Print this page
Saturday, 20 February 2021 00:00

የነዳጅ ዱቤ ሽያጭን ማስቀረት በነዳጅ አቅርቦቱ ላይ አደጋ ያስከትላል ተባለ

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(0 votes)

 መንግስት የነዳጅ ዱቤ ሽያጭን ለማስቀረት ያወጣው አዲስ አሰራር፤ በነዳጅ አቅርቦቱ ላይ ከፍተኛ ጫናን እንደሚያሳድር ተገለጸ። አዲሱ አሰራር ከመጋቢት 1 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ መደረግ ይጀምራል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ነዳጅ አዳዮች ማህበር ትናንት በሰጠው መግለጫ፣ መንግስት ከነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎች ጋር ይፈጽም የነበረውን የዱቤ ንግድ የሚያስቀር አሰራር ከመጋቢት 1 አንስቶ ተግባራዊ መደረግ ይጀምራል። የዚህ አሰራር ተግባራዊ መደረግ ደግሞ ነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎች፣ ለነዳጅ አዳይ ማደያዎች የሚሰጡትን የዱቤ ንግድ የሚያስቀርና በነዳጅ አቅርቦቱ ላይ ከፍተኛ ችግር የሚፈጥር ነው ተብሏል።
የነዳጅ አዳይ ማህበር ቦርድ አባል የሆኑት አቶ ኤፍሬም ተስፋዬ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ መንግስታዊው የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት፣ ከነዳጅ አከፋፋይ ድርጅቶች ጋር ባለው የዱቤ ውል፣ ነዳጅ ለኩባንያዎቹ የሚያቀርብ ሲሆን ኩባንያዎቹ በዱቤ እየሸጡ ገንዘባቸውን ነዳጁ ከተሸጠ በኋላ የሚወስዱበት አሰራር ለረዥም ጊዜያት ተግባራዊ ሲደረግ ቆይቷል።
አሁን የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ለደንበኞቹ ነዳጁን በእጅ በእጅ ክፍያ ሊሸጥ መሆኑን አስመልክቶ ያወጣው አዲስ አሰራር፣ ነዳጅ አዳዮቹ ነዳጁን በዱቤ እየወሰድን ለተጠቃሚው የምናደርስበትን አሰራር የሚያስቀር በመሆኑ፣ እኛንም ሆነ አቅርቦቱን ለከፍተኛ ችግር የሚያጋልጥ ነው ብለዋል። ከዚህ ቀደም ከነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎች የምናገኘውን ነዳጅ በዱቤ አራግፈን ለተጠቃሚው ከሸጥን በኋላ ገንዘቡን ለኩባንያዎቹ እንከፍል ነበር ያሉት አቶ ኤፍሬም፤ ይህ አሰራር እንዲቀየርና ማደያዎች ነዳጁን ከአከፋፋዮቹ በእጅ በጅ ክፍያ እንዲረከቡ የሚያደርግ አሰራር ተግባራዊ ለማድረግ መሞከሩ በእጅጉ የሚጎዳን አሰራር ነው ብለዋል።
የነዳጅ ማከፋፈል ስራ በባህሪው ብዙ ትርፍ የሚገኝበት ስራ አይደለም ያሉት አቶ ኤፍሬም፤ በአሁኑ ወቅት ከአንድ ሊትር ነዳጅ የምናገኘው የሃያ ሶስት ሳንቲም ትርፍ ወደ ሰማንያ ሳንቲም ከፍ ሊደረግ ይገባዋልም ብለዋል።
ነዳጅን በእጅ በጅ ክፍያ ተረክቦ ለተጠቃሚው ማዳረስ ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቅ ስራ መሆኑን የገለጹት አቶ ኤፍሬም፤ ይህንን ለማድረግ የሚያስችል ካፒታል የሌለን በመሆኑና አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ባንኮች ብድር ሊሰጡን ስለማይችሉ የነዳጅ አቅርቦቱ አደጋ ላይ መውደቁ አይቀሬ ጉዳይ ነው ብለዋል። ይህ ከመሆኑ በፊት ግን መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ሊያነጋግረን ይገባል የሚል ሃሳብ ሰንዝረዋል።
ጉዳዩን አስመልክቶ ለተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት ደብዳቤ መፃፋቸውን የተናገሩት አቶ ኤፍሬም፤ አንዳቸውም ግን ምላሽ ሊሰጡን ፍቃደኛ አልሆኑም ብለዋል።
ስለ ጉዳዩ ማብራሪያ ለመጠየቅና ነዳጅ አዳይ ማህበሩ ባነሳው ቅሬታ ላይ የመንግስትን ምላሽ ለማካተት ያደረግነው መከራ  አልተሳካም። የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ታደሰ ኃ/ማርያም፤ በእጅ ስልካቸው ላይ በተደጋጋሚ ብንደውልም፣ በፅሑፍ መልዕክት ብናስቀምጥም ምላሽ ሳይሰጡን ቀርተዋል።

Read 919 times