Tuesday, 09 February 2021 00:00

ቮልስዋገን የሽያጭ ደረጃውን በቶዮታ መነጠቁ ተዘገበ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

      - ቶዮታ ባለፈው አመት 9.53 ሚሊዮን መኪኖችን ሽጧል
        - አፕል የአመቱ የአለማችን እጅግ ስመጥር ኩባንያ ሆኗል

          የጃፓኑ ቶዮታ መኪና አምራች ኩባንያ በ2020 የፈረንጆች አመት ብዛት ያላቸው መኪኖችን በመሸጥ በአለማችን ቀዳሚው ኩባንያ መሆኑን የዘገበው ብሉምበርግ፣ ኩባንያው በአመቱ 9.53 ሚሊዮን የተለያዩ ምርቶቹን ለመሸጥ መቻሉን አመልክቷል፡፡
ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ አለማቀፉ የአመቱ የመኪኖች ሽያጭ በ2019 ከነበረው በ14 በመቶ ያህል ቅናሽ ማሳየቱን ያስታወሰው ዘገባው፣ የቶዮታ ሽያጭም በ11 በመቶ ቢቀንስም በሽያጭ ቀዳሚውን ደረጃ ከመያዝ የሚያግደው ኩባንያ አለመገኘቱን ገልጧል፡፡
ላለፉት አምስት አመታት በሽያጭ ሲመራ የነበረው የጀርመኑ የመኪና አምራች ኩባንያ ቮልስዋገን በአመቱ 9.31 ሚሊዮን መኪኖችን ብቻ በመሸጡ ዘንድሮ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ዝቅ ሊል መገደዱንም አክሎ ገልጧል፡፡
በሌላ የቢዝነስ ዘገባ ደግሞ፣ በአለም ዙሪያ የሚገኙ ታላላቅ ኩባንያዎችን የእውቅናና የተደናቂነት ደረጃ እየገመገመ በየአመቱ ይፋ የሚያደርገው ፎርቹን መጽሔት ከሰሞኑም የ2020 የፈረንጆች አመት ሪፖርቱን ያወጣ ሲሆን፣ ላለፉት 13 ተከታታይ አመታት በ1ኛ ደረጃ ላይ ሆኖ የዘለቀው የአሜሪካው የቴክኖሎጂ ኩባንያ አፕል ዘንድሮም የአለማችን እጅግ ስመጥር ኩባንያ ሆኗል፡፡
ፎርቹን የሃብት መጠን፣ የስራ አመራር ብቃት፣ ማህበራዊ ሃላፊነትን የመወጣት አቅምና ዝና ጨምሮ 9 መስፈርቶችን ተጠቅሞ የኩባንያዎችን ሁኔታ በመገምገም ባወጣው አመታዊ ሪፖርቱ፤ ሌላኛው የአሜሪካ ኩባንያ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ፣ ማይክሮሶፍት በበኩሉ የአመቱ ሶስተኛው ስመጥር ኩባንያ ለመሆን መብቃቱን ሪፖርቱ ያሳያል፡፡
ዋልት ዲዝኒ፣ ስታርባክስ፣ ቤክሻየር ሃታዌ፣ አልፋቤት፣ ጂፒሞርጋን ቼዝ፣ ኔትፍሊክስ እና ኮስቶኮ ሆልሴል እንደቅደም ተከተላቸው ከአራተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ የያዙ የአለማችን ኩባንያዎች መሆናቸውም ተነግሯል፡፡
ፎርቹን መጽሔት በአመቱ ሪፖርቱ ውስጥ ያካተታቸው ኩባንያዎች ገቢያቸው ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሆኑትን እንደሆነ የጠቆመ ሲሆን፣ ኩባንያዎቹ ቴክኖሎጂን ጨምሮ በ52 የተለያዩ የንግድ መስኮች የተሰማሩ እንደሆኑም አመልክቷል፡፡


Read 897 times