Monday, 01 February 2021 00:00

የአገራችን የ50 ዓመት ጉዞ፤ ጥፋትና ልማት

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(2 votes)

 ኢትዮጵያንና ኤርትራን በፌዴሬሽን ለማስተሳሰር በዓለም አቀፍ መድረኮች ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል።  ለአስር ዓመት የቆየው የፌዴሬሽን አስተዳደር ቀርቶ፣ ኤርትራ የኢትዮጵያ አንድ አካል እንድትሆን በታሰበ ጊዜ ንጉሠ ነገሥቱ አፄ ኃይለ ሥላሴና ሌሎች ሲደግፉ፣ ጸሐፊ ትእዛዝ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ፣ አቶ አበበ ረታና ሌሎች መቃወማቸውን አቶ ዘውዴ ረታ “በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት፤ የኤርትራ ጉዳይ” በተባለው መጽሐፋቸው ገልጸዋል።  ውሕደቱ በንጉሡ ፍላጎትና ተጽዕኖ ሳይሆን በኤርትራ ምክር ቤት ነፃ ውሳኔ መደረጉንም ጸሐፊው ጠቁመዋል፡፡
ከኤርትራ ነፃ አውጪ ድርጅት መሥራቾች አንዱ የሆነው መሐመድ አዶም፤ እ.ኤ.አ በ1961 ዓ.ም ካይሮ ላይ ቢሮ ከፈተ። ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥም በኤርትራ በረሃዎች፣ በመንግሥት ኃይል ላይ ጥቃት ሰነዘረ። በኢትዮጵያ ምድር የእርስ በእርስ ጦርነት ተጀመረ። የእርስ በእርስ ጦርነቱ በኤርትራ ምድር ተወስኖ አልቀረም። በየአካባቢው የመገንጠል ጥያቄ ያነገቡ ነጻ አውጭዎች ብቅ ብቅ አሉ። የኦሮሞ ነፃነት ግንባር፣ የኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባር፣ የሰሜን ሶማሌ ነፃ አውጪ ድርጅት፣ የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር፣ የሲዳማ አርነት ለአብነት ይጠቀሳሉ፡፡ የመገንጠል ሳይሆን ብሔራዊ ጥያቄ  አንስተው ከደርግ መንግሥት ጋር ይዋጉ ከነበሩት መካከል ደግሞ ኢዲዩ እና ኢሕአፓ ዋነኞቹ ነበሩ፡፡
በሐምሌ 1969 ዓ.ም በጀኔራል ዚያድ ባሬ የሚመራው የሶማሌ መንግሥት ጦር፣ ድንበር አልፎ ወረራ ጀመረ። ኢትዮጵያ በውስጥም በውጪም በጦርነት ተወጥራ ተያዘች። በመጋቢት 1970 ዓ.ም ሶማሌ ተሸንፋ የያዘችውን የኢትዮጵያን ግዛት ለቃ ወደ መጣችበት ለመመለስ ተገደደች፡፡
መንግሥት "በምሥራቅ የተገኘው ድል በሰሜንም ይደገማል” በማለት ፊቱን ወደ ኤርትራ መልሶ፣ ከሻቢያ ጋር መፋለሙን ቀጠለ። ሻቢያን ደምስሶ ለኢትዮጵያ እፎይታን ያመጣላታል የተባለው የቀይ ኮከብ ዘመቻ ግን ሳይሳካ ቀረ፡፡ የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር፣ ከሻቢያ ጎን ተሰልፎ፣ የኢትዮጵያን ጦር በመውጋቱ የታሰበው አልሆነም፡፡ የደርግ መንግሥት እየተዳከመ መሄዱን ተከትሎ፣ በግንቦት 1983 ሻቢያ አሥመራን በመያዝ ኤርትራን ሲቆጣጠር፣ ሕውሓት/ ኢሕአዴግም አዲስ አበባን ይዞ መንግሥት መሰረተ።
ከኤርትራ ጋር ለዓመታት የዘለቀው ጦርነት ቢያበቃም፣ ኢትዮጵያ ግን ሰላም አልነበረችም። በሽግግሩ መንግሥት ምሥረታ ላይ የነበሩት የኦሮሞ ነፃነት ግንባርና የኦጋዴን ነፃ አውጭ ግንባር ወደ በረሃ ተመልሰው የደፈጣ ውጊያቸውን ቀጠሉ።
ሻቢያ በ1976 ዓ.ም የድንበር ጥያቄ  ለህውሓት አቅርቦ ነበር፡፡ ህወሓት እንዲህ  ዓይነት ጥያቄ ለመወሰን አሁን አልችልም የሚል ምላሽ መስጠቷን አስቀድሜ ላስታውስ። ህወሓት አዲስ አበባ ላይ፣ ሻቢያ አሥመራ ላይ ከነገሱ በኋላ ሻቢያ የድንበር ጥያቄውን እንደገና ቀሰቀሰ፡፡ ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ተደጋጋሚ ደብዳቤም ጻፈ፡፡ መልስ ሲያጣ ሚያዚያ 28 ቀን 1990 ዓ.ም ጦርነት ከፈተ፡፡ በተከታታይ ውጊያ ባድመን ከፊል ሽራሮን፣ ዛለአምበሳን፣ አሊቴናንና ኢሮብን ፣ በአፋር በኩል ደግሞ ቡሬን  እንደያዘ ዶ/ር  ደጃዝማች ዘውዴ ገ/ሥላሴ፤ “የኢትዮጵያና የኤርትራ ግጭት፤ መፍትሔው” በተባለው መጽሐፋቸው ገልጸዋል።
ከዚህ ጊዜ በኋላ ኢትዮጵያ ከባድ ጦርነት ባታካሂድም፣ እንደ ኦጋዴን ያሉት የአገሪቱ አካባቢዎች አልፎ አልፎም ቢሆን ጥይት ይጮህባቸው ነበር፡፡ ጦርነት አልነበረም ማለት ግን በየቦታው ሰላም ሲደፈርስ አልቆየም ማለት  አይደለም። ዘመነ ህውሓት ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ ዜጎች በዘራቸው ሳቢያ ከመኖሪያቸው ሲፈናቀሉና ሲገደሉ ነው የከረሙት፡፡
ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የሚመሩት የለውጥ መንግስት ሥልጣኑን ከተቆጣጠረ በኋላም፣ መፈናቀሉና ግድያው ተባብሶ መቀጠሉ ይታወቃል። በኦሮሚያና በቤንሻንጉል ክልሎች እየደረሰ ያለው አሰቃቂ  የወገን ሞትና መፈናቀል እግዚኦ! የሚያሰኝ ነው፡፡  
በትግራይ ሕግ ለማስከበር ያለቀው ወገን ጉዳይም እንደ እግር እሳት ልብን የሚበላ ነው። “ሐዘንሽ ቅጥ አጣ ከቤትሽ አልወጣ” የሚለው ነው የተደጋገመው። ኢትዮጵያ ሰላም በማጣቷ ሳቢያም ልማቷና ዕድገቷ ክፉኛ ተስተጓጉሏል፡፡
በአንፃሩ፤ ሰሞኑን የአሰዋን ግድብ በይፋ አገልግሎት የጀመረበትን ሃምሳኛ ዓመት በማክበር ላይ የምትገኘው ግብጽ፤ ለስድስቱ ቀንና ለአስራ ዘጠኝ ቀን ከዘለቀው የአረቦችና የእሥራኤል ጦርነት በስተቀር የገጠማት ሰፊ ጦርነት የለም። ያለፉትን ስልሳ ዓመታት ያሳለፈችው በከፍተኛ የልማት እንቅስቃሴ ነው፡፡ ከ169 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር በላይ ውኃ የሚይዘው የአሰዋን ግድብ፤ በዚያ በረሃ ውስጥ ግብጽን ሁሌም ለምለምና አረንጓዴ የለበሰች አድርጓታል። ከ272 ሺ ኪሎ ሜትር  በላይ ርዝመት ባለው ቦይ የአባይን (ናይል) ውኃ በማስተላለፍ፣ አገሪቱን ከዳር ዳር እንዲያዳርስ አድርጋለች። በምግብ እራሷን ከመቻል አልፋ ለጎረቤቶቿ ቀላቢ እስከ መሆንም ደርሳለች፡፡ ከፍራፍሬ ምርቶቿ ሸማቾች አንዷ ደግሞ የኛው አገር  ኢትዮጵያ መሆኗ ያስገርማል፡፡
ከዘመነ መሣፍንት አስተሳሰብ ያልተላቀቀው የኢትዮጵያ ፖለቲካ፤ የጋራ ግብ ነድፎ በጋራ መንቀሳቀስ ሆኖለት አያውቅም፡፡ ይልቁንም እርስ በርስ የመገፋፋት የመጠላለፍና የመጠፋፋት ታሪክ ነው ያለው፡፡ በርግጥ ለዚህም የውስጥ ችግራችን ቢሆን፣ ረጅሙ የግብፅ እጅ ፈጽሞ የለበትም ብሎ መፈጠም  የዋህነት ነው።
የሆኖ ሆኖ እኛ ተስማምተን ለልማት በጋራ መትጋት ሲገባን፣ እርስ በርስ ስንጠላለፍ፣ ግብፆች በእኛ ውሃ እያለሙ፣ አገራቸውን ያጠግባሉ፤ ያበለጽጋሉ፡፡
መንቃት ሆይ ወዴት ነህ!?

Read 9710 times