Print this page
Saturday, 13 February 2021 11:40

የወር አበባ (Menstruation) ሕመሞች እንዲሰሙ ምክንያት ይሆናል፡፡

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

     እኔ በጣም ከፍተኛ የሆነ የእራስ ምታት ወይንም ሕመም አለብኝ በማለት ችግርዋን ለዚህ አምድ ያዋየችው በእድሜዋ የ14/አመት የሆነች ታዳጊ ናት፡፡ ታሪኩን ስታስረዳም ‹‹ …የወር አበባዬ (Menstruation) ሊመጣ አንድ ቀን ሲቀረው ጀምሮ እስከ ሶስተኛው ቀን ድረስ በጣም እራሴን ያምመኛል፡፡ ሰው ማናገር ብርሀን ማየት ሁሉ ያስጠላኛል፡፡ በዚያ ወቅት ትምህርት ቤት መሄድም በጣም እቸገራለሁ፡፡ ትምህርት ቤት ብሄድም እንኩዋን እንኩዋንስ ልማር ቀርቶ መፈጠሬን ሁሉ የምጠላበት ደረጃ ላይ ያደርሰኛል፡፡ ለቤተሰቦቼ ሳማክርም የራስ ሕመሙ አይ ነት ሚግሬይን የሚባል ነው ይሉኛል፡፡ እኔ ለምን ይህ ችግር ይደርስብኛል ብዬ ለመጠየቅ ወደ እናንተ ስልክ ደውያለሁ ነበር ያለችን ፡፡ ታዳጊዋ ስምዋን ለመናገር ፈቃደኛ አልነበረችም፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ችግር የእስዋ ብቻ ተደርጎ የማይታይ ሰለሚሆን ለዚህ እትም Womens- health.govን እና ዶ/ር አበበ ፈጠነ ቀደም ሲል የሰጡንን መረጃ ምንጫችን አድርገናል፡፡
በምንጭነት የጠቀስነው ድረገጽ ከወር አበባ Menstruation ጋር በተያያዘ የሚደርሱ ሕመሞችን በሚመለከት ብዙ ቁምነገሮችን ለንባብ አስፍሮአል፡፡ ጠያቂያችን የተቸገረችበትን የጤና ሁኔታ ወደአማርኛ መልሰነዋል፡፡
የወር አበባና የእራስ ህመም (Menstrual migraine)
ድረገጹ እንደሚያስነብበው በወር አበባ ወቅት ከ10 ሴቶች አራት ያህሉ በህይወት ዘመናቸው የእራስ ሕመም ይገጥማቸዋል፡፡ የእራስ ሕመም ከሚገጥማቸው መካከል ግማሽ ያህሉ የሚ መሰክሩት ህመሙ የሚከሰተው የወር አበባ በሚመጣባቸው ወቅት እንደሆነ ነው፡፡ በእርግጥ ተመራማ ሪዎች ምክንያቱ ይህ ነው ለማለት አልደፈሩም፡፡ ቢሆንም ግን ሳይንሳዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ ይህ ህመም የሚከሰተው ከጭንቀት፤ ግራ ከመጋባት እና ከመሳሰሉት ጋር ተያያዥ በሆነ መንገድ ሊሆን ይች ላል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የወር አበባ ኡደትን የሚቆጣ ጠሩት እጢዎች ከእራስ ሕመም ጋር የሚያያዘውን በጭንቅላት ውስጥ ያለውን ኬሚካል ሊረብሹት እንደሚችሉ ይገልጻሉ ፡፡
ይህ ችግር የገጠማቸው ሴቶች ሐኪማቸው ዘንድ ቀርበው መፍትሔ መፈለግ ይገባቸዋል፡፡ ሕመሙ እንዳለባቸው እና እንደጀመራቸው እርግጠኛ ከሆኑም የሚከተሉትን ምልክቶች ልብ በማለት ለሐኪማቸው ማስረዳት ይጠበቅባቸዋል፡፡
የሚሰማቸው የእራስ ሕመም ለውጥ ከአለው፤
ቀደም ሲል የተሰጣቸው መድሀኒት አሁን መስራት ከአልቻለ፤
መድሀኒቱን በመውሰድ ምክንያት የተከሰተ የጎንዮሽ ጉዳት ከአለ፤
ሆርሞን ያለባቸውን የእርግዝና መከላከያ ኪኒኖች የሚወስዱ ከሆነና አንዳንድ እርግጠኛ ያልሆኑ ብርሀንማ ወይንም ነጠብጣባማ የሆኑ እይታዎች የሚታዩአቸው ከሆነ፤
በመተኛት ጊዜ የእራስ ሕመሙ የሚብስ ከሆነ ወደ ሕምና መቅረብ ይገባል፡፡
በእርግጥ Migraine የተሰኘው የራስ ሕመም የማይድን ሕመም ነው፡፡ ቢሆንም ግን የህክምና ባለሙያዎች በሚሰጡት እርዳታ የተሻለ ማድረግ ይቻላል፡፡ ይህ Migraine የተባለው የራስ ሕመም በሚከሰትበት ጊዜ መረዳት የሚያስፈልገው ሕመሙን ለመከሰቱ ምክንያቱ ምን እን ደሆነ ሲሆን እነዚህን ምክንያት የሚሆኑ ነገሮችን እቀድሞ ማስወገድ መቻል ሌላው በሕመሙ ላለመሰቃየት የሚጠቅም ዘዴ ነው፡፡
ከላይ ከተጠቀሰው ወጣ በማለት አጠቃላይ ሁኔታውን ስንመለከት ከአሁን ቀደም ለዚህ አምድ መልስ የሰጡት የማህጸንና ጽንስ ሕክምና እስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር አበበ ፈጠነ የሚከተ ለውን ማብራሪያ ነበር የሰጡት፡፡
የወር አበባ ሲመጣ ያለው ህመም ዴስሜኖሪያ (dysmenorrheal) ሲባል የህመሙ መንስኤም በሁለት ይከፈላል፡፡የመጀመሪያው (primary) የሚባለው የህመም መንስኤ ለምን ህመም እንደሚኖር ምክንያቱ በትክክል ባይታወቅም የፕሮሰታግላንዲን (Prostaglandin) መብዛት ሊሆን ይችላል የሚሉ መላምቶች ግን አሉት ፡፡የሁለተኛው (secondary) የህመም መንስኤ ግን ምክንያቶች አሉት ለምሳሌ የማህጸን እጢ ካለ እንዲሁም  ኢንዶሜትሪዮሲስ (Endometriosis) የሚባል ማህጸን አካባቢ የሚኖር ችግር ካለ እና ሌሎች ችግሮች ሲፈጠሩ በወር አበባ ጊዜ ህመም ይፈጠራል፡፡የመጀመሪያው ወይም ደግሞ ምክንያቱ ለማይታወቅ ለወር አበባ ጊዜ ህመም መፍትሄው የሚባለው ማግባት ብቻ ሳይሆን መውለድም ጭምር ነው ፡፡የዚህ ምክንያትም  የህመሞቹ መንስኤ ከማህጸን መጥበብ ጋር ይያዛል ተብሎ ስለሚገመት  አንዲት ሴት ልጅ ከወለደች በኋላ  እጅግ ታላቅ በሆነ መልኩ የህመሙ መጠን ይቀንሳል፡፡የህመሙ መንስኤ የሚታወቅ ከሆነ  ለምሳሌ እንደ ኢንዶሜትሪዮሲስ (Endometriosis) ወይም ማዮማ የሚባሉ የማህጸን ዕጢ እና የመሳሰሉት ምክንያቶች  ከሆኑ ግን  ህመሙን ያመጣው ምክንያት እስ ካልተወገደ ድረስ ብታገባም ባታገባም ህመሙ ይቀጥላል፡፡
ምንጭ ያደረግነው Womenshealth.gov እንደሚገልጸው (Menstruation) የወር አበባ ጊዜውን እና ፍሰቱን በተገቢው ሁኔታ ጠብቆ የሚመጣ እና የሚሄድ ከሆነ ይህ ጤናማነትን የሚያሳይ ነው፡፡ አንዲት ሴት እርግዝና ካላት ወይም ጡት የምታጠባ ከሆነ እንዲሁም የወር አበባ መቋረጫ ጊዜ postmenopausal እየደረሰ ከሆነ እና በተለያዩ ሕመሞች ምክንያት በሚሰጡ አገልግሎጾች ምክንያት የወር አበባው ይቋረጣል፡፡ ከዚህ ውጭ የወር አበባ ጊዜውን ጠብቆ የማይመጣ ከሆነ እና ፍሰቱም በተገቢው መጠን ካልሆነ ሕመምን ሊያስከትል ይችላል፡፡ የወር አበባ ፍሰት ከመጠኑ ያለፈ ከሆነ ሕመም መኖሩን የሚያሳይ ሊሆን ይችላል፡፡ የወር አበባ በዚህ መንገድ ጊዜውንና ፍሰቱን በትክክል ጠብቆ የማይመጣ ከሆነ እርግዝና እንዳይከሰት ምክንያት ሊሆንም ይችላል፡፡
የወር አበባ የፍሰት መጠኑ ትንሽ ነው የሚባልባቸው አጋጣሚዎች በብዙ ሴቶች ዘንድ ይስተዋላል፡፡ ይህንን በተመለከተም ዶ/ር አበበ እንደገለጹት የወር አበባው ፍሰት ከ10 ሚሊ ሊትር የሚያንስ ከሆነ የወር አበባ ትንሽ ነው እንላለን ፡፡ይህ ሁኔታ እንዲከሰት የሚያደርጉ የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፡፡ አልፎ አልፎ የውስጠኛው የማህጸን ግድግዳ የሌላቸው ሴቶች አሉ፡፡ በመሆኑም እንደዚህ አይነት ሴቶች ላይ የወር አበባ በጭራሽ ላይኖር ይችላል፡፡መጠኑ የሚቀንሰው የማህጸን የታችኛው ክፍል ማለትም የማህጸን በር (cervix) የመዘጋት ሁኔታ ካለ ወይንም የማህጸን የውስጠኛው ግድግዳ በውርጃ ጊዜ ሲጠረግ የተጎዳ ከሆነ እና በተለያዩ ኢንፌክሽኖች የወር አበባ ማነስ ሊኖር ይችላል፡፡
ባጠቃላይም በወር አበባ ጊዜ ለሚኖረው ሕመም የመጀመሪያው ምክንያት (estrogen) የሚባለው ሆርሞን ያዘጋጀው የማህጸን ግድግዳ በ ፕሮጄስተሮን  (progesterone) ይደገፋል፡፡ በተመሳሳይ ጊዜ ደግሞ እንደ ፕሮስታግላንዲን  (prostaglandin) አይነት የታለያዩ ቅመሞች ማህጸን ወስጥ ይዘጋጃሉ፡፡እንዲሁም እርግዝና ካልተካሄደ ወደ ወሩ መጨረሻ ላይ ፕሮጄስተሮን (progesterone) እና ኤስትሮጂን (estrogen) የሚባሉ ቅመሞች ዝቅ ይላሉ፡፡ በዚህን ጊዜ አዲስ የተሰራው የማህጸን ግድግዳ ላይ ውስጡ ያለው የደም ዝውውር ያንሳል፡፡ የደም ዝውውር አነሰ ማለት ውስጡ ያለው ነገር እየሞተ ነው ማለት ነው፡፡የማህጸን የውስጥ ግድግዳው የሞተ እና እየሞተ ያለ ከሆነ ህመም ሊሰማ ይችላል፡፡ ሁለተኛው እና ዋናው የህመም መፈጠር ምክንያት ደግሞ ፕሮስታግላንዲን (prostaglandin) የሚባለው ቅመም ማህጸን ውስጥ ያለውን ስፓይራል (spiral) የሚባለውን የደም ስር እንዲኮማተር በማድረጉ ከባድ የሆነ ህመም እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ይህን ሲያደርግ አዲስ የተሰራው ግድግዳ ላይ የደም ዝውውር እንዲቀንስ በማድረጉ  ለ ኤስኪሚክ (ischemic) ወይም ለምግብ እጥረት በማጋለጥ  ህመም እንዲሰማ ያደርጋል፡፡    ሶስተኛው የህመም ምክንያት ደግሞ ፕሮስታግላንዲን (prostaglandin) የሚባለው ንጥረ ነገር የማህጸን ግድግዳ እንዲኮማተር በማድረጉ ነው፡፡እንዲኮማተር የሚያደርግበት አንደኛው ምክንያት  የደም ዝውውሩ እንዲቀንስ እና ሴቲቱ  ብዙ እንዳትደማ ለማድረግ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ   በምግብ እጥረት የተነሳ ከውስጥ የሞተው ክፍል  ከማህጸን ውስጥ እንዲወጣ የግድ ማህጸን መጨመቅ ስላለበት  የመጭመቅ ሂደቱ ህመም እንዲሰማ በማድረጉ ነው፡፡ ስለዚህ ባጠቃላይ በወር አበባ ጊዜ ሶስት መሰረታዊ ህመሞች አሉ ማለት ነው፡፡ በምግብ እጥረት ፣አየር (oxygen) እጥረት እና ሶስተኛው ደግሞ ማህጸኑ እራሱ ስለሚኮማተር በእነዚህ ምክንያቶች ህመም ይከስታል የማህጸንና የጽንስ ሕክምና እስፔሻሊስቱ ዶ/ር አበበ ፈጠነ እንደሰጡት ማብራሪያ እና ከ Womenshealth.gov እንዳገኘነው መረጃ፡፡

Read 15461 times