Sunday, 21 February 2021 17:04

ፓርቲዎች አዳዲስ የቅስቀሳ ዘዴዎችን እየተከተሉ ነውየኢትዮጵያ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

 የሙዚቃ ኮንሰርቶች -- ነፃ ትራንስፖርት የአደባባይ ትዕይንቶች----

            በዘንድሮ በምርጫ የሚሳተፉ የፖለቲካ ድርጅቶች አዳዲስ የምርጫ ቅስቀሳና ራስን የማስተዋወቂያ መንገዶችን እየተከተሉ ነው።
የሚበራ አምፖልን ምልክቱ ያደረገውና ሰሞኑን በጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ አማካኝነት የምርጫ መወዳደሪያ ምልክቱንና ማኒፌስቶውን ያስተዋወቀው ብልጽግና ፓርቲ፤  ሰዎች በነፃ የሚታደሙባቸው የሙዚቃ ኮንሰርቶች ማቅረብ ጀምሯል። ብልጽግና በዚሁ የምርጫ ቅስቀሳ፤ መራጮቹን ለማነቃቃትና ራሱን ለማስተዋወቅ የሙዚቃ ኮንሰርቶችን እንደ አንድ አማራጭ መጠቀሙን ይቀጥላል፡፡ ጠ/ሚኒስትሩም በዘንድሮ የምረጡኝ ቅስቀሳ በተለያዩ መድረኮች በመገኘት በቀጥታ ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ብልጽግና የምረጡኝ ቅስቀሳው አካል የሆነውን  የሙዚቃ ኮንሰርት ባለፈው ሃሙስ በጊዮን ሆቴል አቅርቧል፡፡ በቀጣይም በሌሎች አካባቢዎች ተመሳሳይ ዝግጅቶች ይኖራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
“ሚዛንን” የምርጫ ምልክቱ አድርጎ ለምርጫው እየተዘጋጀ ያለው (ኢዜማ) በበኩሉ ከባለፈው ሰኞ ጀምሮ በተለይ በአዲስ አበባ  ራስን የማስተዋወቅና የምረጡኝ ቅስቀሳ ጀምሯል፡፡
ነፃ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎትን እየሰጠ ራሱን ያስተዋውቃል፡፡
ባለፈው ሰኞ በአዲስ አበባ የተመረጡ አካባቢዎች ከፊት ለፊት አርማውን የለጠፉ አውቶቡሶችን በማዘጋጀት ተጠቃሚዎችን በነፃ ሲያጓጉዙ ውሏል፡፡ በእነዚህ አውቶቡሶች ላይ የተመደቡ የፓርቲው ሊቀ መንበር የሺዋስ አሰፋና ፣ምክትል መሪው አንዷለም አራጌን ስለ ኢዜማ ገለፃ ሲያደርጉ ሰንብተዋል፡፡
ኢዜማ ይህን የቅስቀሳ መንገድ የሚቀጥልበት ሲሆን ሌሎች አዳዲስ የምረጡኝ ቅስቀሳ ሰልቶችን መቀየሱ ታውቋል፡፡
አዲስ አበባ ላይ ዋነኛ ተፎካካሪ እሆናለሁ የሚለው ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ በበኩሉ የተጨበጠ የቀኝ እጅን የምርጫ ምልክቱ አድርጎ፣ በተለያዩ ስልቶች ቅስቀሳ ለማድረግ ማቀዱ ታውቋል፡፡
የጎዳና ላይ ቅስቀሳዎችን ጨምሮ በተለያየ መልኩ በታተሙ በራሪ ወረቀቶች መልዕክቶች ቅስቀሳ ለማድረግ ማቀዱን የፓርቲው የፖለቲካ ጉዳዮች ሃላፊ አቶ ጌታነህ ባልቻ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
ፓርቲው ራሱን የሚያስተዋውቅበትና ለምርጫው ማስኬጃ ገቢ የሚያሰባስበበት የእራት ግብዣ መርሃ ግብር የካትት 23 ቀን 2013 ዓ.ም ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ አዘጋጅቷል፡፡ በነገው እለትም ከመኢአድ፣አብን፣ኢብአፓ ጋር በመሆን በአዲስ አበባ ጉዳናዎች 50 ሺህ ሰዎች የሚሳተፉበት የቅስቀሳ መርሃ ግብር ያከናውናል
 የምርጫ ምልክቱን ሰዓት ያደረገው አብን በበኩሉ፤ በነገ ዕለት፡ በአዲስ አበባ በጋራ ለመስራት ከተስማማቸው ፓርቲዎች ጋር የምርጫ ቅስቀሳ ማስጀመሪያ ሥነ ስርዓት እንደሚያካሂድ የታወቀ ሲሆን በባህር ዳር፣ ጎንደር፣ ደሴና ደብረ ብርሃን እንዲሁም ቅስቀሳ ያካሂዳል፡
በየከተሞቹ ዋና ዋና መንገዶች ላይ የአደባባይ ትዕይንቶችና ልዩ ልዩ ኪነ ጥበባዊ ትርኢቶች ይቀርባሉ ተብሏል፡፡

Read 13474 times