Saturday, 13 February 2021 11:16

በትግራይ በሴቶችና ህፃናት ላይ ኢ-ሰብአዊ ተግባር መፈጸሙን ኢሰመኮ አስታወቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

      በሁለት ወር ውስጥ 108 ሴቶች ፆታዊ ጥቃት ተፈፅሞባቸዋል
                             
                 በትግራይ ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ ከሆስፒታሎች  በተገኘ መረጃ መሰረት፣ 108 ሴቶች የአስገድዶ መድፈር ወንጀል
እንደተፈጸመባቸው ያስታወቀው የኢትዮጵያ  ሰብአዊ  መብቶች ኮሚሽን በክልሉ የመሰረተ ልማት፣ የማህበራዊና አስተዳደራዊ አገልግሎቶች
በአፋጣኝ የመመለሱ ተግባር ልዩ ትኩረት ያስፈልገዋል ብሏል።
ኮሚሽኑ ከጥር 2 እስከ 15 በመቀሌ ከተማና ደቡባዊ የትግራይ ዞን አላማጣ፣ መሆኒ እና ኩኩፍቶ ከተሞች ምርመራ ማድረጉን የጠቆመ ሲሆን
በዚህ ምርመራውም ከመቀሌ፣ ከአይደር፣ አዴግራትና ውቅሮ ሆስፒታሎች በተገኘ መረጃ መሰረት፤ 108 ሴቶች ላይ የአስገድዶ መደፈር ጥቃት
ስለመፈጸሙ ለማወቅ ችሏል።
የምርመራ ቡድኑ በተለይ በአይደር ሆስፒታል በተገኘበት ወቅት ተኝቶ መታከሚያ ክፍል ከነበሩ 20  ከፍተኛ የአእምሮ ጭንቀትና ድንጋጤ
ታካሚ ህፃናት ውስጥ 16 ያህሉ በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው እንደሆኑ አረጋግጧል። ከህፃናቱ መካከል እጃቸውን፣ እግራቸውንና
አይናቸውን ጨምሮ የአካል ክፍሎቻቸውን ያጡ ወይም የተለያየ አይነት ጉዳት የደረሰባቸው እንደሚገኙ አስታውቋል።
ህፃናቱ ላይ ለደረሰው መሰል ጉዳቶች አንዱ ምክንያት በመሬት ውስጥ የተቀበሩና ሜዳ ላይ የተጣሉ ፈንጂዎች መሆናቸውን ጠቁሟል- ኢሰመኮ።
 በክልሉ በዜጎች ላይ የደረሰው እጅግ አሳዛኝና አሳሳቢ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ከዚህ የበለጠ እንዳይሰፉ ልዩ ትኩረት እንደሚያሻውም ኮሚሽኑ አሳስቧል።
በብዙ የትግራይ አካባቢዎች አሁንም የትራስፖርት፣ባንክ፣ ስልክ፣ መብራት አገልግሎቶች  አለመመለሳቸውን፤ በሌላ በኩል የምግብ ፣
መድሃኒትና ሌሎች መሰረታዊ አቅርቦቶች ዝውውር አስቸጋሪ ሁኔታ እየገጠመው መሆኑ ሰብአዊ ቀውሱን እንዳያባብሰው ስጋት እንዳለውም ኮሚሽኑ አስገንዝቧል።
የምግብ፣ህክምና፣መድሃኒት እንዲሁም መጠለያና ሌሎች መሰረታዊ አቅርቦቶች አለመሟላትን ለመቅረፍ መንግስት የተፋጠኑ እርምጃዎችን
እንዲወስድም ኢሠመኮ አሳስቧል።


Read 13188 times