Saturday, 30 January 2021 10:55

“ህወኃት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተደምስሷል”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

   በ349 ሰዎች ላይ የእስር ትዕዛዝ ሲወጣ 124ቱ ተይዘዋል

                ህወኃት በሰሜን እዝ መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት አድርሶ ጦርነቱን ሲጀምር በ3 ወር ጊዜ ውስጥ በድል አጠናቆ ሃገሪቱን ለመቆጣጠር በማቀድ እንደነበር የአቃቢ ህግ የምርመራ ግኝት አመለከተ፡፡
ጠቅላይ አቃቢ ህግ በህግ ማስከበሩ ሂደት ተያያዥ የፍ/ቤት ሂደቶች ላይ ትናንትና  በሰጠው መግለጫ፤ ህወኃት ጦርነቱን ሲጀምር በቂ ዝግጅት አድርጎ፣ በፋይናንስና በሰው ሃይል ራሱን በሚገባ አደራጅቶ እንደነበር አመልክቷል፡፡
ህወኃት በ3 ወር አጠናቅቀዋለሁ ባለው ጦርነት ከ170ሺ በላይ ልዩ ሃይል ማዘጋጀቱን፤ ሱር፣መሶበ ሲሚንቶና መስፍን ኢንጂነሪንግ የተሰኙት የኢፈርት ደርጅቶች ደግሞ ምሽግ በመቆፈርና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ ሲረባረቡ እንደነበር በመግለጫው ተመልክቷል፡፡
በአጠቃላይ በዚህ የጦርነት እንቅስቃሴ ጉልህ ድርሻ አላቸው የተባሉ 349 ሰዎች ላይ የእስር ትዕዛዝ መውጣቱን  የገለፀው አቃቤ-ህግ እስካሁንም 124ቱ በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና ቀሪዎቹን የማደን ተግባርም ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቋል።
ተጠርጣሪዎቹ በሃገር ክህደት፣በሃገር ሉአላዊነት መዳፈር፣ በሽብር ወንጀሎችና በሌሎች ተደራራቢ ወንጀሎች የሚጠየቁ መሆኑንና ጠ/አቃቢ ህግ አስታውቋል፡፡ በተጠርጣሪዎቹ ላይም 680 የሰውና የሰነድ ምስክርነት የቀረበባቸው መሆኑ ተመልክቷል፡፡
ከ1000 በላይ ዜጎች በማንነታቸው በተጨፈጨፉበት የማይካድራው ጉዳይም 279 ሰዎች ተጠርጥረው እየታደኑ ሲሆን ከእነዚሁ መካከል እስካሁን 36ቱ በቁጥጥር ስር ውለዋል ተብሏል፡፡
በሌላ በኩል ከዚሁ በትግራይ ሲካሄድ ከነበረው የህግ ማስከበር እርምጃ ጋር ተያይዞ፣ በአሁኑ ወቅት ህወኃት ማንሰራራት ወደማይችልበት ደረጃ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ማይመለስበት ደረጃ መድረሱን የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቀነአ ያደታ አመልክተዋል፡፡

Read 13567 times