Monday, 08 February 2021 00:00

በ2020 የአለማቀፍ ቱሪስቶች ቁጥር በአንድ ቢሊዮን ቀንሷል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

      የአለማችን ቱሪዝም ዘርፍ ባለፈው የፈረንጆች አመት 2020 በታሪክ የከፋውን ቀውስ ማስተናገዱንና የአለማቀፍ ቱሪስቶች ቁጥር አምና ከነበረበት ከ74 በመቶ ወይም በአንድ ቢሊዮን መቀነሱን የአለም የቱሪዝም ድርጅት አስታውቋል፡፡
ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች ከተጣሉ በርካታ የጉዞ እና የእንቅስቃሴ ገደቦች እንዲሁም ከቱሪዝም ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ ጋር በተያያዘ የቱሪዝም መስኩ ያጣው ገቢ 1.3 ትሪሊዮን ዶላር እንደሚደርስም ድርጅቱ ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል፡፡
ከአለማች በአመቱ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የቱሪስቶች ቁጥር ክፉኛ የቀነሰባቸው የእስያና ፓሲፊክ አገራት መሆናቸውን የሚያሳየው የድርጅቱ ሪፖርት፣ በአገራቱ የቱሪስቶች ቁጥር ከአምናው በ84 በመቶ ወይም በ300 ሚሊዮን መቀነሱን እንዲሁም በመካከለኛው ምስራቅና አፍሪካ አገራት በ75 በመቶ መቀነሱንም ያብራራል፡፡
በቱሪዝሙ መስክ የተፈጠረው ቀውስ እስከ 120 ሚሊዮን የሚደርሱ በዘርፉ የተሰማሩ ሰዎችን የስራ ዕድል አደጋ ውስጥ መጣሉን የጠቆመው ድርጅቱ፣ በቅርቡ ባደረገው ጥናት ከተሳተፉ የመስኩ ባለሙያዎች መካከል ግማሽ ያህሉ ቱሪዝሙ በመጪው አመት የተሻለ አፈጻጸም ያስመዘግባል ብለው እንደሚጠብቁ መግለጻቸውንም አስረድቷል፡፡
አለማቀፉ የንግድ ጉዞ ማህበር በበኩሉ በፈረንጆች አመት 2020 ለንግድ ጉዞ ወጪ የተደረገው ገንዘብ ካለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር የ52 በመቶ ወይም የ694 ቢሊዮን ዶላር ቅናሽ ማሳየቱን ከሰሞኑ ባወጣው መረጃ መግለጹን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የንግድ ጉዞ ወጪ በተያዘው የፈረንጆች አመት 2021 ከአምናው ጋር ሲነጻጸር በ21 በመቶ ያህል እድገት ያሳያል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆመው ዘገባው፣ የዘርፉ ወጪ ከኮሮና ወረርሽኝ በፊት ወደነበረው 1.43 ትሪሊዮን ዶላር ለመመለስ ግን ሶስት አመታት ያህል ሊወስድበት አንደሚችል መነገሩንም አክሎ ገልጧል፡፡


Read 2554 times