Monday, 22 February 2021 06:52

XXXII ኦሎምፒያድ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

  • በ1 ዓመት መዘግየቱ ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ አክስሯል
      • 4.8 ሚሊዮን ትኬቶች ተሸጠው ነበር፤ ከ810ሺ በላይ ጃፓናውያን ገንዘባቸው እንዲመለስ ጠይቀዋል፡፡
      • ስፖንሰር ካደረጉ የጃፓን ኩባንያዎች 36 በመቶው ኦሎምፒኩ በድጋሚ እንዲራዘም ሲጠይቁ 29 በመቶው ደግሞ ሙሉ ሙሉ እንዲሰረዝ ብለዋል፡፡
      • ከቶኪዮ 2020 በፊት ኬንያ 14 ኦሎምፒያዶችን በመሳተፍ 31 የወርቅ፤ 38 የብርና እና 34 የነሐስ ሜዳልያዎችን በድምሩ 103 ሜዳልያዎችን              ስትሰበስብ፤ ኢትዮጵያ 13 ኦሎምፒያዶች 22 የወርቅ፤ 11 የብርና እና 21 የነሐስ ሜዳልያዎችን በድምሩ 54 ሜዳልያዎችን ተጎናፅፋለች፡፡


              የጃፓኗ ከተማ ቶኪዮ ለምታስተናግደው 32ኛው ኦሎምፒያድ 152  ቀናት የቀሩ ሲሆን አወዛጋቢ ሁኔታዎችን በ2021 እኤአ ላይ ዓለም በጉጉት የሚጠብቀው ታላቅ የስፖርት መድረክ ሆኗል፡፡ ከ18 ዓመታት በፊት የቶኪዮ ከተማ ኦሎምፒክን እንድታስተናግድ ስትመረጥ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በከፍተኛ ደረጃ ተደስተው ነበር፡፡
የኦሎምፒክ መስተንግዶው ለረጅም ጊዜ የቆየውን የጃፓን ኢኮኖሚ መቀዛቀዝ የሚያነቃቃ፤ በፉኩሺማ የኑክሌር አደጋ የተፈጠረውን አሳፋሪ ሁኔታ የሚያስረሳ እና የአገሪቱን መልካም ገፅታ እንደሚገነባ ታምኖበት ነው፡፡
ይሁንና ነገሮች እንደታሰቡት በትክክል አልሄዱም፤ ታላቁ የስፖርት መድረክ ኦሎምፒክ በአንድ ዓመት ያዘገየው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዋንኛ ምክንያት  ስለሆነ ብቻ አይደለም፡፡ በቶኪዮ ከተማ የሚገኘው ዋናው የኦሎክ ስታድዬም ዲዛይን የብስክሌተኛ ሄልሜት፤ መንኮራኩር ወይንም ኤሊን የመሰለ በመሆኑ ከፍተኛ ውዝግብ ሲያነሳ ከመቆየቱም በላይ የተጋነነ ወጭ ስለነበረው ነው፡፡ ለውድደሩ የተዘጋጀው ሎጎ በቤልጂየም ውስጥ የቲያትር ምስል መሆኑ ታውቆ ክስ ከቀረበ በኋላ መወገድና አዲስ መሰራት ነበረበት፡፡ ሰሞኑን ደግሞ የቶኪዮ ኦሊምፒክ አዘጋጅ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት የነበሩት ዩሹሪ ሞሪ  በቦርድ ስብሰባዎች ውስጥ ሴቶችበጣም ብዙ ይናገራሉ ሲሉ የሰጡትን አስተያየት ተከትሎ በደረሰባቸው ትችት ስልጣናቸውን እንዲለቁ ግፊት አድርጎባቸዋል፡፡
32ኛው ኦሎምፒያድ በ1 ዓመት መሸጋሸጉ በእርግጥ  አዘጋጆቹን ወደ 3 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ወጪ በተጨማሪ አስወጥቷቸዋል። ከቶኪዮ ኦሎምፒክ የተለያዩ ውጣውረዶች በኃላ ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ሌሎች  አሳሰቢ አጀንዳዎችን ለመጋፈጥ ግድ ሆኖበታል፡፡ በተለይ ኦሎምፒክን ለማስተናገድ የሚፈልጉት አገሮች ብዛት እያነሰ መምጣቱ ነው፡፡ በ2004 እኤአ ላይ ኦሎምፒክ ለማስተናገድ 11 አገራት ነበር የተወዳደሩት ለ2020ው ኦሎምፒክ ብዛታቸው ወደ አምስት ቀንሷል ፡፡ ከዚያ በኋላ እየተካሄዱ ለሚቀጥሉት ኦሎሚኮች ያመለከቱት ሁለት አገራት ሆነዋል። ሁኔታው ያስጨነቀው ዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ (IOC) የ2024 እና የ2028 ጨዋታዎችን አሸናፊ በተመሳሳይ ጊዜ ይፋ ለማድረግ ተገድዷል፡፡
በሌላ በኩል COVID-19 አሁንም በብዙ የዓለም ክፍሎች እየተስፋፋ መሆኑን ያገናዘበው የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ (አይኦሲ) በሐምሌ ወር ለሚጀመረው የቶኪዮ ኦሊምፒክ እና ፓራሊምፒክ ጨዋታዎች ለተሳታፊ አትሌቶች፤ ፌደሬሽኖች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት አራት የመመርያ መፅሃፍትን አዘጋጅቷል። የመመርያ መፅሃፍቱ ለአባል አገራት የኦሎምፒክ ኮሚቴዎችና ፌዴሬሽኖች፣ ለአትሌቶች እና ባለሥልጣናት፣ ለፕሬስ እና ለብሮድካስት ኩባንያዎች የተሰራጩ ናቸው። እያንዳንዱ አትሌት ወደ ኦሊምፒኩ ስፍራ ከገባ ጊዜ ጀምሮ የጉዞ ሁኔታ፣ ለቀናት ተገልለው የሚቆዩበት፣ ምርመራ፣ ራሳቸውን የሚጠብቁባቸው ቁሳቁሶች እና ክትባቱን መስጠት የሚሉ ሂደቶችን የሚያሳልፍ ይሆናል።  
በርካታ የስፖርቱ ተንታኞች ኦሎምፒኩን ያለ በቂ የደህንነት ዋስትና ማካሄዱን “ኃላፊነት የጎደለው” አድርገው እየተቹት ቢሆንም የIOC ፕሬዝዳንት ቶማስ ባች     የእኛ ተግባር የኦሎምፒክ ጨዋታዎችን ማደራጀት እንጂ የኦሎምፒክ ጨዋታዎችን ለመሰረዝ አይደለም በሚል ምላሻቸው ተሟግተዋል፡፡ ይህንን አመለካከት በመደገፍም የቶኪዮ 2020 ፕሬዝዳንት ዮሺሮ ሞሪ ጃፓን የወረርሽኝ ሁኔታ ምንም ይሁን ምን የኦሎምፒክ እና የፓራሊምፒክ ውድድሮችን ማዘጋጀቷ አይቀርም ብለው ተናግረዋል፡፡ በአሎምፒኩ  ላይ ለሚገኙ አትሌቶች እና ባለሥልጣናት በመመርያ መፅሃፍቱ ከቀረቡት ዋና ህጎች መካከል ሁሉም ኦሎምፒያኖች የኮቪድ ምርመራ ጃፓን ከመግባታቸው በፊትና በኋላ ማድረግ እንዳለባቸው፤ የሰውነት ሙቀታቸው በየጊዜው እንደሚለካ የተገለፁት ይገኙበታል፡፡
ሰሞኑን ደግሞ ከኦሊምፒኩ ጋር በተያያዘ በስፋት እየተነሳ ያለው ሃሳብ የኦሊምፒኩ ተሳታፊዎች የኮቪድ 19 ቫይረስ ክትባት መውሰድ እንዳለባቸው የተነሳው ሲሆን ክትባቱን በቀላሉ ማግኘት አዳጋች መሆኑ ግን እየተጠቆመ ነው፡፡ የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ፕሬዚዳንት ቶማስ ባች፤ ክትባቱ ለኦሊምፒክ ተሳታፊዎችም ይደርሳል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡  በኦሎምፒክ ተመልካቾች ጉዳይ ላይ ዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴም የመጨረሻውን ውሳኔ ከ1 ወር በኋላ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል፡፡
ለአትሌቶች ደህንነትና ከዓለም ሕዝብ ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር ውድድሩ ያለ ተመልካች በዝግ መካሄድ እንዳለበት የሚከራከሩ ብዙ ሲሆኑ በአንጻሩ ውድድሩ ያለ ደጋፊ መካሄዱ ድምቀቱን የሚያደበዝዘው በመሆኑ መፍትሄ እንዲፈለግም  ሃሳቦችም ተሰንዝረዋል። የቶኪዮ 2020 አዘጋጅ ኮሚቴ  ጃፓን ውስጥ ብቻ 4.48 ሚሊዮን ቲኬቶችን  መሸጡን ቢያሳውቅም  ባለፈው ወር ከ810ሺ በላይ ጃፓናውያን ተመላሽ ገንዘብ እንደጠየቁ ታውቋል፡፡ 32ኛው አሎምፒያድ ከቲኬቶች ሽያጭ እስከ 867 ሚሊዮን ዶላር ገቢን እንደሚያስገኝ ተተንብዮ የነበረ ቢሆንም የሚሳካ አይመስልም፡፡
ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ እና የጃፓን የኦሎምፒክ አዘጋጅ ኮሚቴ 32ኛው ኦሎምፒያድን  በማናቸውም መስዕዋትነት እና ቅድመ ጥንቃቄ ለማካሄድ ቢወስኑም በተለያየ ሚዲያ ተቋማት የተሰበሰቡ ድምፆች የአዘጋጅ አገሯን ሁኔታ አጠራጣሪ አድርጎታል፡፡ ኦሎምፒኩ  ወራት እየቀሩት ሮይተርስ ባሰባሰበው ድምፅ የስፖርት መድረኩን ስፖንሰር ካደረጉ  የጃፓን ኩባንያዎች መካከል ከ60 በላይ የሚሆኑት በተለያየ መንገድ ተቃውሞ አሰምተዋል። ከጃፓኖቹ ኩባንያዎች 36 በመቶው ኦሎምፒኩ በድጋሚ እንዲራዘም ሲጠይቁ 29 በመቶው ደግሞ ሙሉ ሙሉ እንዲሰረዝ ብለዋል፡፡
እንዲካሄድ የሚፈልጉት የጃፓን ኩባንያዎች 35 በመቶን ድርሻ ይወስዳሉ። በሌላ በኩል የጃፓን ጋዜጣ በሰበሰበው ድምፅ ከጃፓን ህዝብ 77 በመቶው እንዲሰረዝ ወይንም በድጋሚ የሚካሄድበት ወቅት እንዲራዘም ይፈልጋሉ። ጃፓን በ2003 እኤአ ላይ የኦሎምፒክ መስተንግዶውን ስታገኝ ከ7.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ በጀት በማውጣት እስከ 2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማትረፍ አቅዳ ነበር፡፡
ኮቪድ 19 በፈጠረው ተፅእኖና በሌሎች ምክንያቶች የኦሎምፒክ መስተንግዶውን ለማሳካት ወጭው 25 ቢሊዮን ዶላር አልፏል፡፡ ይህም  በኦክስፎርድ ዩኒቨርስት ጥናት መሰረት በአሎምፒክ 125 አመታት ታሪክ ከፍተኛው ወጭ ሆኖ በአዲስ ክብረወሰንነት የተመዘገበ ነው፡፡
የኬንያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ልዩ ዝግጅትና የኢትዮጵያ ሁኔታ
የኦሎምፒኩ ዓመት ምንም እንኳን በኮቪድ 19 እና ተያያዥ የኢኮኖሚ ጫናዎች የተስተጓገጎለ ቢሆንም ኬንያውያን በሚሳተፉ ኦሎምፒያኖች ብዛት እና ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ስኬታማ ለመሆን ተስፋ አድርገዋል፡፡  
በፖል ቴርጋት የሚመራው የኬንያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ለኦሎምፒኩ በሰጠው ልዩ ትኩረት ላለፈው 1 ዓመት ኦሎምፒያኖቹን በተለያዩ ቡድኖች በመከፋፈል ከፍተኛ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታም የኦሎምፒክ ቡድኑን ዝግጅት በቅርብ ርቀት በመከታተል ያበረታታሉ፡፡ ኦሎምፒክ ኮሚቴው ለ32ኛው ኦሎምፒያድ ብቻ ሳይሆን ፓሪስ በ2024 እኤአ ለምታዘጋጀው 33ኛው ኦሎምፒያድም በማቀድ ነው እየሰራ የሚገኘው፡፡
በተለይ አዳዲስ ኦሎምፒያኖች ከዝግጅት ጋር በተያያዘ በፋይናንስ ችግር ውስጥ እንዳይገቡ በማሰብ የአጋርነት ስምምነት ኬሲኤስ Kenya Charity Sweepstake (KCS) ከተባለ ተቋም ጋር ተፈራርሟል። በስምምነቱ መሰረት ለሚቀጥሉት 3 ዓመታት የኬንያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ከተቋሙ ዓመታዊ ገቢ 10 በመቶ ድርሻ የሚወስድ ሲሆን ለቶኪዮ ኦሎምፒክ ዝግጅትም የመጀመርያው ዙር ክፍያ 90ሺ ዶላር ተበርክቶላቸዋል፡፡ ይህ አይነቱ ድጋፍ አትሌቶችን በኦሎምፒክ ተሳትፎ ውጤታማ የሚያደርጋቸውን የ4 ዓመታት ቀጣይ ዝግጅት ለመስራት እንደሚያመች ነው የተላዩ ዘገባዎች የጠቀሱት፡፡
ኬንያ  በቶኪዮ 2020 ኦሎምፒክ ከ100 በላይ ኦሎምፒያኖችን ለማሳተፍ ያቀደች ሲሆን፤ 56 የኦሎምፒክ ሚኒማውን ከወዲሁ ከማሳካታቸውም በላይ  15 አትሌቶች በብሄራዊ ኮሚቴ፤ በአፍሪካ ኦሎምፒክ ኮሚቴዎች ማህበር ድጋፍ ለኦሎምፒክ እየተዘጋጁ ናቸው። የኬንያ ኦሎምፒክ ፕሬዝዳንት ፖል ቴርጋት ከኦሎምፒክ ቡድናቸው በተለይ በቦክስ እና በራግቢ ቡድን የሚኖተረው ተሳትፎ አጓጉቶታል። የኬንያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ 32ኛው ኦሎምፒያድንና በ2024 የሚካሄደውን የፓሪስ 33ኛው ኦሎምፒያድ ኢንፍሮንት በተባለ የሚዲያ ኩባንያ አማካኝነት  በቀጥታ የቴሌቭዥን ስርጭት ሽፋን ለማግኘት ስምምነት አድርጓል፡፡ ኬንያ ካለፉት 31 ኦሎምፒያዶች 14 ኦሎምፒክን የተሳተፈች ሲሆን  31 የወርቅ፤ 38 የብርና እና 34 የነሐስ ሜዳልያዎችን በድምሩ 103 ሜዳልያዎችን ሰብስባለች፡፡ በ2016 እኤአ ላይ ሪዮ ዲጄኔሮ ባስተናገደችው 31ኛው ኦሎምፒያድ  ኬንያ በ7 የተለያየዩ ስፖርቶች 89 ኦሎምፒያኖችን በማሳተፍ 6 የወርቅ ሜዳልያዎች በጠቅላላው 13 ሜዳልያዎችን መሰብሰቧ ይታወሳል። ቶኪዮ የምታስተናግደው 32ኛው ኦሎምፒያድ ላይ ኢትዮጵያ ስትሳተፍ በታሪክ 14ኛዋ የኦሎምፒክ መድረክ ሲሆን በሶስት የስፖርት አይነቶች በአትሌቲክስ፤ ብስክሌት እና ቴክዋንዶ ስፖርቶች ኦሎምፒያኖችን እያዘጋጀች ነው፡፡ ከቶኪዮ 2020 በፊት ኢትዮጵያ በተሳተፈችባቸው  13 ኦሎምፒያዶች 22 የወርቅ፤ 11 የብርና እና 21 የነሐስ ሜዳልያዎችን በድምሩ 54 ሜዳልያዎችን ሰብስባለች፡፡

  10 የምንግዜም ውድ ኦሎምፒያዶች
በኮቪድ 19 ሳቢያ በአንድ ዓመት የተሸጋሸገው 32ኛው ኦሎምፒያድ በጃፓን ቶኪዮ ከ25 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጭው በመድረሱ ይምንገዜም ውድ አዞሎምፒክ ሆኖ በመጀመርያ ደረጃ እንዲሰፍር አድርጎታል፡፡
ከዚህ በታች የቀረበው በኦሎምፒክ ታሪክ ከፍተኛ ወጭ በማስመዝገብ  እሰከ 10ኛ ደረጃ የያዙበት ዝርዝር ሲሆን ይህም የበጋ እና የክረምት ኦሎምፒክን ያካትታል፡፡
32ኛው ኦሎምፒያድ በጃፓን ቶኪዮ 2020 21 እኤአ $25 billion (£20billion)
በራሽያ፤ ሶቺ የተዘጋጀው የክረምት ኦሎምፒክ 2014 እኤአ $21.9billion (£17billion)
30ኛው ኦሎምፒያድ በእንግሊዝ ለንደን 2012 እኤአ $14.9billion (£11.6billion)
25ኛው ኦሎምፒያድ በስፔን ባርሴሎና 1992 እኤአ $9.7billion (£7.5billion)
29ኛው ኦሎምፒያድ በቻይና ቤጂንግ 2008 እኤአ $6.8billion (£5.3billion)
27ኛው ኦሎምፒያድ በአውስትራሊያ ሲድኒ 2000 እኤአ $5billion (£3.9billion)
31ኛው ኦሎምፒያድ በብራዚል ሪዮዲጄኔሮ 2016  $4.6billion (£3.6billion)
በጣሊያን ቱሪን የክረምት ኦሎምፒክ 2006 እኤአ  $4.4billion (£3.4billion)
26ኛው ኦሎምፒያድ በአሜሪካ አትላንታ 1996 $4.14billion (£3.2billion)
28ኛው ኦሎምፒያድ ግሪክ አቴንስ 2004 እኤአ $2.9billion (£2.25billion)
የዓለማችን 10 ሃብታም ኦሎምፒያኖች
$2 billion አይኦን ቲሪያክ ሮማኒያዊ ዜግነት ያለው ይሄ ስፖርተኛ በሆኪ ስፖርት በ1964 እኤአ በተካሄደው የክረምት ኦሎምፒክ ተሳትፎ 12ኛ ደረጃ ነበረው፡፡ ከ1970ዎቹ ጀምሮ ታዋቂ የሜዳ ቴኒስ ስፖርተኛ ሆኖ አሳልፋል፡፡
$1.9 billion ማይክል ጆርዳን በ1984 እኤአ  እና በ1992 እኤአላይ የአሜረሪካ ቅርጫት ኳስ ብሄራዊ ቡድን በአምበልነት በመምራት ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎችን ተጎናፅፏል፡፡
$1.2 billion  የዊንክሎቭ ወንድማማቾች  በ2008 እኤአ በቤጂንግ ኦሎምፒክ ሜዳልያ ባያገኙም አስደናቂ ተሳትፎ አድርገዋል፡፡
$600 million ማጂክ ጆንሰን በ1992 እኤአ ላይ በበባርሴሎና ኦሎምፒክ ላይ የወርቅ ሜዳልያ ከወሰደው የአሜሪካ ብሄራዊ ቡድን ጋር አባል ነበር፡፡
$560 million ፍሎይድ ሜይዌዘር ከስኬታማ የቦክስ ስፖርተኞች አንዱ ቢሆንም በ1996 እኤአ በአትላንታ ኦሎምፒክ በቀላል ሚዛን የነሐስ ሜዳልያ ተሸልሟል፡፡
$460 million ክርስትያኖ ሮናልዶ በ2004 እኤአ ላይ በቴንስ ኦሎምፒክ ከፖርቱጋል ብሄራዊ ቡድን ጋር ቢሰለፍም የሜዳልያ ሽልማት አልተጎናፀፈም፡፡
$450 million ሮጀር ፌደሬር ምንም እንኳን በሜዳ ቴኒስ የምንግዜም ውጤታማ ስፖርተኛ ቢሆንም በግሉ የወርቅ ሜዳልያ በኦሎምፒክ መድረክ ላይ አላስመዘገበም። በ2008 እኤአ ቤጂንግ ላይ በቡድን የወርቅ ሜዳልያ ብቻ አሸንፏል፡፡
$440 million ሊብሮን ጄምስ ከአሜሪካ ብሄራዊ ቡድን ጋር በቅርጫት ኳስ 3 የወርቅ ሜዳልያዎችን በ2004 አኤአ አቴንስ፤ በ2008 እኤአ በቤጂንግ እንዲሁም በ2012 እኤአ በለንደን ኦሎምፒክ
$400 million ሊዮኔል ሜሲ በ2008 እኤአ በቤጂንግ ኦሎምፒክ ቻይና ከአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድን ጋር የወርቅ ሜዳልያ ወስዷል፡፡ ሁለት የኦሎምፒክ ጎሎችን አስቆጥሯል፡፡  
$400 million ሻክ ኦኔል ቅርጫት ኳስ በ1996 እኤአ አትላንታ ኦሎምፒክ ላይ የወርቅ ሜዳልያ
ተጎናፅፏል፡፡  
በከፍተኛ የሜዳልያ ስብስብ 10 አገራት
ባለፉት 31 ኦሎምፒያዶች በአጠቃላይ የሜዳልያ ስብስብ ከ1 እስከ 10 ደረጃ የሚይዙት አገራት የሚከተሉት ናቸው፡፡


Read 953 times