Saturday, 06 February 2021 12:00

ምርጫ ቦርድና ተቃዋሚዎች “በቻተም ሃውስ” በምርጫ ዝግጅት ላይ ተወያዩ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

በግንቦት በሚካሄደው ምርጫና ተያያዥ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ት ብርቱካን ሚዴቅሳ። ጠ/አቃቢ ህግ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ፣ የኢዜማ መሪ ፕ/ር ብርሀኑ ነጋና የኢሶዴፓ ሊቀ መንበር ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ በእንግሊዙ የጥናት ተቋም ቻታሞ ሃውስ የኢንተርኔት መድረክ ሰፊ ውይይት አድርገዋል፡፡
የእንግሊዝ የጥንት ተቋም  “ቻተሞ ሃውስ”፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ባዘጋጀው በዚህ ውይይት፤ በቀጣዩው ምርጫ ሊያጋጥሙ በሚችሉ ተግዳሮቶች፣ የፀጥታ ሁኔታና የምርጫ ቅስቀሳ ነፃነት እንዲሁም የአለማቀፍ ታዛቢዎችና የምርጫ ሂደት ጉዳይ በተወያዮች በስፋት ተመክሮበታል፡፡
የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ጠ/አቃቢ ህግና የሁለቱ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች በተሳተፉበት በዚህ ውይይት፤ የምርጫ ቦርዱ ሰብሳቢዋ ወ/ሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ፤ ቦርዱ ለምርጫው ስላደረጋቸው ዝግጅቶች በሰፊው ያስረዱ ሲሆን በአሁኑ ወቅት 53 የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው ለመወዳደር ተመዝግበው ምልክት መውሰዳቸውን አስታውቀዋል፡፡
ከትግራይ ክልል ውጪ በሌሎች የሃገሪቱ አካባቢዎች ለምርጫው ጠንካራ ዝግጅት መደረጉን የጠቆሙት ሰብሳቢዋ፤ የፀጥታና ሰላም መታጣት ችግር በምርጫው ተግዳሮት እንዳይሆን ከሚመለከተው የመንግስት አካል ጋር የማስተካከያ ተግባራት እየተከናወኑ  መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
መጪውን ምርጫ ለታዛቢዎችና ለመገናኛ ብዙሃን ክፍት በማድረግም ነፃነቱንና ግልጽነቱን የጠበቀ መሆኑን ለማረጋገጥ ቦርዱ መዘጋጀቱን ያወሱት ወ/ት ብርቱካን፤ የምርጫውን ፍትሃዊነት የሚያረጋግጡ ተግባራት ከወዲሁ ያከናውናሉ ብለዋል፡፡
በምርጫው ላይ ያላቸውን ተስፋና ስጋት በውይይቱ ላይ የገለፁት የኢዜማ መሪ ፕ/ር ብርሀኑ ነጋ በበኩላቸው፤ መጪው ምርጫ ነፃና ፍትሀዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ፓርቲያቸው የድርሻውን እንደሚወጣ ገልፀዋል፤ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የምታደርገው ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ለምስራቅ አፍሪካም በጣም ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ምርጫው ሁሉን አሳታፊ፣ ነፃና ፍትሀዊ እንዲሆንም ከመንግስት ብዙ እንደሚጠበቅ፣ ሰላምና መረጋጋት የማስፈን ጉዳይም ቅድሚያ ሰጥቶ እንዲሰራ ያስገነዘቡት ፕ/ር ብርሀኑ ነጋ፤ በተለይ የሃገሪቱን የምጣኔ ሀብት ሁኔታ የሚያሻሽሉ የፖሊሲ አማራጮች ላይ ፓርቲያቸው እንደሚያተኩር አስታውቀዋል።
መጪው ምርጫም ከዚህ ቀደም ከተካሄዱት ሁሉ የተሻለ ሆኖ ይጠናቀቃል የሚል ተስፋ መሰነቃቸውን አክለው ገልፀዋል፡፡
ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ የኢሶዴፓ ሊቀ መንበር ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ በበኩላቸው መጪውን ምርጫ ነፃ ፍታዊና ዴሞክራሲያዊ ከሆነ በመላው አፍሪካ ሰላምና ዲሞክራሲ መሰረት የሚጥል መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ይህ እንዲሆንም ዘንድ ምርጫ ቦርድን፣ የፍትህ ተቋማት፣ መንግስት፣ ገዢው ፓርቲ፣ ተቃዋሚዎችና ህዝቡ የየድርሻውን ሚና በስነ ምግባር ሊወጡ እንደሚገባ ያስገነዘቡት ፕ/ር በየነ፤ ምርጫው ለሀገሪቱ የዴሞክራሲ ሽግግር በእጅጉ ወሳኝ መሆኑን አስምረውበታል፡፡
ከምርጫው ማግስት ባሉ አምስት አመታትም፣ በዋናነት በሃገሪቱ ብሔራዊ መግባባትና እርቀ ሰላም በሚፈጠርበት ሁኔታ ላይ አተኩሮ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል- ፕ/ር በየነ፡፡  የፌደራል ጠ/አቃቢ ህግ  ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ በበኩላቸው፤ በፍትህ ስርአቱ በኩል ምርጫውን ፍትሃዊ ሊያደርጉ የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶች መከናወናቸውን በዝርዝር አስረድተዋል ከተደረጉ ዝግጅቶች መካከልም የምርጫ አቤቱታን የሚዳኙ ጽ/ቤቶች መቋቋማቸውን ጠቅሰዋል፡፡


Read 11243 times