Saturday, 06 February 2021 12:09

ለጠ/ሚኒስትሩ ድጋፍ በተደረጉ ሰልፈኞች 30 ሚ. ህዝብ ተሳትፏል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 የኦሮሚያ ብልጽግና የአብንን ስሞታ አጣጥሎታል

          ሰሞኑን በመላው የኦሮሚያ ከተሞች ለጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ድጋፍ በተደረጉ ሰላማዊ ሰልፎች ላይ በአጠቃላይ 30 ሚሊዮን ህዝብ መሳተፉን የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ አስታውቋል፡፡
የድጋፍ ሰልፉ  ከለውጡ በኋላ በጠ/ሚኒስትሩ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን እውቅና ለመስጠት ያለመ እንደሆነና ህብረተሰቡ በራሱ ተነሳሽነት ያደረገው መሆኑን የገለፁት የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ፤ በሰልፎቹ ላይ የተንፀባረቁ መልዕክቶች የብልጽግና ፓርቲ ሳይሆኑ የህዝቡ ነው ብለዋል፡፡
በ”ሰላማዊ ሰልፉ ላይ ስማችን ያላግባብ ተነስቷል የሚሉ አካላት ስማቸው የተነሳበት መንገድ በህዝቡ ዘንድ ያላቸው ቦታ የሚያንጸባርቅ ነው” ብለዋል - ሃላፊው፡፡
“በሰልፉ ፓርቲያችን ያለአግባብ ተወንጅሏል” ሲል አብን አቤቱታውን ለምርጫ ቦርድ ያቀረበ ሲሆን ፓርቲው ያቀረበውን አቤቱታ መርምሮ መግለጫ ያወጣው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ ብልጽግና ፓርቲ ከዚህ አካሄዱ እንዲቆጠብ አስጠንቅቋል፡፡
በህጋዊ መንገድ ተመዝግበው በምርጫ የሚሳተፉ የፖለቲካ ድርጅቶችን በሰልፉ ላይ ማውገዙ በምርጫ ዋዜማ እንደታዩ መጥፎ ምልክቶች የቆጠረው ምርጫ ቦርድ፤ ሌሎችም  እንዲታቀቡ አሳስቧል፡፡
ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ያወጣውን ማስጠንቀቂያ አስመልክቶም  የኦሮሚያ ብልጽግና ከቦርዱ ጋር እንደሚወያይበት አቶ ፍቃዱ ተሰማ አስታውቀዋል፡፡ በምርጫ ቦርድ መግለጫ እንደተመለከተው፣ በሰልፉ ላይ አብን፣ ባልደራስና ኦነግ፣ በአመጽ ተግባር በመሳተፍ ከቦርዱ ከተሰረዘው ጁንታ በሚል ከሚጠራው የህወሃት ፓርቲ ጋር አንድ በማድረግ፣ የኢትዮጵያ ጠላት ናቸው ብሎ በመፈረጅና ህገ ወጥ በማለት የስነ ምግባር ጥሰት ተፈፅሟል፡፡


Read 11692 times