Print this page
Sunday, 07 February 2021 00:00

የትኛው “ሰላማዊ ለውጥ” ይሻለናል? እንምረጥ!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(2 votes)

  1. ጥንታዊው ሰላማዊ ለውጥ፣ “የተሻረውም ንጉሥ ሖሩ!” የተሾመውም ንጉሥ ሖሩ!”… ”ሁላችሁም በያላችሁበት እርጉ፣ ተረጋጉ”!
    2. ዘመናዊው ሰላማዊ ለውጥ፣ “ኪም ሱ ንግ ሄ ደ። ኪ ም ኡ ን መጣ። እገሌም ተባለ፣ እከሌም ተባለ፣…ሁሌም ፓርቲያችን አለ!”…
    3. ስልጡን ሰላማዊ ለውጥ፣ “ይሄኛው ቢመረጥም፣ ያኛው ቢያሸንፍም፣ ስራቸው ግን አይለወጥም… ህግና ስርዓትን አክብረው ለማስከበር ፣ መሃላ
      ይፈጽማሉ”… “to preserve, product and defend…. ብለው”
                
          ሰላማዊና የተረጋጋ የመንግስት ለውጥ፣ ለነኢትዮጵያ፣ ገና የሩቅ ምኞት ነው፡፡ ከባድነቱ ግን ከሁሉም አገር ነው፡፡ ቢከብድና ባይሳካ እንኳ፣ የሰላምና የእርጋታ ምኞት ግን ሁሌም ይኖራል፡፡ ከነውጠኛ ዝንባሌ ጎን ለጎን፣ የሰላም ምኞትም፣ ከሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ጠፍቶ አያውቅም፡፡
“የሰላምና የእርጋታ ምኞትን” የሚገልፅ አንድ የጥንት አባባል አለ። አንዱ ንጉስ ሞቶ፣ በቦታው ሌላ ሰው ተተክቶ ሲነግሥ፣ አዲሱ ንጉሥ፣ አዋጅ ያወጣል። መርዶውንና የምስራቹን ያስነግራል።
“የሞትነውም እኛ፤ የነገሥነውም እኛ፤…
ሁልህም በያለህበት እርጋ”… ብሎ ያውጃል።
የአዋጁ መልዕክት ግልፅ ነው - አገር ሰላም እንደሆነ የሚገልፅ የማረጋጊያ መልዕክትን ያስተላልፋል። ነገር ግን፣ የማሳሰቢያ ትዕዛዝም ጭምር ይዟል፡፡ በአንድ በኩል “አትስጉ” ብሎ ያረጋጋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፣ “አታሰፍስፉ” ብሎ ያስጠነቅቃል፡፡ “ሁሉም ሰው በያለበት ይርጋ!” የሚል ማስፈራረያ ይዟል።
በአጭሩ፣ የአወጁ መልዕክት፣ “የፈረሰም የተፈጠረም መንግስት የለም” እንደማለት ነው።
“ነባሩ ስርዓት አልጠፋም። አዲስ ስርዓት አልመጣም” የሚል ትርጉም ይሰጣል።
የቀድሞው የበላይ አስተዳዳሪ በአዲስ ተተካ እንጂ፤…. የቀድሞው የፖሊስ አዛዥ በሌላ ተቀየረ እንጂ፣…. መንግስት አልተለወጠም። ህግና ስርዓቱ፣ መንግስትና ተቋማቱ፣ እንደወትሯቸው ፀንተው ይቀጥላሉ እንደማለት ነው። እናም፣ “ሁልህም በያለህበት እርጋ”… ይላል መልእክቱ።
የሞተውም የነገሰውም፣ የተሻረውም የተሾመውም፣ ያው ናቸው። እንዲህ አይነት አዋጅ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ፣ እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ በጣም የተለመደ አባባል ነበር።
ድሮ ጥንትማ፤ ከምሳሌያዊ አባባል ያለፈ ዋጋ ነበረው። “የተሻርነውም እኛ፣ የተሾምነውም እኛ” ብሎ የምር ለማሳመን የሚገለግል ስብከት ከመሆኑ የተነሳ፣ ግብፅ ጥንታዊ ገዢዎች፣ ተመሳሳይ የመጠሪያ ስም ይጠቀሙ ነበር። የነባሩ ንጉሥ ስም “ሖሩ” ነው። እሱ ሞቶ፣ ልጅየው ወይም ሌላ ሰው ሲነግስም፣ “ሖሩ” የሚል ስም ይወጣለታል። ቀጥሎ የሚመጣውም ንጉሥ፣ ስሙ ተቀይሮ፣ “ሖሩ” ተብሎ ይሰየማል፡፡ ምን አይነት ትርጉም እንደሚሰጥ አስቡት። በአንድ በኩል ንጉስ ተለውጧል፡፡ በሌላ በኩል ግን፣ የተለወጠ ነገር የለም - ሕግና ስርዓት አልተፋለሰም፤ መንግስት አልፈረሰም ይላል። ለምን? ያው፣…
“የሞተውም ሖሩ፣ የነገሰውም ሖሩ” ያስብላል - ነገሩ።
ይሄ የጥንቱ “ሰላማዊ የስልጣን ለውጥ” ነው። በዘመናዊ ገፅታውስ?
በአንድ በኩል፣ በበርካታ የአረብ አገራት እንደምናየው፣ ከንጉሥ ወደ ልዑል፣ ከአባት ወደ ልጅ የሚወረስ፣ የቀድሞው ዓይነት ስርዓት አለ። የንጉስ ዘመን ሲያበቃ፣ መንግስት አይፈርስም። በንጉስ የተሰየመ ወይም ከንጉስ የተወለደ አልጋ ወራሽ፣ ስልጣኑን ይረከባል፡፡ አገርም በሰላም፣ አዳሜም በእርጋታ ይቀጥላል ይላሉ።
በኩባ፣ ከፊደል ካስትሮ ወደ ወንድማቸው ወደ ራውል ካስትሮ የተከናወነው ሰላማዊ የስልጣን ለውጥንም መጥቀስ ይቻላል። የሰሜን ኮሪያም ተመሳሳይ ነው። ከአባት ኪም ኤል ሱንግ ወደ ልጅ፣ ከዚያም ወደ ልጅ ልጅ ወደ ኪም ጆንግ ኡን የመንግስት ስልጣን ሲሸጋገር፣ ሲወራረስ አይተናል።
የነኩባ “ስታይል”፣ እንደድሮው “በቤተሰብ ጥላ ስር” የሚከናወን ለውጥ ቢሆንም፤ የፓርቲ ገፅታንም ይቀላቅላል፡፡ የሣዑዲ አረቢያን እና የቻይናን ስታይሎች እንደመቀየጥ ቁጠሩት -የሰሜን ኮሪያ የስልጣን ሽግግር፡፡ ወይም የኳታርና የኢህአዴግ ስታይሎች ቅይጥ ነው ማለት ይቻላል - የኩባ የስልጣን ለውጥ።
የቻይናው ዓይነት የስልጣን ለውጥ፣ በአንድ ፓርቲ ጥላ ስር የሚካሄድ እንጂ፣ ከአባት ወደ ልጅ የሚተላለፍ አይደለም። ስልጣን የያዘ፣ አንድ ነባር የፓርቲ አለቃ፣ በሌላ ነባር አለቃ ተተክቶ ስልጣኑን ሲያስረክብ አይተናል። ግን፣ አገር አይፈርስም፤ መንግስትም አይለወጥም። ለምን? ያኛውም “ሖሩ” ፣ ይሄኛውም “ሖሩ” እንደማለት አይመስልም? ባለስልጣን ቢቀያየርም፣…. ፓርቲው አገርን ይገዛ ነበር፤ ፓርቲው አገርን እየገዛ ነው። “ሁልህም በያለህበት እርጋ!” የሚል ነው ነገሩ።
ከእነዚህ የተለየ ሌላ የስልጣን ሽግግርና እጅግ የተሻለ ሌላ የለውጥ ገፅታ አለ። በአሜሪካና በበርካታ የአውሮፓ አገራት የምናየው ሰላማዊ የፓርቲዎችና የባለስልጣናት ለውጥን ተመልከቱ።
በአሜሪካ ወይም በእንግሊዝ የሚካሄድ የስልጣን ሽግግር፣ በፓርቲ ወይም በቤተሰብ አጥር ውስጥ የተገደበ አይደለም። በምርጫ የተሸነፈ ፓርቲና ፖለቲከኛ ከስልጣን ተሽሮ፣ በምርጫ ያሸነፈ ቦታውን ይወስዳል። ተሿሚ ይሆናል፡፡
አንዱ ፓርቲ ተሸንፎ፣ ተቃራኒው ፓርቲ ስልጣን ይይዛል። አንዱ ፖለቲከኛ ወርዶ፣ ተቀናቃኙ ወደ ቤተ-መንግስት ይገባል።
እንዲያም ሆኖ፤ አገር አይበጠበጥም፣ ዜጋ አይሸበርም፡፡ ለምን? ባለስልጣን ቢለዋወጥም፣ ፓርቲ ቢቀያየርም፣ ነባር መንግስት አይፈርስም፣ አዲስ መንግስት አይመሰረትም። የእስከዛሬው ስርዓት አይሻርም፤ አዲስ ስርዓት አይፈጠርም። ነባሩ የመንግስት መዋቅር፣ ነባሩ ሕግና ስርዓት ፀንቶ ቀጥላል።
ታዲያ፣ ይህ “ሰላማዊና የተረጋጋ የስልጣን ለውጥ”፣ በፓርቲዎችና በፖለቲከኞች “መልካም ፈቃድ” አማካኝነት ብቻ የሚከናወን ጉዳይ አይደለም። የህግ ግዴታ ነው። “በምርጫ ማሸነፍና ስልጣን መያዝ” ማለት፣ ነባሩን የመንግስት መዋቅር በትኖ፣ ነባሩን ሕግና ስርዓት አፍርሶ፣ አዲስ የመፍጠርና የማዋቀር ስልጣንን አያስገኝም።
በተቃራኒው፤ ነባሩን ሕግና ስርዓት ማክበር፣ “የሁሉም ባለስልጣን ግዴታ” ነው። ምን ማክበር ብቻ? በምርጫ ያሸነፈና ስልጣን የያዘ ሰው በሙሉ፤ ከየትኛውም ፓርቲና ወረዳ ቢመጣ፣ “ነባሩን ህግና ስርዓት ማክበር” ብቻ ሳይሆን፣ “የማስከበር ግዴታም” አለበት።
ይህን የሕግ ሃላፊነት በስራ ለመተግበርም፣ ቃል መግባት ግዴታው ነው። ስልጣን ከመረከቡ በፊት፣ ቃለ-መሃላ ይፈፅማል።
በአሜሪካ፣…”To Preserve, Protect And Defend The Constitution Of The United States Of America” በማለት ቃል ይገባል።
ያለ ቃለ መሃላ፣ ስልጣን መያዝ አይቻልም - በምርጫ ቢያሸንፍም። በሌላ አነጋገር፣ ፓርቲው ወይም ፖለቲከኛው፣ በምርጫ ያሸነፈው፤ “ህግና ሥርዓትን አክብሮ ለማስከበር” እንጂ፤ “ነባሩን አፍርሶ፣ ያሻውን አይነት ስርዓት ለመፍጠር” አይደለም።
ነባሩ ባለስልጣንም፣ የአገሪቱን ሕግና ሥርዓት አክብሮ ለማስከበር ቃል ገብቶ ነበር - ሕጋዊ ግዴታው ነውና፡፡ አሁን፣ ተቀናቃኙ ፓርቲ አሸንፎ ሌላ ፖለቲከኛ ቤተ መንግስት ሲገባም፤ ቃል ይገባል - “የአገሪቱን ህግና ስርዓት አክብሮ ለማስከበር”፡፡ ይህን ህጋዊ ሃላፊነት እንዲተገብር ነው፣ ህጋዊ ስልጣን የሚይዘው፡፡
አዎ፤ ፓርቲዎቹና ፖለቲከኞቹ በአብዛኛው አይዋደዱም። አንዱ ፓርቲ ከሌላኛው፣ አንዱ ፖለቲከኛ ከሌላኛው ጋር፣ ተቀናቃኝና ተቃዋሚ ናቸው፡፡ አንዱ አሸንፎ ሌላው እየተሸነፈ፣ ስልጣን ላይ ይፈራረቃሉ፡፡ ባለስልጣናት ይለዋወጣሉ፡፡
ነባሩ ህግና ስርዓት ግን ይቀጥላል፡፡ የሚፈጠር ወይም የሚጠፋ ስርዓት የለም፡፡ የትኛውም ፓርቲ ወርዶ፣ የትኛውም ፓርቲ ስልጣን ቢጨብጥ፣ ሕግና ስርዓትን የመጠበቅ ግዴታ እንጂ፣ የማፍረስና የመለወጥ ፈቃድ አያገኝም፡፡
በዚህ መንገድ፣ በአሜሪካና በእንግሊዝ የምንመለከተው የለውጥ አይነት፣ በሕግና ሥርዓት የሚከናወን፣ ሰላማዊና የተረጋጋ የስልጣን ሽግግር ወይም የለውጥ አይነት ነው፡፡ ዘመናዊ ብቻ ሳይሆን፣ ስልጡን የለውጥ አይነት ነው፡፡ ነጻነትንና የህግ የበላይነትን ያጣመረ፣ በህግና በሥርዓት የሚከናወን፣ ሰላማዊና የተረጋጋ የመንግስት ለውጥ ነው፡፡
በእርግጥ፣ የምርጫው ውጤት ለተሸናፊው መርዶ፣ ለአሸናፊው ደግሞ የምስራች መሆኑ አይቀርም፡፡ ነገር ግን “ለውጥ” የለውም፡፡ ህግና ስርዓትን ለማስከበር፣ ያኛውም ቢያሸንፍ ያኛውም ቢያሸንፍ፣ ቃለ መሀላ ይፈጽማል፡፡….. አገርም ሰላም ይሆናል፡፡
“ያሸነፍነው እኛ፣ የተሸነፍነው እኛ፣ ሁልህም  በያለህበት እርጋ፣”…. እንደማለት ይመስላል፡፡ አዎ፤ ኢትዮጵያን ለመሳሰሉ አገራት፣ ነፃነትንና የህግ የበላይነትን የሚያዋህድ፣ ሕግና ስርዓትን የሚያጸና፣ ሰላማዊና የተረጋጋ የስልጣን ሽግግር፣… ”ለምኞትም” ሩቅ ነው፡፡ አሁንማ፣ ለአሜሪካና ለነ አውሮፓም፣ እየከበዳቸው ነው፡፡
እነኢትዮጵያ ግን፣… ገና ከአጠገቡ የሉም። ሰላምንና እርጋታን የሚሰጥ “ስልጡን የሆነ፣ የነፃነትና የህግ የበላይነት ሥርዓት፣ ገና ባይተዋራችን ነው፡፡ ገና በወጉ መች እናስብበታለን! ራሳችሁ ፍረዱ፡፡ ለነፃነትና ለህግ የበላይነት ፅኑ እምነት የያዘ ፖለቲከኛ ስንቱ ነው? ይሄ ይቅር፡፡ ግን ስንቱ ነው፣ ለህግና ስርዓት ደንታ ያለው? አብዛኛውን ባለስልጣን እዩ፡፡ “በህግ ለመግዛት” እንጂ፣ “በህግ ለመገዛት” አይሻም።
መቶ ምናምን ፓርቲ ሁሉ፣ በምርጫ ካሸነፍኩ፣ ሕግና ስርዓቱን አፍርሼ አዲስ የራሴን ስርዓት እገነባለሁ እያለ ይፎክራል። ህገመንግስትን እቀይራለሁ፤ የመንግስትን አወቃቀር ከፌደራል እስከ ክልል፣ ያንን አጥፍቼ፣ አዲስ አምጥቼ…. እያለ ይፎክራል፡፡ አብዮት እፈጥራለሁ እያለ ቃል ይገባል፡፡
ይሄ፣ ሰላምንና እርጋታን የሚሰጥ የለውጥ አይነት አይደለም፡፡ ደግሞም አይዘልቅም፡፡
የምርጫ አሰራር፣ ከአንድ ምርጫ በላይ እድሜ የሚኖረው፣… “አከብረዋለሁ፤ አስከብረዋለሁ” ብለው ቃል የሚገቡ ፖለቲከኞች ሲበረክቱና፣ ቃል የሚገቡለት ስልጡን ስርዓት ወይም ደህና መነሻ ስርዓት ሲኖር ብቻ ነው፡፡


Read 10799 times