Saturday, 20 February 2021 00:00

ጠ/ሚኒስትሩ ለትግራይ የእርዳታ ድጋፍ ጥሪ አቀረቡ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 ከትናንት በስቲያ ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች ጋር በጽ/ቤታቸው የተወያዩት ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ በክልሉ ዘላቂ ሰላም ለማምጣትና ትግራይን  መልሶ ለመገንባት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከክልሉ አመራሮች ጋር በትግራይ መልሶ ግንባታ፣ በሰብአዊ መብት ጥብቃና ለዜጎች በሚቀርብ የምግብና ሌሎች ድጋፎች ዙሪያ ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን ያስታወቁት ጠ/ሚኒስተሩ፤ ትግራይን መልሰን እንገንባ” ሲሉ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የአንድነት የድጋፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በክልል ደረጃም እያንዳንዱ ክልል የተደራጀ ድጋፍ እንዲያሰባስብ የጠየቁት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ከዚህ ቀደም ከእያንዳንዱ ክልል ቃል የተገቡ የተሽከርካሪ፣ ልዩ ልዩ ቁሳቁሶች፣ ለአርሶ አደርች የሚያቀርቡ የሰብል ዘሮችና የእርሻ መገልገያ መሳሪያዎች፣አምቡላንስ፣መድሃኒት እንዲሁም የገንዘብ ድጋፍ በጥቂት ቀናት ውስጥ እንዲሰባሰብ ጠይቀዋል፡፡
በሃገራዊ አንድነቱ የድጋፍ ማሰባሰብ ሂደት ከሁሉም የክልል ርዕሠ መስተዳደሮች ጋር በበይነ መረብ አማካይነት መምከራቸውንና በጎ ተነሳሽነትና ምላሽ መገኘቱንም ነው ጠ/ሚኒስትሩ በፌስ ቡክ ገፃቸው ያሰፈሩት፡፡
ለሚሰባሰበው ድጋፍም አርአያ ለመሆን ጠ/ሚኒስትሩ የአንድ ወር ደሞዛቸውን፣ከመደመር መፅሃፍ ሽያጭ የተገኘ 2 መቶ ሺ ብር እንዲሁም በጠቅላይ ሚኒስተር ጽ/ቤት በኩል ሶስት የውሃ ማመላለሻ ባለታንከር መኪናዎች ማዋጣታቸውን አስታውቀዋል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው ሁሉም ሰው ትግራይን መልሶ በመገንባት የአንድነት ንቅናቄ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡


Read 12849 times