Saturday, 30 January 2021 10:39

በሱዳን ወረራ ኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮች ከ226 ሚ.ብር በላይ ንብረት መዘረፋቸውን ተናገሩ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

  የዛሬ 2 ወር ገደማ የሱዳን ጦር በሃይል ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ገብቶ የመሬት ወረራ ሲፈፅም ከ226 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት፤ መዘረፋቸውን የአካባቢው ባለሃብት አርሶ አደሮች ለአዲስ አድማስ የገለፁ ሲሆን መንግስት አስቸኳይ ድጋፍ  አድርጎላቸው፣  ወደ ስራቸው መመለስ እንዲችሉ ጠይቀዋል፡፡
16 የሚደርሱ ባለሀብት አርሶ አደሮች በሱዳን ወታደሮች ወረራና ጥቃት እያንዳንዳቸው ከ2.5 ሚሊዮን እስከ 39 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት እንደተዘረፉ ተናግረዋል፡፡ ህዳር 26 ቀን 2013 ዓ.ም ከቀኑ ስምንት ሰዓት ተኩል ላይ ባልጠበቅነው ሁኔታ ነው ጥቃት  የተፈፀመብን የሚሉት ባለሃብት አርሶ አደሮቹ፤ ቋሚ ንብረታቸውን ጨምሮ በማሳ ላይ የነበረ የደረሱ የሰሊጥና የማሽላ ሰብልም መዘረፋቸውን ነው ለአዲስ አድማስ ያስረዱት፡፡
ትራክተሮች፣ የውሃ መሳቢያ ሞተሮች፣ ጄኔሬተሮች፣ ኮምባይነሮች፣ ማረሻ ማሽኖች፣ የውሃ ታንከሮች፣ የነዳጅ ቦቴ ተሽከርካሪዎችና የተለያዩ ማሽነሪዎች እንዲሁም በመቶዎች የሚቆጠሩ በጎችና ዶሮዎች፣ በወታደሮቹ መዘረፋቸውን ያስረዱት እኒህ አርሶ አደሮች፤ በማሳ ላይ የነበረ የደረሰ የሰሊጥና የማሽላ ሰብል በኮምፓይነር እየወቁ ሰብስበው መውሰዳቸውንም ተናግረዋል፡፡
ከኛም በፊት ወላጆቻችን በዚህ መሬት ላይ ያርሱ ነበር ያሉት አርሶ አደሮቹ ግብርናቸው ዘመናዊና ሜካናይዝድ እንደነበረ ነው የገለጹት።  ሁሉን ነገር ተነጥቀው በአሁኑ ወቅት ባዶ እጃቸውን እንደቀሩና ከፍተኛ የባንክ ብድር እዳም እንዳለባቸው የገለጹት፤ እኚሁ ባለሃብት አርሶ አደሮቹ፤ መ   መንግስት ድጋፍ  አድርጎላቸው ወደ ስራ መግባት እንዲችሉ  ጠይቀዋል፡፡


Read 756 times