Saturday, 30 January 2021 10:47

ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ለገባችው የድንበር ውዝግብ የሣኡዲ አረቢያን ሽምግልና ጠየቀች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

  በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል የተፈጠረውን የድንበር ውዝግብ ለመፍታት ሳኡዲ አረቢያ እንድትሸመግል ሱዳን የጠየቀች ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ፤የሱዳን ወታደር በሀይል የያዘውን አካባቢ ሳይለቅ ድርድር አይኖርም ብሏል፡፡
በሱዳን ሉአላዊ ም/ቤት አባል በሆኑት መሃመድ አልፋኪ ሱሊማን የተመራው የሱዳን ከፍተኛ የልኡካን ቡድን ከትናት በስቲያ ወደ ሳኡዲ አቅንቶ፣ ከኢትዮጵያ ጋር በተፈጠረው የድንበር ውዝግብ ዙሪያ ከሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር መምከሩን የሱዳኑ አል ጣሂር ጋዜጣ ዘግቧል፡፡
የሱዳን ልኡካን ቡድን በተለይም ከሳኡዲ የደህንነት ሃላፊዎች ጋር ባደረጉት ውይይት፣ ግጭቱን የኢትዮጵያ ሚሊሻዎች እንደጀመሩ መግለጻቸውን የዘገበው ጋዜጣው፤ ሱዳን የተወሰደባትን ግዛት የማስመለስ ተግባር ማከናወኗን እንዳስረዱ ጠቁሟል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ፤ ወረራውን የሱዳን ጦር እንደጀመረና ትንኮሳ እንዳልተፈጸመ በተደጋጋሚ የገለፀ ሲሆን የአካባቢው አርሶ አደሮችም የሱዳን ጦር ያልታሰበ  ድንገተኛ ወረራና ጥቃት እንደፈፀመባቸው ነው የተናገሩት፡፡
የሱዳን ጦር በአካባቢው እንዲሰፍር መደረጉ የአካባቢውን ደህንነት ለመጠበቅ ነው ያሉት የሱዳን ልኡክ መሪ ሱልማን፤ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የቆየ ወዳጅነት የሚያበላሽ እርምጃ ፈጽሞ አትወስድም ብለዋል፡፡ መፍትሄውም ሶስተኛ ወገን ባለበት መደራደር ነው ያሉት የልኡኩ መሪ፤ የማሸማገል ተግባሩንም የሳኡዲ መንግስት እንዲወስድ ጠይቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ፤ የሱዳን የጦር በሃይል ከተቆጣጠራቸው አካባቢዎች ለቆ ካልወጣ በስተቀር ድርድር እንደማይኖር በተደጋጋሚ ማሳሰቡ ይታወቃል፡፡
የዛሬ ሁለት ወር ገደማ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በህግ ማስከበር ተግባር ላይ መጠመዱን ያሰላው የሱዳን ጦር ድንበር ዘሎ በመግባት አካባቢውን በሃይል የወረረ ሲሆን እስካሁን የመውጣት ፍንጭ አላሳየም፤ እንዲያውም ይዞታውን ይበልጥ እያጠናከረና አካባቢውን ለቆ እንደማይወጣ እያስፈራራ ነው ተብሏል፡፡  

Read 12680 times