Saturday, 30 January 2021 16:14

እንደ መንደርደሪያ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 “እኔ ፖለቲካ አልፈራም! ፖለቲከኞችን ግን እፈራለሁ” ይለኝ ነበር አንድ ወዳጄ፡፡
ይሄ አባባል ትክክል መሆኑ ዘግይቶ ነበር የገባኝ፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገሮች ከፖለቲካ ውጪ ነኝ ማለት እጅግ ከባድ ነው፡፡ ምክንያቱም አድሎ፣ መገለል፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ የኑሮ ውድነት፣ የመፃፍና የመናገር ዴሞክራሲያዊ መብት አፈና…የቀን ተቀን የህይወት ውጣ ውረድ በሆነባት ሀገር ውስጥ ራስን ከፖለቲካ ውጪ ማድረግ ይቻላል ብሎ ማሰብ ከባድ ይመስለኛል፡፡
መብቱ ሲጣስ ለምን ብሎ መጠየቅ፣ አድልዎና መገለል ሲደርስበት ይህን መቃወም ተፈጥሯዊ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የየትኛውም የፖለቲካ አባል ሳይሆኑ ብዙዎች መከራ ተቀብለዋል፣ ግፍም ተፈጽሞባቸዋል። ለመብቱ የቆመን ሰው ፖለቲከኛ አስብሎ መከራ እንዲቀበል አድርጎታል፡፡
ከሁሉ የከፋው ግን ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲ በሀገራችን እንዳይወጣ ገዢው ፓርቲ ሲጓዝበት የነበረው አስቀያሚ የጨለማ መንገድ ሁሌጊዜ ሲያበሳጨኝ ይኖራል። በፖለቲካ ፓርቲዎች ላይም እምነት እንዳይኖረን አድርጓል፡፡ በወቅቱ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ሲያራምድ የነበረው ሀሳብ ገዢ አለመሆኑንና ሕዝብ እንደማይቀበለው አስቀድሞ የተረዳ እንደሆነ በግለጽ ያወቀው ይመስለኛል፡፡ ለዚህም ሳይሆን አይቀርም በሃሳብ ልእልና ከመፋለም ይልቅ በተፎካካሪ ፓርቲዎች መሃል የራሱን ሰዎች አስርጎ በማስገባትና በተቃዋሚዎቹ ውስጥ ያሉትን ጠንካራ አባላት በተለያየ ማስፈራሪያ፣ ጥቅማጥቅምና እጅ መንሻ እጃቸውን ጠምዝዞ በማስገደድ ማስፈራራት ላይ የተጠመደው፡፡
ሀሳብን የሚፈራ እርሱ የመጨረሻ ፈሪ ብቻ ሳይሆ የተሸነፈ ነው፡፡ የኔ ሃሳብ የተሻለ ነው ብሎ በያዘው ሀሳብ እምነት ያለው ከየትኛውም አቅጣጫ የሚመጣን ሀሳብ በሀሳብነቱ ሳይፈራ ሊሞግት ይገባል፡፡
በተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥ ሰርገው በገቡና በተለያዩ አስገዳጅ ምክንያቶች አባል በሆኑበት ፓርቲ ውስጥ ሆነው ለገዢው ፓርቲ መረጃዎችን በማቀበል ስራ ውስጥ በተሳተፉ ሰዎች ምክንያት በርካታ ኢትዮጵያዊያን ስቃይና ግፍ ተቀብለዋል። በእኔ እይታ በያዙት የፖለቲካ አቋም ምክንያት ግፍና ስቃይ የተፈፀመባቸው ኢትዮጵያዊያን በሙሉ አሸናፊዎች ናቸው። ዛሬ ግን ከገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ውስጥ ሀሳብ ያለው መሪ ተወልዷል ብዬ አስባለሁ ይሄ ለኢትዮጵያችን ትንሳኤ ይመስለኛል፡፡
በተቃዋሚነትም ይሁን በተፎካካሪነት እየተንቀሳቀሱ ያሉ ፓርቲዎችም በራሳቸው ውስጥ ያለውን የውስጥ ዴሞክራሲ ሊፈትሹ ይገባል እላለሁ፡፡ ምክንያቱም በዴሞክራሲ ስም እየማሉና እየተገዘቱ እነርሱ ግን ዴሞክራት ካልሆኑ ነገ የስልጣን እርከኑን ሲቆናጠጡ አምባገነን እንደማይሆኑ ምንም  ማረጋገጫ አይኖረንም፡፡ በሌላም በኩል የችግራቸውን ሁሉ ምንጭ  ውጫዊ በማድረግና በሌላው ላይ በማላከክ ራስን ንጹህ አድርጎ የማቅረብ አዝማሚያም ሊወገድ ይገባል እላለሁ፡፡
*   *   *
የመሰብሰቢያ ጐጆዋን ጸጥታ የሚገስ ነጎድጓዳማ ድምጽ ተሰማ…. ጥንድ ዓይኖች ሁሉ ወደ መድረኩ ተወረወሩ… ሊቀመንበሩ ይሁንበላይ ጠይም ፊታቸው ላይ ወዛቸው ቸፍ ብሏል፡፡ በርበሬ የሚመስሉት አይኖቻቸው ዛሬም እንደቀሉ ናቸው፡፡ “ለዛሬ እዚህ ቦታ ላይ ለመሰብሰብ ያስገደደን ዋናው ምክንያት ስብሰባው ምስጢራዊ እንዲሆን ስለተፈለ ነው” በማለት ሊቀመንበሩ አቶ ይሁን በላይ ስብሰባው ከጽህፈት ቤት ውጪ የተደረገበትን ምክንያት በአጭሩ በመግለጽ ንግራቸውን ጀመሩ፡፡
አስከትለውም “…በጽህፈት ቤታችን ውስጥ የምናደርጋቸው ስብሰባዎችና የምናካሂዳቸው ውይይቶች ለገዢው ፓርቲ እየደረሱ በአባላቶቻችን ላይ ጥቃት ሲሰነዘር ቆይቷል፡፡ በቅርቡም በማዕከላዊ እስር ቤት ለወራት ያህል ታስሮ ሰቆቃና ግፍ ሲፈጸምበት ቆይቶ ከእስር የወጣው ወንድማችን ይታገሱ ደበበ አንዱ ማሳያ ነው።
እኛ በዚህ ፓርቲ ውስጥ የተሰበሰብን አባላት በሙሉ ዘር፣ቋንቋ፣ ሃይማኖት…. ሳንል በኢትዮጵያ አንድነት ስር የተሰባሰብን የአንድ ሀገር ልጆች ነን፡፡ ትግላችን፣ መውጣት መውረዳችን፣ ማዘን መደሰታችን፣….ለዚህቺው መተኪያ ለሌላት እናት ሀገር ነው። በዚህ ሀገራችን ላይ እውነተኛ ዴሞክራሲና የእያንዳንዱ ዜጋ ሰብአዊ መብት ተከብሮ እስክናይ ድረስ ትግላችን በቀላሉ አይገታም። ይህ ደግሞ ቀላል አይሆንም፡፡
ገዢው ፓርቲ ከሚደርስብን ወከባና እንግልት በላይ በእኛው ውስጥ ተሰግስገው እኛኑ የሚያስጠቁን መኖራቸው ምንም እንኳን ትግላችንን ጠመዝማዛ ቢያደርገውም ትግሉን ግን ፈጽሞ ሊቀለብሰው አይችልም። ስለዚህም ትግሉ የትኛውንም ያህል ዋጋ ቢጠይቅ የሚከፈለውን ሁሉ መስዋዕትነት በመክፈል ከዳር ማድረሳችን አይቀሬ ነው፡፡
አንድ ነገር ለሁላችሁም ግልጽ ማድረግ  የምፈልገው ገዢው ፓርቲ አይኑን በእኛ ላይ መጣሉን ነው፡፡
ለዚህም ነው ቀን ከሌሊት ያለ እረፍት ሰላዩቹን መድቦና በውስጣችንም አስርጎ በማስገባት ስለላ የሚያካሂድብን። ይህ ደግሞ ምን ያህል በእኛ ትግል እንቅልፍ ማጣቱን ያመለክታል፡፡ በመሆኑም ነቅተንና ቆቅ ሆነን እያንዳንዱን እንቅስቃሴ መከታተልና መረጃዎችን በሚስጢር መጠበቅ ይኖርብናል፡፡
ዛሬ ልንወያይበት ያስፈለገን ጉዳይም በመካከላችን እሾህ ሆኖ የሚወጋን አንድ አባል ባሰባሰብነው ማስረጃ መሰረት ለማጋለጥና ሁላችንም በዚህ ጉዳይ ላይ ተወያይተን ጠንካራ ውሳኔ ለማሳለፍ ነው። ስለ አባሉ ከመግለጻችን በፊት ግን ከዚህ ከፓርቲያችን ውስጥ በወጣው መረጃ ምክንያት ስቃይ የደረሰበትን አባላችን ይታገሱ ደበበ ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ የደረሰበትን እንግልት እንዲገለጽልን እድሉን እሰጠዋለሁ” አሉና ይታገሱ እንዲናገር ጠቆም አደረጉት፡፡
ይታገሱ ለአፍታ ዓይኖቹን ተሰብሳቢ አባላቱ ላይ አንከራተተና በእጆቹ አገጩ ላይ ያሳደገውን ሪዙን እያሻሸ “አመሰግናለሁ!...” በማለት ንግግሩን ጀመረ፡፡”… አመሰግናለሁ ክቡር ሊቀ መንበር!... ዛሬ በዚህች ቦታ ላይ የደረሰብኝን ስቃይ በህይወት ኖሬ ለመናገር ስለተፈቀደልኝ ደግሜ አመሰግናለሁ። ትዝ ይለኛል ከመያዜ ከሁለት ሳምንት በፊት ነበር በጽህፈት ቤት ውስጥ ከሰሜን ሸዋ ከመጡ አምስት ወጣቶች ጋር ስለ ፓርቲሪያችን ፕሮግራምና ዓላማ ውይይት ያደረግነው፡፡
ወጣቶች በሀገሪቱ ውስጥ እየተካሄደ ባለው ሰላማዊ ትግል ደስተኞች አልነበሩም። የመጡበትም ዋናው ምክንያት ሰሜን ሸዋ የተደራጀ ሁሉን አቀፍ ትግል ማድረግ ስለሚቻልበት ሁኔታ ከፓርቲያችን ጋር ለመነጋገር ነበር፡፡ ፓርቲው ሙሉ በሙሉ ሀሳባቸውን ከተቀበለ የሚያስፈልገውን የስንቅና ትጥቅ ድጋፍ እናገኛለን በሚል ተስፋ ነበር የመጡት፡፡
መጀመሪያ ይህን ሀሳባቸውን ሲያቀርቡልኝ ገዢው ፓርቲ እኛን ለመሰለል የላካቸው ቅጥረኞች መስለውኝ ስለነበር በጥርጣሬ ነበር ያየኋቸው ስለዚህም በዴሞክራያዊ ምርጫ በህዝብ ተሳትፎ በማሸነፍ ሕዝብን የሥልጣን ባለቤት ማድረግ ይቻላል ብዬ ስለ ሰላማዊ ትግል ገለጻ አደረኩላቸው፡፡ የትጥቅ ትግል ለሀገሪቱ ለበርካታ ዓመታት ያለፈችበት መስመር በመሆኑና በርካታ ኢትዮጵያዊያን እንደ ቅጠል የረገፉበት የትግል ስልት በመሆኑ ዳግም ሀገራችን በዚህ አዙሪት ውስጥ ልንከታት እንደማይገባ አጽንኦት ሰጥቼ ነገርኳቸው፡፡
ስለዚህም ትላንት የፈሰሰው የንፁሃን ኢትዮጵያዊያን ደማቸው ሳይደርቅ ዛሬም ሌላ ደም የምንገብርበት ሁኔታ ሊኖር ስለማይገባ ፓርቲያችን ሀገራችን ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር የትጥቅ ትግል ተቀባይነት የሌለውና የኛ ትግል ስልት ሰላማዊ ትግል እንደሆነና የኃይል አማራጭ አስፈላጊነቱ በፓርቲያችን ተቀባይነት እንደሌለው በማስረዳት ሸኘኋቸው፡፡




Read 2632 times