Saturday, 30 January 2021 16:16

“ሰው ከሠራ ይሳሳታል”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሚስተር ሥራ ውሎ ደክሞት ቤት ይገባል፡፡ ባይደክመውም “ደክሞኛል፣” ስላለ በቃ ደክሞታል አንበል፡፡ (የምር እኮ...ሥራ ውለን፣ ወይም መሥሪያ ቤት ውለን ቤታችን ስንገባ “ሥራ አድክሞኝ ነው የዋልኩት፣” የምንል ሰዎች ሁሉ በእውነት ያደከመን ሥራው ከሆነ፣ ይህች ሀገር እስካሁን የት በደረሰች ነበር፡፡) እናላችሁ... አባወራችን ‘ላብ ማድረቂያ’ አሪፍ ምግብ ያስፈልገዋል...ብዛት ሳይሆን ጥራት፡፡ ማዳም እማወራ ደግሞ ቀድሞ እንዲመገብ ምን ብታዘጋጅለት ጥሩ ነው... ምን የመሰለች የዶሮ ሾርባ፡፡ (ተራውን የሚጠብቀው እንጀራ በሹሮው እንደ ‘ሜይን ኮርስ’ ሊወሰድ ይችላል፡፡ እነ እንትና ‘ሜይን ኮርስ’ የተባለው በእናንተ ቋንቋ እንደምትሉት ‘ትምሮ’ ሳይሆን ሳይሆን ምግብ ቢጤ ነው፡፡)
እኔ የምለው... ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ.... በዓመት በጣም ከተመቸን ሁለት ወይም ሦስት ጊዜ ብቻ ልናገኘው የምንችለውን የዶሮ ሾርባን፣ የጉንፋን መድሀኒት ማድረግ ‘ፌይር‘ ነው! አሀ...ከየትም ብሎ ለሚደርስብን የጤና ችግር፣ የትም ብለን የማንደርስበትን ነገር መድሀኒት አታድርጉብና!
የእውነት ግን... እንግዲህ ጨዋታም አይደል... እዚህ ሀገር እንደሆነ ትንሽ የጤና ችግር በገጠመ ጊዜ በመድሀኒትነት የሚሰጠን ምክር እስካሁን መድሀኒቱ ምን እንደሆነ ሳይንስ ደርሶበት እንደሆነ እንኳን ያልታወቀ ‘ሆድ መባስ’ የሚል ችግር የሚያስከትል ነው፡፡  
“አንተ ዘለዓለምህን የኪኒን መአት ስትውጥ፣ የመርፌ መአት ስትጠቀጠቅ ልትኖር ነው እንዴ! በደንብ አድርግህ ስማኝ፣ ምን እንደምታደርግ እኔ እነግርሀለሁ። ስማኝ... እህ ብለህ ስማኝማ፣ ላቱ እንዲህ ተጠለቅልሎ መሬት ሊነካ የደረሰ ሙክት አለ አይደል! እሱን ትገዛና ምንም ሳይሰሰት አጥንቱን በርከት አድርገህ ቀቅለህ፣ እሱን መጠጣት፡፡ እየው፣  እሱን ሁለት… ሦስት ሳምንት ግጥም ብታደርግ… አይደለም በሽታ ብሎ ነገር ባለህበት ድርሽ ሊል፣ ራስህ ላቷን መስለህ ነው የምትወጣው፡፡” በእርግጥ አንዳንድ እንዲህ የሚሉንን ሰዎች፣ ከበግ ነጋዴዎች ጋር የጥቅም ትስስር ሳይኖራቸው አይቀርም ብለን እንደምንጠረጥር ይታወቅልንማ! እናላችሁ... የታመመው ሰው ገና የሀሪ ፖተርን የመሰለው የሙክቱ ትርክት ከአእምሮው ሳይወጣ ሌላኛው መካሪ ይመጣል፡፡
“ስማ...ይሄ እንደው ግርማ ሞገስ ያለው ዶሮ አለ አይደል...እሱን ሸክ ታደርግና ጠዋት፣ ቀንና ማታ እየደጋገምክ ሾርባህን ግጥም እያደረግህ፣ አስከትለህ ደግሞ አጭሬውን ፈረሰኛውን ምኑን በወይራ ዘይት እያስጠበስክ...” (ወደ ተከታዩ ገጽ ይዞራል፡፡) አስራ አምስት ቀን  ብትመገብ አይደለም አንተ፣ አንተን ያየ ሁሉ ከበሽታ ይድናል፡፡ (“ሌላው በዝቶብናል ደግሞ የዶሮ ሾርባ ነቢይነት መጣብን!” ብንል ምን ይገርማል!) እናማ የሙክት መረቅና የዶሮ ሾርባ ምክር የምትሰጡን ወዳጆቻችን ረጋ በሉማ! አሀ... የአስራ አምስት ብር ሙዝ ይዛችሁ መጥታችሁ አስራ አምስት ሺህ ብር የሚያስወጣ ምከር አትስጡና! አስቡልና...መጀመሪያውኑ የጤና ችግር የመጣው እኮ  የሙክት መረቅና የዶሮ ሾርባው ስለራቀን ነው!
እናላችሁ... ከሥራ ደክሞት የገባው አባወራ ገና የዶሮ ሾርባው ሲቀርብለት መላ ሰውነቱ ይነቃቃል፡፡ በሆዱም “ይህንንስ በሾርባ ማንኪያ ሳይሆን በመለስተኛ ጭልፋ ና ግባ በሞቴ ማለት ነበር!” አይነት ነገር ይጀምራል፡፡
አንድ ማንኪያ፣ ሁለት ማንኪያ፣ ሦስት ማን....‘ቆይ ቆይማ! ይሄ ጥቁር ነገር ምንድነው? አጭሬውንም አብራ ጨምራው ነው እንዴ!’ አየት ያደርግና በማንኪያው ገልበጥ፣ ገልበጥ ሲያደርገው ድንግጥ! ምን! እንደገና ገልበጥ ሲያደርገው ምን ቢሆን ጥሩ ነው... የአውራሪስ ቀንድ ያለው የሚመስል ግድንግድ ዝምብ፡፡
እማወራ ጉድ ፈላባት!
“ስሚ፣ ይሄ ምንድነው?”
“ምኑ?”
“እዚህ ሾርባ ውስጥ ያለው ምንድነው?”
“ስጋው ይሆናላ...
“ይሄ ነው ስጋ! ነይና ተመልከቺው!” ማዳም እማወራ ትመጣና፣ እሷም በማንኪያ ገልበጥ፣ ገልበጥ አድርጋ ታያለች፡፡ ታይና ፈገግ ትላለች፡፡
“ውይ... ዝምብ ነች እንዴ! እኔ ደግሞ ምን ጉድ ተፈጠረ ብዬ!” ብላ አቶ ባልን አየት ስታደርገው፣ ብቻውን ሠላሳ ሰው ለመግጠም የተዘጋጀ ይመስላል፡፡ እና ምን ብትል ጥሩ ነው...
“ይሄ እኮ የሚገጥም ነገር ነው፡፡ ደግሞ ሰው ከሠራ ይሳሳታል፡፡” (አሁን ይሄ ሰውዬ ሰማንያውን መቶ ሰማንያ ቦታ ካልሸረካከትኩ በሚል ያዙኝ ልቀቁኝ ቢል ይፈረድበታል! አሀ... “የዶሮ ሾርባና የዝንብ ኮምቦ አዘጋጁልኝ፣” አላለማ! ቂ...ቂ...ቂ...
እናላችሁ...ይቺ “ሰው ከሠራ ይሳሳታል” የሚሏት ነገር ከሀላፊነት እንደ ማምለጫም እየሆነች ነው፡፡ ምንም ይሄ ነው የሚባል ሥራ ሳይሠራ “ሰው ከሠራ ይሳሳታል ከሚባልባቸው” ሀገራት የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊዎች እኛ ሳንሆን አንቀርም፡፡
ለአንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከሚሰጠው የአየር ሰዓት ላይ ተቀንሶ ለዚች ስንኝ ይሰጥልንማ! ልክ ነዋ...የእነሱን እኮ “አቶ እከሌ የአንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ሀሳብ ጠቅለል አድርገው ይነግሩናል፣” ማለት ይቻላላ! እናላችሁ...መንቀባረር የሚመጣው እውቀት ሞልቶ ስለፈሰሰ አይደለም ለማለት ያህል ነው፡፡
ለምሳሌ እንበልና የሆነ ባለሙያ የህክምና ስህተት ይፈጽማል፡፡ የፈለገውን ቢሆን በእንዲህ አይነት ወሳኝ ሙያ ላይ “ሰው ከሠራ ይሳሳታል፣” ማለት አሪፍ አይደለም። እንደዛ አይነት ነገሮች እንሰማለንና ነው፡፡
አንዳንዴ ደግሞ “ሰው ከሠራ መቼም ይሳሳታል፣” ከተባለ በኋላ ምን ይከተላል መሰላችሁ... “ይቅርታ እንጠይቃለን” ይባላል፡፡
የልብን ሠርቶ ይቅር በሉኝ
ምንስ አጠፋሁ ምን በደልኩኝ
እያለ አለ ሰውን የሚያሞኝ
የምትል ዘፈን አለች አይደል... በችሎታና በቸልተኝነት ‘የሚሳሳቱትን’ ያው የልባቸውን እንደሠሩ ብንጠረጥርስ! ልከ ነዋ... የማይችሉትን “አልችለውም” ማለት እኮ ብልህነት ነው፡፡ ስሙኝማ... የእውነት ግን ዘንድሮ በብዙ ስፍራዎች ሥራዎች በተገቢው ሁኔታ የማይሠሩት ወይም መአት ‘ስህተቶች’ የሚፈጸሙት ሥራና ሠራተኛ ባለመገናኘታቸው አይመስላችሁም! እናላችሁ... አንድ ሺህ አንድ ስህተቶች እየፈጸሙ “ሰው ከሠራ ይሳሳታል፣” አከታትሎ ደግሞ “ይቅርታ እንጠይቃለን” ቀሺም ነገሮች ናቸው፡፡  
ስሙኝማ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...እንዲህ ሁሉ ሆኖ ግን ‘ስህተት’ እየሠሩም ደረታቸውን ፊኛ የሚያሳክሉ መአት ናቸው እኮ! ስህተት መሥራት እኮ አለ አይደል... ጭምት አያደርግም ወይም አንገት አያስደፋም፡፡ ኮሚክ እኮ ነው...ሁሉንም ነገር የምናውቅ ሰዎች በዛንና በትንሽ ትልቁ ቀብረር ማለት የበዛ አይመስላችሁም!
ከዚህ በፊት የጠቀስናትን የዘፈን ስንኝ እንድገማትማ...
እንደ አፈር ፍርክስክስ ለሚለው ገላችን
እንደ ደንጋይ ስብር ለሚል አጥንታችን
የእኛ መንቀባረር ከቶ ለምንድነው
የአፈር መለሰኛ ጭቃ ለምንሆነው፡፡
እና ምን ለማለት ነው...በአቅም ማነስና በቸልተኝነት፣ በሥራ ፍላጎት ማጣት፣ አልፎ አልፎም ሆነ ተብሎም ነገሮች እየተበላሹ “ሰው ከሠራ ይሳሳታል... እየተባለ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ (ይቺን ነገር በአጭርኛ ያ.ሁ.ያ. ሲሏት አነበብኩ ልበል!)
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1728 times