Saturday, 30 January 2021 10:50

የአዳማ ግንብ ገበያ ባለ አክሲዮኖች፤መንግስት እንዲታደጋቸው ተማፀኑ

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(2 votes)

  “ፍትህ ሲገባን የ151 ሚሊዮን ብር ባለዕዳ እንድንሆን ተፈርዶብናል”
                            
             በአዳማና አካባቢው በሚኖሩ ከ500 በላይ ነጋዴዎች የተቋቋመው ግንብ ገበያ ባለ አክስዮኖች፤ “ፍትህ ስንጠብቅ የ151 ሚ.ብር ባለ-ዕዳ ተደረግን” በማለት መንግስት እንዲታደጋቸው ተማጸኑ። ነጋዴዎቹ በ1991 ዓ.ም አክሲዮን ማህበሩን ካቋቋሙ በኋላ 525 ምድር ላይ ያሉ ሱቆችና ባለ 3 ወለል አራት የገበያ ህንጻዎቸን ለማስገንባት ኮራኮን ኮንስትራክሽን ከተባለ ተቋራጭ ጋር ተዋውለው ነበር። ተቋራጩ በ2 ዓመት ውስጥ ግንባታውን አጠናቅቆ ሊያስረክበን ቢስማማም በቃሉ ግን አልተገኘም ይላሉ ነጋዴዎቹ።
እስከ 2009 ዓ.ም ድረስ ሁሉም ሳይሳካ ቆይቶ የግንባታ ዋጋ ንሯል በሚል ተጨማሪ ማካካሻ 33 ሚ.ብር እንዲከፍሉ መገደዳቸውን የአክሲዮን ማህበሩ አዲሱ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሽሬ ረሺድ ያስረዳሉ፡፡
“ቦርዱ፣ ተቋራጩና አማካሪ ደርጅቱ በመመሳጠር፣ ከደሃው ህዝብ ገንዘብ ሲመዘብሩ ቢቆዩም  ጭራሽ ተቋራጩ ከአከስዮን ማህበሩ ቀሪ ገንዘብ አለኝ በሚል በከፍተኛ ፍርድ ቤት በ151 ሚሊዮን ብር ዕዳ ማህበሩን ከስሶ 117 ሚሊዮን ብር እንድንከፍል ተወስኖብናል ይላሉ በምሬት፡፡
ማህበሩ ጠበቃ ቀጥሮ ተከራክሮ ይግባኝ ሰሚ ከዚያም ሰበር ሰሚ፣ ችሎት ቢደርስም ሰሚ በማጣታችን ጉዳያችን በህገ መንግሰት አጣሪ ኮሚሽን እየታየ ነው፣ በየደረጃው ላሉት ፍርድ ቤቶች፣ የኦሮሚያ ፀረ-ሙስና የኦዲት ሪፖርትን በዋቢነት ብናቀርብም ሊሰሙንና ጉዳዩን በጥልቀት ሊያዩልን፣ አልቻሉም ሲሉ አማርረዋል ባለ አክስዮኖቹ።
ሽንኩርት ቸርችረው፣ በርበሬ ሸጠው፣ ቆጮ ፍቀውና ታግለው መጦሪያ ይሆነናል በሚል ከቋጠሯት ላይ ከ500 እስከ 800 ሺህ ብር አዋጥተው አክሲዮን የገዙ አቅመ ደካማ እናቶች ባለፈው ሀሙስ በአክሲዮን ማህበሩ ህንፃ ላይ እያለቀሱ ብሶታቸውን ገልጸዋል። 525 ባለ አክሲዮን ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ሰብስቦ የነበረ ቢሆንም የአክስዮን ድርሻ ሳይኖራቸው በቦርድ አባልነት የተመረጡ ሰዎች ከአማካሪው ETG ኮንሰልታንትና ከተቋራጩ ኮራኮን ኮንስትራክሽን ጋር በመመሳጠር በደሀው ህዝብ ላይ ብዝበዛ ሲያደርሱብን ቆይተዋል ብለዋል። ቦርዱ ከመመስረቻና ከመተዳደሪያ ደንቡ ውጪ ሶስት ዓመት ብቻ መምራት ሲገባው ለ11ዓመታት በጉልበት ሲመራና በህዝብ ገንዘብ  ላይ ሲቀልድ ቆይቷል ሲሉም አክለዋል። ህዝቡ ያዋጣው ከግማሽ ቢ ብር በላይ እያለ መበደር ሳይኖርብን ቦርዱ፣ ተቋራጩና አማካሪው ተመሳጥረውና ህዝቡን አስገድደው በማስፈረም መጀመሪያ 100 ሚ ብር ከንብ ባንክ  እድንበደር ተደረገ የሚሉት የቦርዱ ሰብሳቢ፤ ቀጥሎ ያለ ህዝቡ እውቅና ድጋሚ፣ 100 ሚ ብር አሁንም ከዚሁ ባንክ ብድር ወስዳችኋል ተባልን ይላሉ ባአክሲዮኖቹ ሳግ እየተናነቃቸው።
ግንባታውም ባለመጠናቀቁ የብድሩም ወለድ እየጨመረ በመምጣቱ፣ ቡና ባንክ ጅምሩን ህንፃ ሊሸጥብን ጨረታ ሲያወጣ አዋሽ ባንክ ህንፃዎቹ ያሉበትን ተጨባጭ ሁኔታ  በማየት፣ ለንብ ባንክ እዳችንን ከፍሎ ከመሸጥ አትርፎልንና የሁለት ዓመት እፎይታ ሰጥቶ ያዳነልን ቢሆንም አሁንም የአዋሽ ባንክን እዳ ለመክፈል ህንፃው ባለማለቁ ተቸግረናል፤ በዛ ላይ 30 በመቶ እንኳን ያልተጠናቀቀ፣ ጣሪያው ሙሉ በሙሉ የሚያፈስስ ጅምር ህንፃ ሆኖ ሳለ የአማካሪው ድርጅት ETG ኮንሰልታንት  ባለቤት ዶ/ር እሸቱ አሜሪካ ተቀምጦ ከማህበራችን  በወር 78 ሺህ ብር ደሞዝ እየተከፈለው 93 በመቶ ተጠናቅቋል የሚል ሪፖርት ፅፎብን፤ ለዚህ ሁሉ መከራ ስለዳረገን መንግስት በህግ ይጠይቅልን ሲሉ ተማፅነዋል።
በዚህ አክስዮን ምክንያት በለቅሶ እይታውን ያጣ፣ የአልጋ ቁራኛ የሆነ፣ ህይወቱ ያለፈ  ሁሉ እንዳለ  የአዲሱ የቦርድ አመራሮች ይናገራሉ።
“ተቋራጩ ኮራኮን ኮንስትራክሽን፣ አማካሪው ETG ኮንሰልታንት እና የማህበሩ የቦርድ አባላት በመመሳጠር አራቱንም ንህፃ ዙሪያውን አጥረው ባለ አክሲዮኑ አካባቢው ላይ እንዳይደርስ ከልክለው ህዝቡ ሲያለቅስ ከርሟል” የሚሉት ወ/ሮ አዳነች አበቤ የአዳማ ከተማ ከንቲባ በነበሩበት ጊዜ ጉዳዩን በዝርዝር በመረዳት፣ አጥሩን ከፍተው እንድንገባ መቼም አንረሳውም፤ ጅምር የቀረውን ንብረታችንን እንድናይና ፈጣታሪችንን እንድናመሰግን ለዋሉልን ውለታ እናመሰግናለን። ብድራቱን በልጆቻቸው ያግኙት ብለዋል።
አሁን ህንፃውን የተወሰነ ጨርሰን ሱቆች አከራይተን የአዋሽ ባንክን ዕዳ ለመክፈል ብንፍጨረጨርም አልቻልንም ይላሉ።
በተለያየ ጊዜ በቦርዱ አባላት በተቋራጩና በአማካሪ ድርጅቱ ላይ ክስ መስርተን 9 የቦርዱ አባላትና ተቋራጩ በእስር ላይ የነበሩ ቢሆንም መንግሰት የፖለቲካ እስስረኞችን ሲፈታ፣ በግርግር አብረው ወጥተው አሁንም ምስኪን ባለ አክስዮኞችን ስማችንን እንዳትጠሩ በማለት እስከ ማሳፈራራት የደረሱ እጀ ረጃጅሞች ስለሆኑ መንግሰት ያስታግስልን ብለዋል፡፡
እነዚሁ አካለት ተመሳጥረው ለንብ ባንክ  40 ሱቆችን በ37 ሚሊዩን ብር ገዝተው ብሩን በማህበሩ አካውንት ቢያስገቡም ያ 37 ሚሊዮን ብር ከህግ አግባብ ውጪ ከቦርዱ ጋር ተቋራጩም ፈራሚ ሆኖ ከማህበሩ አካውንት መውጣቱንና የት እንደደረሰ እንደማይታወቅ ተናግረዋል፡፡
“እንደ ኦሮሚያ ፀረ ሙስና መ/ቤት የምርመራ ኦዲት ሪፖርት ከሆነ በነዚህ አካላት እስካሁን ወደ 184 ሚ. ብር መመዝበሩንና እክሲዮን ማህበሩ እንኳን ዕዳ ሊኖርበት ቀርቶ ከተቋራጩ የሚጠብቀው ተመላሽ ገንዘብ እንዳለው ቢያመለክትም፣ ተቋራጩ ግን አዲስ አበባ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በ151 ሚሊዮን ብር ከሶን 117 ሚ.ብር ተፈርዶብናል፣ የአዋሽ ባንክ ብድርና ወለዱ 320 ሚ.ብር ደርሷል፣ በዚያ ላይ ገቢዎች የሚጠበቅብን የግብር ገንዘብ አለ፡፡ በዚህ ሁሉ አጣብቂኝ ውስጥ ሆነን ይህ ህንጻ በዕዳ ምክንያት  ቢሸጥ ሜዳ ላይ ከመውደቅ ውጭ አማራጭ የለንም” በማለት መንግስት እንዲታደጋቸው ተማጽነዋለ እድሚያቸው ከ80 ዓመት በላይ መሆናቸው ቆጮ በመፋቅ እድሚያቸውን የፈጁ፣ ከ1965 ጀምሮ ከማረቆ በርበሬ እያመጡ ሲነግዱ የኖሩና አሁን እይታቸውን አጥተው በሰው እየተመሩ የመጡ የ81 ዐኣመት አዛውንት እናት፣ ለዚሁ አክስዮን ሲሉ ቤት ሸጠው አክስዮን የገዡ የ86 ዓመት አዛውንትና በርካታ አቅመ ደካሞች የደረሰባቸውን በደልና ግፍ ለሚዲያ ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡
መንግሰት አሁንም በግርግር የተፈቱ የቦርድ አባላት፣ አማካሪውና ተቋራጩ ለመዘበሩት የደሃ ህዝብ ንብረት ተጠያቂ እንደሆኑ የኦሮሚያ ፀረ ሙስና የኦዲት ሪፖርትን መነሻ በማድረግ ተቋራጩ ካስበየናቸው ከ117 ሚ.ብር ዕዳ ነፃ እንዲሆኑና የሕዝቡ እንባ ኢንዲታበስ ነጋዴዎች መንግሰትን ተማጽነዋል፡፡


Read 12163 times