪያቸውን እየቃኙ ነበር የሚጓዙት። አንዳንዶቹ ፊታቸውን ከንፋሱም ሆነ ከአቧራው ለመከለከል በሚመስል ሁኔታ ተሸፋፍነዋል።
ወደ ውቅሮ ስንገባ ከጠዋቱ አራት ሰዓት ሆኗል። ጥቂት በተለምዶ ባጃጅ ተብለው የሚጠሩ ባለሶስት እግር ተሽከርካሪዎች ከተማይቱን አቋርጧት በሚያልፈው አውራ ጎዳና ውር ውር ይላሉ። ከጠበቅኩት ከፍ ያለ የሰው እንቅስቃሴ ይታያል። ደላላ መስሎኝ የነበረው እና በጨዋታችን መሃል የጋራዥ ሰራተኛ መሆኑን የነገረኝ ወጣት፤ በከተማው ስለተገደሉ ወጣቶች፣ በህንጻዎች እና የንግድ መደብሮች ላይ በጥይት እና በከባድ መሳሪያ ስለደረሰው ጉዳት ማብራሪያ መስጠት ጀመረ። በከተማይቱ ጎልቶ የሚታየውን ባለ አራት ፎቅ ህንጻ  እንድመለከት በጣቱ ጠቆመኝ።
በማህበር መሰራቱ የተነገረኝ፣ “ዕዳጋ ማእከል” የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ህንጻ በተንጣለለ ስፍራ ላይ የተገነባ ነው። ወደ ጎን ረዥም ነው። ለሚመለከተው ስድስት አነስተኛ ህንጻዎች ተቀጣጥለው የተሰሩ የሚመስል ስሜት ይሰጣል። ስድስቱም የህንጻው ክፍሎች በአብረቅራቂ መስታወት ተሸፍነዋል። ወጣቱ ተመልከት የሚለኝም በጥይት የተበሳሱትን እና መሃል ላይ በርካታ ቀዳዳዎችን ያበጁትን መስታወቶቹን ነው። ስድስቱም የህንጻው ክፍሎች በዚህ መልኩ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ወጣቱ ሹፌራችን መኪናዋን ከህንጻው ብዙም ሳይርቅ አቆማት። ይሄኔ ውቅሮ የምትታወቅበትን የሽምብራ እና የገብስ ቆሎ የያዙ ወጣቶች ወደ እኛ ተጠጉ። ለራሱም፣ ለቤተሰቡም መግዛት የፈለገ ሁሉ በኪሎ ያሰፍር ገባ። ቆሎ ለመግዛት በቆምንበት ደቂቃዎች ውስጥም ሆነ ውቅሮን ተሰናበትን እስክንወጣ ድረስ በተቀመጥኩበት ሆኜ ዙሪያ ገባውን በተቻለኝ መጠን ለመቃኘት ሞክሬያለሁ።
ከመንገዳችን ግራ እና ቀኝ በተደረደሩ ህንጻዎች፣ የንግድ መደብሮች፣ ባንኮች እና ሌሎች በርካታ አገልግሎት መስጪያዎች መጎዳታቸውን ተመልክቻለሁ። ከሚታዩት ውስጥ የብዙዎቹ ህንጻዎች ተሰባብረዋል። በጥይት የተበሳሱም በርካቶች ናቸው። አንዳንዶቹ ዘረፋ እንደተካሄደባቸው በአቅራቢያቸው ከተዝረከረኩ ቁሳቁሶች መረዳት ይቻላል። ከአንድ የጫማ መሸጪያ ሱቅ ፊት ጫማዎች የሚቀመጡባቸው በርካታ ባዶ ካርቶኖች በየቦታው ተበታትነው አይቻለሁ። በርካታ ሞባይል መሸጪያ ሱቆች የዘረፋው ሰለባ መሆናቸውን በወፍ በረሩ ምልከታዬ ታዝቤያለሁ።      
አብረውኝ የሚጓዙት ሰዎች በህዝብ ንብረት ላይ በዚህ መልኩ ጉዳት በመድረሱ አዝነዋል። በውቅሮ ለተገደሉ ሰዎች እና ለደረሰው አብዛኛው ጉዳት ተጠያቂዎቹ የኤርትራ ወታደሮች መሆናቸውንም ይነጋገራሉ። ወደ ከተማይቱ መውጫ ስንቃረብ ሁለት ነጭ መጋዘን መሰል ነገሮች እና አንድ መለስተኛ ህንጻ ከርቀት ተመለከትኩ። ዙሪያውን በታጠረ ግቢ ውስጥ የሚገኙት መጋዘኖች የሰማይታ እምነበረድ ፋብሪካ ማምረቻዎች መሆናቸውን ወደ ቦታው ስንጠጋ ተረዳሁ።
በትግራይ ክልል በነበረው ውጊያ፤ ከፍ ያለ ውድመት እና ዘረፋ ከደረሰባቸው ፋብሪካዎች መካከል አንዱ የሆነው ሰማያታ አራት ሄክታር በሚጠጋ የተንጣለለ መሬት ላይ የተገነባ ነው። የዛሬ አምስት ዓመት ገደማ ማምረት የጀመረው ፋብሪካው 400 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገበት በወቅቱ ተነግሮ ነበር። ፋብሪካው አጠገብ ስንደርስ ከሁሉ አስቀድሞ አይኔ የገባው፤ በቅጥር ግቢው መግቢያ በስተግራ ካለው ባለ ሶስት ፎቅ ህንጻ ፊት የቆመች ፒክ አፕ መኪና ነች። መኪናዋ አራቱንም ጎማዎቿን አጥታ ተሰናክላ ቆማለች። ባለ ሁለት ጋቢና የሆነችው የዚህችው መኪና አራት በሮችም ተገንጥለው መለመላዋን ቀርታለች። የዕቃ መጫኛ ክፍሏ የኋላ መከለያም በቦታው የለም።
በአብረቅራቂ መስታወት ወደተሸፈነው የፋብሪካው ህንጻ አማተርኩ። በስተቀኝ ጎኑ ባለው መስታወት ላይ ከሚታየው ሽንቁር ባሻገር የከፋ ጉዳት የደረሰበት አይመስልም። ፋብሪካው ላይ በከባድ መሳሪያ የደረሰ ውድመት ይኖር እንደሁ በሚል፤ ካለፍነውም በኋላ ዞሬ አተኩሬ መረመርኩት። ወደዚህ ከመምጣቴ በፊት፤ በትግራይ ያሉ ፋብሪካዎች በከባድ መሳሪያ መመታታቸውን የሚያሳዩ ምስሎች በማህበራዊ ድረ ገጾች ላይ ሲዘዋወሩ በመመልከቴ ሰማያታም ያ ዕጣ ፈንታ ገጥሞት እንደሁ ማረጋገጥ ነበረብኝ። ከርቀት እንደተመለከትኩት ከሆነ ነጭ ቀለም የተቀቡት ሁለቱ የማምረቻ መጋዘኖች ላይ ጉልህ የሆነ ውድመት አይታይም።
አብረውኝ የሚጓዙት ሰዎች ስለ ፋብሪካው እየተወያዩ ነው። ሹፌሩ እና የጋራዥ ሰራተኛው፤ ፋብሪካው በኤርትራውያን ወታደሮች እንደተዘረፈ መስማታቸውን ነገሩን። በመቐለ ካነጋገርኳቸው ሰዎች ውስጥ አንድ ሁለቱ፤ ኤርትራውያን ወታደሮች የዚህን ፋብሪካ ማሽን ነቅሎ ለመውሰድ ቀናቶች እንደወሰዱባቸው አጫውተውኝ ነበር።
መኪናችን ጉዞዋን ቀጥላለች። ሹፌራችን በጨዋታችን መሃል በስተቀኝ ያለ ኮረብታን እንድናይ አመለከተን። በአረንጓዴ ቁጥቋጦዎች በተሸፈነው ዳገታማ ቦታ ላይ ወጣ ያለ ድንጋያማ ኮረብታ ይታያል። ኮረብታው ጫፍ ላይ፤ ግድግዳው አረንጓዴ እና ነጭ የተቀባ ቤተክርስቲያን ተቀምጧል። ሹፌራችን ቤተክርስቲያኑ የአማኑኤል እንደሆነ እና በካባድ መሳሪያ መመታቱን ነገረን። አጠገቤ የተቀመጠችው ሴት በድንጋጤ ክው ብላ “እዋይ….እዋይ” አለች። ቤተክርስቲያኑ ከዋናው መንገድ ርቆ የሚገኝ በመሆኑ፤ ጉዳቱ ምን ያህል እንደሆነ ግን በቅጡ መመልከት አልቻልኩም።  
ሹፌራችን በአል ነጃሺ መስጊድ ላይም ተመሳሳይ ጉዳት መድረሱን እያጫወተን፤ ዳገታማ እና ጠመዝማዛ በሆነው መንገድ ላይ በዝግታ ያሽከረክራል። ወደ አንደኛው መታጠፊያ ስንደርስ አስፋልት የነበረው መንገድ ተቀይሮ የተቆፋፈረ፤ በአፈር እና በድንጋይ የተሞላ ቦታ ገጠመን። የትግራይ ልዩ ኃይል አባላት፤ ወደ መቐለ እያመራ የነበረውን የመከላከያ ሰራዊት ጉዞ ለማስተጓጉል መንገዱን አፍርሰውት እንደነበርና በስተኋላ መጠገኑን ሹፌራችን ገለጸልን። ያገጠጠ አለት በአንድ ወገን እንደ ግድግዳ የቆመበትን፤ ይህን ቦታ ከተሻገርን ከደቂቃዎች በኋላ ወደ አነስተኛዋ ነጋሽ ከተማ ገባን። --
(ከ"ኢትዮጵያ ኢንሳይደር" ድረ ገጽ ባለ ሦስት ክፍል ዘገባ የተወሰደ)




Read 8452 times