Sunday, 21 February 2021 18:57

ሰሜን ኮርያውያኑ የክፍለ ዘመኑ ቀንደኛ የባንክ ዘራፊዎች 1.3 ቢ. ዶላር በማጭበርበር ተከሰሱ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ሰሜን ኮርያ 9 የኮሮና ክትባቶችን መረጃ ለመዝረፍ መሞከሯ ተነገረ


          የአሜሪካ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ፣ በተለያዩ የአለማችን ባንኮችና የንግድ ኩባንያዎች ላይ ላይ የኢንተርኔት ጥቃት በመፈጸም በድምሩ ከ1.3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለማጭበርበር የሞከሩ #የ21ኛው ክፍለ ዘመን ስመጥር የባንክ ዘራፊዎች; ናቸው ባላቸው ሦስት ሰሜን ኮርያውያን ላይ ክስ መመስረቱን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
የሰሜን ኮርያ መንግስት የደህንነት መስሪያ ቤት ባልደረቦች እንደሆኑ የተነገረላቸው ጆን ቻንግ ሆክ፣ ኪም ኢል እና ፓርክ ጂን ሆክ የተባሉት ሶስት ሰሜን ኮርያውያን፣ በተለያዩ ጊዜያት፣ የኤቲኤም ማሽኖችን በቫይረስ በመበከል እንደፈለጉ እንዲከፍሉ ማድረግን ጨምሮ በተለያዩ ባንኮች ላይ የሳይበር ጥቃት ወንጀሎችን በመፈጸም፣ 1.2 ቢሊዮን ዶላር ያህል ለማጭበርበር መሞከራቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡
የክፍለ ዘመኑ ቀንደኛ የባንክ ዘራፊዎች የተባሉት ሰሜን ኮርያውያኑ፣ ጠመንጃ ሳያነግቡ በኮምፒውተር ኪቦርድ ብቻ በመጠቀም ከፍተኛ የዝርፊያ ወንጀል ሲፈጽሙ መቆየታቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ ግለሰቦቹና ግብረአበሮቻቸው ከ2015 እስከ 2019 በነበሩት አመታት በቬትናም፣ ባንግላዴሽ፣ ታይዋን፣ ሜክሲኮ፣ ማልታና ሌሎች አገራት ባንኮች ላይ የማጭበርበር ድርጊት መፈጸማቸውንና በባንግላዴሽ ባንክ በፈጸሙት ጥቃት ብቻ 81 ሚሊዮን ዶላር ማጭበርበር መቻላቸውን አስታውሷል፡፡
በፈረንጆች አመት 2017 በተፈጸመውና “ዋናክራይ” በሚሰኘው ግዙፍ የኢንተርኔት ጥቃት ተሳታፊ ነበሩ ከተባሉትና በአሁኑ ወቅት ሰሜን ኮርያ ውስጥ ሳይሆኑ አይቀሩም ከተባሉት ተከሳሾች አንዱ የሆነው ፓርክ፣ በ2014 በሶኒ ፒክቸርስ ኩባንያ ላይ በተፈጸመው ጥቃት ተሳታፊ በመሆኑ ከዚህ ቀደም ተከስሶ እንደነበርም ዘገባው አስታውሷል፡፡
ሮይተርስ በበኩሉ፣ ሰሜን ኮርያ የአሜሪካ መድሃኒት አምራች ተቋም ከሆነው ፋይዘር፣ የኮሮና ክትባት መረጃዎችን በኢንተርኔት ጥቃት ዘርፋ ለመውሰድ መሞከሯን፣ የደቡብ ኮሪያ ደህንነት ኤጀንሲ ባወጣው መረጃ ማስታወቁን ዘግቧል፡፡
ኮሮና ቫይረስ ወደ ግዛቴ አልገባም በማለት ደጋግሞ ሲናገር የከረመው የሰሜን ኮርያ መንግስት ያሰማራቸው የኢንተርኔት መንታፊዎች፤ ከፋይዘር በተጨማሪ ኖቫክስ እና አስትራዚኔካን ጨምሮ ቢያንስ በዘጠኝ የኮሮና ክትባት አምራች ኩባንያዎች ላይ የመረጃ ዘረፋ ሙከራ ማድረጉንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡



Read 1359 times