Saturday, 06 February 2021 11:39

በትግራይ ያለው ሁኔታ አሁንም የበለጠ ያሳስበናል - ዓለማቀፍ ተቋማት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

       የተከሰቱ ሰብአዊ ቀውሶች በገለልተኛ አካል መጣራት ይገባቸዋል

             በትግራይ ከተከናወነው የህግ የማስከበር ዘመቻ ጋር ተያይዞ የተከሰቱ የሰብአዊ መብት ቀውሶችና የኤርትራ ወታደሮች በጦርነቱ የመሳተፋቸው ጉዳይ በገለልተኛ አካል፣ በአስቸኳይ እንዲጣራ፣ መድረክ ጠይቋል፡፡
አለማቀፍ ተቋማት በበኩላቸው፤የሰብአዊ ቀውሱ ይበልጥ አሳሳቢ ሆኖብናል ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት መድረክ፣ በትግራይ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ከሰሞኑ ባወጣው  መግለጫ፤ ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ በትግራይ እየተፈጠረ ያለው ሰብአዊ ቀውስ በእጅጉ አሳስቦኛል ብላል፡፡
በጦርነቱ የተፈጠረው ቀውስ ክልላዊ ብቻ ሳይሆን ሀገራዊ የኢኮኖሚ ቀውስ የሚፈጥር ነው ያለው መድረክ፤ #በክልሉ የመሰረተ ልማት አገልግሎት መቋረጥና የንግድ እንቅስቃሴ መቀዛቀዝ ህብረተሰቡን ለጉስቁልና ዳርጎታል፤ ይሄ ደግሞ ቆይቶ ሃገራዊ ቀውስ ይፈጥራል፤ስለዚህ በጊዜ እልባት ያሻዋል; ብሏል፡፡
መድረክ በዚሁ መግለጫው፤ በጦርነቱ ለተጎዱ ዜጎች በሙሉ አስቸኳይ ሰብአዊ ድጋፍ እንዲደረግ፣ የተፈናቀሉትም  በአፋጣኝ እንዲቋቋሙ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በተጨማሪም ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በገልተኛ አካላት መጣራት እንዲደረግላቸው፣ የኤርትራ ወታደሮች በጦርነቱ መሳተፍና ኢ-ሰብአዊ ድርጊት መፈፀም ጉዳይም ተጣርቶ እንዲቀርብ እንዲሁም የማንነት ጥያቄን አስታከው የሚቀርቡ የግዛት ማካለል ጉዳዮች ህጋዊ መንገድ ብቻ እንዲከተሉ መድረክ ጠይቋል፡፡
የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር፤በሁሉም ትግራይ፣ መልሶ የማቋቋም ስራ በተሳካ መልኩ እንዲያከናወን አሳስቧል ---መድረክ በመግለጫው፡፡
በተደጋጋሚ የትግራይ ወቅታዊ ጉዳይ ያሳስበኛል ሲል የቆየው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፤ሰሞኑን በጉዳዩ ላይ እንደሚመክር ታውቋል፡፡
የድርጅቱ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ፤ በትግራይ ያለው ሁኔታ ግልጽ መረጃ ያልቀረበበት በመሆኑ አሁንም ያሳስበናል ብለዋል፡፡ ሰዎች በጅምላ መጨፍጨፋቸውን፣ ዘረፋዎችና የአስገድዶ መደፈር ወንጀሎች መፈጸማቸውን የተመለከተ ማስረጃ ማሰባሰቡን የገለጹው አምነስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ፤ በጦርነቱ ከ450 ሺህ በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል፤ 2.3 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች ደግሞ እርዳታ ይሻሉ ብሏል፡፡
ተፈፅመዋል የተባሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችም በገለልተኛ አካል እንዲጣሩ አምነስቲ ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ ጠይቋል፡፡

Read 932 times