Tuesday, 23 February 2021 00:00

ምርጫው ብቻ ወይንስ የምርጫው ትክክለኛነት?

Written by  ነብዩ ኤርምያስ
Rate this item
(0 votes)


            "አንዳንዶች በትክክለኛ ምርጫ ዲሞክራሲያዊ መንግሰት ሲመሰርቱ፣ ሌሎቻችን ደግሞ በተቃራኒው በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ኢ-ፍትሃዊ የሆነ መንግስት እንዲቋቋም ድርሻ እናበረክታለን፡፡ ስለዚህም በአስተውሎት ትክክለኛውን አማራጭ ማወቅና የፓርቲዎችን ፕሮግራም ጠንቅቆ መረዳት፣ ለጥቂት ሰዎች የሚሰጥ ጉዳይ ባለመሆኑ እያንዳንዳችን ኃላፊነታችንን እንወጣ፡፡ ትክክለኛ የሆነ ምርጫን ከውነን፣ የምንፈልጋትን ሀገር እንፍጠር፡፡-"
               
            ሀገራችን ኢትዮጵያ በመጪው ግንቦት ወር ማብቂያ ላይ አንድ አብይና ብርቱ ጉዳይ ታስተናግዳለች፤ 6ኛውን ብሔራዊ ምርጫ፡፡ በአንድም ሆነ በሌላ ምርጫው ይመለከተናል ያሉ ወገኖች ሁሉ፣ በየፊናቸው ቅድመ ምርጫ ዝግጅት ላይ ተፍ ተፍ እያሉ ነው። ምርጫው እንደሚባለው፣ ለዲሞክራሲ ሽግግር ወሳኝ መሆኑን በመገንዘብ፣ ህዝባዊ መንግስት ለመመስረት ብሎም፣ የህዝብን የስልጣን ባለቤትነት ለማረጋገጥ የሚደረግ ነው፡፡ በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ፤ ምርጫ የዲሞክራሲ ሂደት ማሳያ ብሎም፣ የአንድ ሀገር የፖለቲካ እንቅስቃሴ የደረሰበትን ደረጃ መለኪያና ማሳያ ነው፡፡
በዚህም ረገድ መጪው ሀገራዊ ምርጫም፣ በመርህ ደረጃ፣ ይህንኑ አላማ ማንገቡ አይቀሬ ነው፡፡ ነገር ግን በርግጥ ይህ ምርጫ ትርጉሙንና ዓላማውን በሀገራችን ከግብ ያደርሳል ወይ? ሲጀምርስ ለአንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ምርጫ ምኑ ነው? በምርጫው ሂደት መሳተፍ ብቻውን፣ አግባብና ትክክል ነው ወይ? የምርጫን ትክክለኛነት በምንና እንዴትስ እናረጋግጣለን? የምርጫ ሂደቱስ፤ መምረጥና መመረጥ ምን ይፈልጋሉ? የሚሉትን ጥያቄዎች መፈተሽ አስፈላጊ በመሆኑ፣ ይህ ጽሁፍ ማጠንጠኛውን በነዚህ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በማድረግ በከፊል ለመዳሰስ ይሞክራል፡፡
ምርጫ
ምርጫ በፍላጎታችን አንድን የፖለቲካ ፓርቲ (ቡድን) ለተገደበ ጊዜ፣ የአስተዳደር ሃላፊነት የምንሰጥበትና የማይፈለገውን የምንሽርበት የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አንዱ አካል ነው፡፡ ዳሩ ግን ምርጫ ባህል ባልሆነበትና የዲሞክራሲ ሥርዓት ባልዳበረበት አግባብ፤ ሂደቱ ቀላል አይሆንም፡፡ በርግጥ በምርጫ መሳተፍ ለምሳሌ መምረጥ የተለየ ችሎታ/መሰጠትን አይጠየቅም፡፡ ምክንያቱም መምረጥ፤ ለአቅመ መምረጥ ለበቃ ሰው በትክክለኛው ሰዓት፣ በምርጫ ጣቢያው በመገኘት፣ ካሉት የምርጫ ክልሉ ተመራጮች በአንዱ ላይ ምልክት በማድረግ፣ በተዘጋጀው የድምጽ ኮሮጆ ውስጥ የማስቀመጥ ድርጊት ነውና፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ መምረጥም ቢሆን በዚህ ደረጃ ቀላል ሊሆን አይችልም፡፡ ምክንያቱም በዋናነት ከፊታችን ያለው ሀገራዊ ምርጫ የሚከወንበት ጊዜ፣ ከወትሮው በተለየ ሀገሪቷን የሚንጡ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ባሉበት፤ የተለያዩ አንዳንዴም ተጻራሪ የፖለቲካ እይታዎች በሚስተናገዱበት፤ በብዙ ጉዳዮች ላይ ሀገራዊ መግባባት ባልተደረሰበት፤ ፖለቲካው በጥቂት ግለሰቦች ላይ ጥገኛ በሆነበት፤ ባጠቃላይ የሀገሪቷ ሁለንተናዊ ሁኔታ ከቀደሙት  ጊዜያት በተለየ  ሁኔታ ውስጥ የሚደረግ  ነውና፡፡  
ምርጫው እነዚህን ሀገራዊ ችግሮች ታሳቢ ያደረገ መሆን ይኖርበታል፡፡ ምንም እንኳን አንዳንዶች፣ ኢትዮጵያ እውነተኛ የምርጫ ታሪክ የላትም የሚል መከራከሪያ ሀሳብ በማምጣት፣ አሁን ያሉት ችግሮች በምርጫው እንደማይመለሱ ቢያውጁም፤ ምርጫውን ነፃ፣ ፍትሃዊና ትክክለኛ ካደረግነው፣ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ታሪክ አቅጣጫ የመቀየር አቅም ይኖረዋል፡፡ ያም የሚሆነው ምርጫው የሚከወነው፤ ጠንካራ ተቋሟትን ስለ መገንባት፤ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ስለ ማስከበር፤ ፍትህን ስለ ማግኘት፤ እኩልነትን ስለ ማረጋገጥ፤ የህግን የበላይነት ስለ ማስፈን፤ እውነተኛ ራስን በራስ የማስተዳደር መብትን ስለ መጎናፀፍ፤ መሰረተ ልማቶችን ስለ ማስፋፋት፤ ስራ አጥነትንና ድህነትን ስለ መቀነስ፤ ባህልና ቋንቋን ስለ ማበልፀግ፤ ባጠቃላይ የነገን መፃኢ ዕድልን ለመወሰን ሲሆን ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ምርጫው፣ ጥያቄዎቻችንን ሁሉ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይመልሳል ማለት አይደለም፡፡ ምርጫ ጥሩ ወይም መጥፎ መንግስት የሚቋቋምበት ብቸኛው ባይሆንም አንደኛው መንገድ ስለሆነ በድምፃችን ዲሞክራሲያዊ መንግስት መስርተን፣ ችግሮቹ የሚፈቱበትን መደላደል ልናበጅ እንችላለን፡፡
ለዚህም ነው ለአንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ብሎም፣ ለሀገሪቷ ምርጫው ቀላል የማይሆነው፤ ይልቁኑ በጣም አስፈላጊ፤ ወሳኝና ብርቱ ጉዳይ ቢሆን እንጂ፡፡ ነገር ግን የምርጫ አስፈላጊነት፣ የምርጫን ትክክለኛነት አያረጋግጥም፡፡ አንድ ሰው የሞራል/የዜግነት ግዴታውን ስለተወጣና አስፈላጊ መሆኑን ስላመነበት፣ በምርጫው መሳተፉ ብቻውን ድርጊቱን ትክክል አያደርገውም፡፡ ምክንያቱም አንድን ነገር የማድረግ ወይንም ያለማድረግ መብት ቢኖረንም፣ መብቱን መጠቀም በራሱ ብቻውን ትክክል ላይሆን በመቻሉ ነው። ምርጫውን በአግባቡ፤ በጥንቃቄና፤ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ካላስኬድነው፤ መምረጥንና መመረጥን በእውቀት ላይ ካላደረግነው፣ የምርጫው አስፈላጊነት ብሎም ውጤቱ ጥያቄ ውስጥ ይገባል፡፡ በመሆኑም መብትን ከመጠቀም በዘለለ ስለ ምርጫው ትክክለኛነት መትጋትና ማረጋገጥ ለነገ የማይባል ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ፅሁፍ ስለ ምርጫው ትክክለኛነት ሲዳስስ ግን ስለ ምርጫው የጊዜ ሰሌዳ፤ ስለ ምርጫ ቦርድ ኃላፊነት፤ ወይንም ስለ ምርጫው ነፃና ፍትኃዊ መሆን ወይንም በሰላም መጠናቀቅ አይደለም፤ይልቁንም  በዋናነት ለምንና እንዴት የመምረጥ መብትን እንጠቀም ብሎም የምርጫ ኃላፊነትን መውሰድን ነው የሚቃኘው፡፡ ከዚህ አንጻር የምርጫውን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ እንደ መራጭ ምን ይጠበቅብናል? የፖለቲካ ፓርቲዎችና የመገናኛ ብዙኃንስ ሚና ምንድን ነው? በእኒህ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ጥቂት ሃሳቦችን ለማንሸራሸር እንሞክራለን፡፡   
እንደ መራጭ ዜጋ
ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ምርጫ ልክ ምግብ ቤት ገብተን ከምግብ መዘርዝር ውስጥ የፍላጎታችንን እንደ መምረጥ ወይንም በመሰለኝና ደሳለኝ የምንከውነው ድርጊት ሳይሆን፤ በምርጫው መሳተፋችን በሀገሪቱ ውስጥ ያሉትን ችግሮች ማገናዘቡንና ለጥያቄዎቻችን መልስ መስጠቱን ማረጋገጥ የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡ ለምሳሌ፤ በምርጫው እንዲያሸንፍ የምንፈልገው የፖለቲካ ቡድንና የሚከተለው ፕሮግራም ያሉትን ወሳኝ ችግሮችና የህዝብ ጥያቄዎች በምን አይነት ማዕቀፍ ነው የሚያስተናግደው? በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ያለው አመለካከት ምንድን ነው? ቁርጠኝነቱስ ምን ይመስላል? የሚሉ ነጥቦችን ከብዙ በጥቂቱ መፈተሽ ይኖርብናል። ለዚህም ተመልካች ልቡና ብሎም የማያዳላ አዕምሮ ባለቤትነት ወሳኝ በመሆናቸው፣  የምርጫውን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ማስተዋል ከሚገቡን የተወሰኑትን እናንሳ፡፡
ዛሬ ላይ እንደሚነገረው፤ በምርጫ ቦርድ እውቅና ያገኙ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢኖሩም፣ ፖለቲካው የሚዘወረው ግን በጥቂት ግለሰቦች መሆኑ የአደባባይ ሚስጢር ነው፡፡ ነገር ግን ስንቶቻችን ነን አመራሮቹንና የፖለቲካ አመለካከታቸውን፤ ወይንም የሚከተሉትን ፖሊሲና ፕሮግራም ልዩነት አጥርተን የምናውቀው? ብዙዎቻችን የፖለቲካ ባህላችንም ሆነ ልምዳችን ያልዳበረ በመሆኑ እነዚህን ነገሮች ቀላቅለን ነው የምናየው፡፡ ለምሳሌ አንድ የብሔር ስያሜ ያለው የፖለቲካ ድርጅት፣ ብሔሩን ማዕከል ስላደረገ ብቻ ወይንም ስያሜው ስለሚማርክ በጭፍን የምንደግፍ፤ ለካሜራ ምሉዕ መሆንን (photogenic) እንደ ምክንያት በመውሰድ ይሁንታችንን የምንሰጥ የለንም? ነገር ግን በድርጅትና ህዝብ ብሎም አመራሩ መካከል ልዩነት መኖሩን ልንገነዘብ ይገባል። ምክንያቱም ድርጅት አንድ አላማ አንግቦ፣ አላማውን ከግብ ለማድረስ ፕሮግራም ቀርፆ የሚንቀሳቀስ መሳሪያ እንጂ ህዝብን ወይንም ብሔርን የሚወክል አይደለምና ነው፡፡ አመራሮቹም ቢሆኑ ለዛ አላማ ራሳቸውን ተገዢ አድርገው የሚንቀሳቀሱ፣ እንደ ሁኔታውም ሊቀየሩና ሊቀያየሩ የሚችሉ አካላት መሆናቸውን አለመዘንጋት ያስፈልጋል፡፡
ከፓርቲው ስያሜና ከአመራሮቹ የግል ሰብዕና ይልቅ ማጠንጠኛችን መሆን ያለበት ያነገቡት ዓላማና የሚከተሉት ፕሮግራም ነው፡፡ ምን አይነት የፖለቲካ አማራጭ አንግበው እንደሚንቀሳቀሱ በአስተውሎት ማጤን አስፈላጊ ነው፡፡ በርግጥ እያንዳንዱን ፖሊሲና ፕሮግራም በጥልቀት መርምሮ መገንዘብ ራሱን የቻለ እውቀትና የፖለቲካ አረዳድ ቢፈልግም፣ እንደ አንድ መራጭ ዜጋ፣ ግንዛቤያችንንና እውቀታችንን ለማስፋት መሞከር ለምርጫው ትክክለኛነት ወሳኝ እርምጃ ነው፡፡ ለዚህም እንዲረዳን ቀዳሚው ነገር፣ አስፈላጊውን መረጃና ማስረጃ መሰብሰብና ስለሚቀርቡት አማራጮች በጥልቀት ውይይት ማድረግ፤ ለጥቆም የነገሮችን ቅደም ተከተል መለየትና የተለያዩ አማራጮችን በማነፃፀር፣ ሚዛናዊ ፍርድ ማስቀመጥ ወሳኝ ነው፡፡
ለዚህም ይረዳን ዘንድ ተአማኒ የመገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም አስፈላጊውንና አጥጋቢ የሆነ ግንዛቤ ለማግኘት መሞከር፣ በተጨማሪም የሚከተሉትን መሰረታዊ ልዩነቶች በአፅኖት ማስተዋል ይኖርብናል፡፡
በመጀመሪያ የድርጅቱ አላማ ምን ላይ መሰረት ያደረገ ነው፤ አመክንዮ ላይ ነው ወይንስ ስሜት ላይ? የፖለቲካ ድርጅቶች አላማ የተፀነሰው ከመሰረቱ ምክንያታዊነት ላይ ወይንስ ባልተጨበጠ ትርክት? (የግል/የቡድን ዕምነትን ወደ ህዝቡ ለማስረፅ የሚደረግ ጥረት?) የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በርግጥም እውነተኛ ግባቸው ነው ወይንስ ለምርጫ ሰሞን ብቻ የተፈጠረ  የማማለል ስልት? እኒህን ጥያቄዎች  በአስተውሎት መመለስ አስፈላጊ ነው፡፡ ምክንያቱም ባለን የምርጫ ታሪክ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ስልቶችን በመቀያየር፣ከድልድይ እንገነባለን እስከ የዶሮ ወተት እናቀርባለን -- ዓይነት ቃል በመግባት መሰረታዊ አላማቸውን ከግብ ለማድረስ ሲሞክሩ አስተውለናል፡፡
ሌላኛው በምርጫ ሰሞን የሚደረጉ ንግግሮች፤ በተለይ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚደረጉ ክርክሮች ላይ የሚፈፀሙ አመክኖአዊ ስሁቶችን (logical fallacies) ለይቶ ማወቅ ነው፡፡ ለአብነት ለመጥቀስ ያህልም፡-
ስንኩል የሆኑ አማራጮችን በማስቀመጥ ሀሳብን ቅርቃር ውስጥ በመክተት መራጭን አወዛግቦ ኣማራጭ ለማሳጣት መሞከር፤ ለምሳሌ፡- እኔን ካልመረጥክ ከኛ ብሔር አይደለህም/ሽም አይነት አመክንዮ፤
በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት ቅቡልነት ባገኙ ግለሰቦች ንግግር፣ ባህል፤ ወይንም ሀይማኖት ላይ በመንተራስ ሃሳብን እውነት አስመስሎ ለማስተላለፍ መሞከር፤
የማይገቡ ምሳሌዎችን መምሰል፤ ለምሳሌ አንድን ፓርቲ ከሌላኛው መምረጥ፤ ከፍቅርና ከጦርነት ፊልም ለማየት እንደመምረጥ አድርጎ መምሰልና የራስን ሃሳብ ለማረጋገጥ መሞከር፤
ነጥቦችን በማገናኘት ከመጀመሪያው ሊፈጠር የማይችል ክስተትን እንደሚፈጠር አድርጎ በማቅረብ፣ መራጭን በማሸበርና በማሳሳት የራስን ኃሳብ ተቀዳሚ አማራጭ ለማድረግ መሞከር፤
አንድ ጥፋት ያለበትን ድርጊት በራሱ ከማረቅ ይልቅ ድርጊቱን እናንተም ፈጽማችሁታልና ስህተት ልትሉት አይገባም በማለት፣ ስህተትን በስህተት ለማረም መሞከር፤
የፖለቲካ ድርጅትን አማራጭ ወደ ጎን በመተው የድርጅቱን አመራር/ሮች ሰብዕና በማብጠልጠል አሸናፊነትን የመቀናጀት ስልት፤
የተነሳው ሀሳብን በቀጥታ ከመዳሰስ ይልቅ በማስቀየስና በማንሸዋረር ምቾት በሚሰጣቸው ጉዳይ ላይ ጊዜ በመውሰድ ከሃሳቡ የመሸሽ ስልት፤
ብዝኃነት ላይ መሰረት በማድረግ አማራጭን ብቸኛ እውነት አድርጎ ለማቅረብ መሞከር፡፡ ‘ብዙ ደጋፊዎች ስላሉኝ የኔ አማራጭ ትክክል ነው’ አመክንዮ ከሃሳቡ ጥራት ይልቅ መሰረቱን የሚያደርገው ቁጥር ላይ ነው፡፡ ነገር ግን አንድ ኃሳብ ትክክል የሚሆነው ብዙ ሰዎች ስለ ተቀበሉት ነው ወይስ ብዙ ሰው የተቀበለው ኃሳቡ ትክክል ስለሆነ ነው በሚለው መካከል ትልቅ ልዩነት መኖሩን መገንዘብ የግድ ይላል፡፡ በመሰረቱ ንግግር በሦስት መሰረታዊ ነገሮች ማለትም በተናጋሪው፤ በኃሳቡና በተደራሲው መካከል ያለ መስተጋብር ነው፡፡ ንግግሩ ውጤታማና ትክክል የሚሆነው በሦስቱ መካከል ጥሩ ውህደት (fine balance) ሲኖር ነው፡፡ በመሆኑም በተናጋሪውና ታዳሚው ስለተስማማ ኃሳቡ እውነት ነው ብሎ ፈፅሞ መደምደም ያሳስታል፡፡ ስለዚህም የንግግሩን ፍሬ ኃሳብ በቅቡልነቱ ሳይሆን በምክንያት መመርመሩ ለውሳኔያችን ወሳኝ ነው፡፡
በተጨማሪም የመገናኛ ብዙኃን የሚያስተላልፉትን መረጃዎች እንደ ወረዱ ከመቀበልና ለውሳኔ ከመጣደፍ ይልቅ ስለ እውነታው ለማረጋገጥ መሞከር፣ ለምርጫው ትክክለኛነት ትልቅ ግብአት ይሆነናል፡፡ እንደ ህዝብ በሚደረገው የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎአችንን ለማረጋገጥ፣ ትክክለኛ ውሳኔ እንወስን ዘንድ ተከታዮቹን ነጥቦች ማስተዋል አስፈላጊ ነው፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች
የፖለቲካ ፓርቲዎች በዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታና የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ የላቀ ሚና እንደሚጫወቱ ይታወቃል። ይህ የፓርቲዎች ሚና የሚጎላው የአንድን የህብረተሰብ ክፍል መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያስችሉ አማራጭ ሃሳቦችን ከማመንጨት አንስቶ እስከ ተግባራዊነታቸው ድረስ ያለው ሂደት በዲሞክራሲያዊ መንገድ ሲከወን ነው። በተለይ በምርጫ ሰሞን ፓርቲዎች እንወክለዋለን ለሚሉት የህብረተሰብ ክፍልና ለቆሙለት አላማ ለመታገል የሚከተሉት መርህ፣ የዲሞክራሲ ባህል እንዲያብብ የሚያግዝ መሆን ይገባዋል፡፡ በርግጥ የምርጫው መተዳደሪያ ህግ ያስቀመጠልን አግባቦች እንዳሉ ሆኖ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች አጽንኦት ሰጥተው መራጭ ዜጋውን ሊያግዙ የሚችሉባቸውን ብርቱ ነጥቦች ማንሳት ይገባቸዋል፡፡ ከምንም በላይ ፓርቲዎች በርግጥም የፖለቲካ ፓርቲዎች መሆን አለባቸው፡፡ ማለትም ግልጽ የሆነ የፖለቲካ አላማ ባለቤት እንዲሁም ለተፈጻሚነቱ ቁርጠኛ የሆኑ ድርጅቶች ሊሆኑ ይገባል፡፡  
እንግዲህ የማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ግብ፤ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት በማግኘት፣ አማራጭ ሆኖ መቅረብና የመንግስት ስልጣን ይዞ ሃሳቡን ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡ ነገር ግን ቅቡልነትን የመጨረሻ ግብ አድርጎ መስራት ብቻ ሳይሆን ሂደቱ ላይ ማተኮር፣ ለዲሞክራሲያዊ ልምምድ  በብርቱ ይረዳል፡፡ ለዚህም በምን ዓይነት መንገድ ነው በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት የምንችለው? የሚለውን ጥያቄ መመለስ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ ጥያቄ በብዙ መልኩ ቢመለስም፣ መራጭ ዜጋው ከሚፈልገው መልስ አንዱ፤ አቋምን ሳይሆን ምክንያታዊ ኃሳብን የማስተላለፍ የፓርቲዎችን አቅም ነው፡፡ አንድን ያልተረጋገጠ ትርክት በመያዝ በተለያዩ መንገዶች ለማስረዳት ከመሞከር ይልቅ፤ አግባብነት ባለው፤ ተቀባይነት ባገኘ በተጨማሪም ከአጥጋቢ ማስረጃ በመነሳት ኃሳብ ይዞ ለመሞገት መሞከር፣ ከዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታው አልፎ የሀገሪቷን መፃዒ እጣ ፈንታ በማመላከቱ ረገድ የማይተካ ሚና ይጫወታል፡፡ ሌላው መራጭን ስሜታዊ ከማድረግና የስነልቡና ጫና ከማሳደር ይልቅ ምክንያታዊ በመሆንና ማስረጃ በማቅረብ፣ ሊተገበር የሚችል ሀገራዊ ኃሳብ ግልፅ በሆነ መንገድ አቅርቦ፣ የመራጭን ይሁንታ ለማግኘት መሞከር፣ መራጩ ትክክለኛ ምርጫ እንዲያደርግ በትልቁ ያግዛል፡፡
በተጨማሪም በምርጫ ሰሞን ስለ ሚደረጉት የምረጡኝ ቅስቀሳና በተወዳዳሪ የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል ስለሚደረግ ክርክር የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ እንደሚታወቀው የፖለቲካ ፓርቲዎች እነዚህን አበይት ጉዳዮች ለማስፈፀም የአንደበት ችሎታ ያላቸውን ግለሰቦች ይጠቀማሉ፡፡ በርግጥ መራጭን ለመማረክና አላማን በአግባቡ ለማስተዋወቅ የአንደበት ችሎታ ቢያስፈልግም፣ በቃላት የመጫወት ክህሎት ወይም ማራኪ የሆነ የአነጋገር ስልት ማወቅ ብቻውን አሸናፊነትን አያጎናጽፍም፡፡ ይልቁኑ ስለሚወራው ርዕሰ ጉዳይ አጥጋቢና የማያሻማ እውቀት መያዝ፤ ሐቀኝነትና ግልፅነት፤ የአቋም ወጥነት፤ ስህተትን ወይንም ድክመትን የማረም ዝግጁነት፤ ብሎም ስሜታዊ አለመሆንና አድማጭንም ስሜታዊ ያለማድረግ ባህሪያትን መጎናፀፍ ክርክሩን ከማሸነፍ ባለፈ የሀገሪቷን የፖለቲካ ባህል የመቀየር ጉልበቱ ኃያል ነው፡፡
ባጠቃላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫን ለማሸነፍ ብቻ የተለያዩ ስልቶችን ከመቀየስ ይልቅ አመለካከታቸውን እምነታቸውንና አሰራራቸውን በዲሞክራሲያዊ አኳኃን በማድረግ፣ የሀገሪቷን ሁለንተናዊ ሰላም፤ አንድነትና እድገት ለማረጋገጥ መትጋት ይኖርባቸዋል፡፡
መገናኛ ብዙኃን
የዲሞክራሲን ስርአት በመገንባትና ተግባራዊ በማድረጉ ረገድ የመገናኛ ብዙኃንም ሚና ልዩ ክብደት ሊሰጠው የሚገባ ነው፡፡ በተለይም በምርጫ ወቅት መራጭ ዜጋውም ሆነ የፖለቲከ ድርጅቶች የመገናኛ ብዙኃን ጥገኛ ስለሚሆኑ፤ የመገናኛ ብዙኃኑ ሚና በምርጫው ሂደት ላይ እጅጉን የላቀ ነው፡፡ ለምሳሌ ስለ ምርጫው ለህብረተሰቡ መረጃን በመስጠቱ በኩል፤ በምርጫው ዙሪያ ያለውን ግንዛቤ በማስፋቱ ረገድ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ከህዝቡ ጋር በማስተዋወቁ ብሎም፣ የምርጫውን አጠቃላይ ሂደት የመዘገብ ተልእኮ ይኖራቸዋል፡፡ ነገር ግን የመገናኛ ብዙኃን ጤናማ ካልሆኑ በምርጫው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራሉ፤ ምናልባትም የምርጫውን ውጤት እስከ መቀየር በሚደርስ፡፡ ምክንያቱም የመገናኛ ብዙኃን አጀንዳ የመቅረጽ ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ በተለይ በምርጫ ሰሞን ጎልተው የሚሰሙ ድምጾች በህዝብ ዘንድ የመስረጽ አቅም ስለሚኖራቸው ሚዛናዊነት አስፈላጊው ነገር ነው፡፡ ስለዚህም በተለይ ዘርፈ ብዙ የመረጃ ፍሰት ባለበት በዚህ ወቅትና አማራጭ የመገናኛ ብዙኃን በተስፋፉበት ዘመን፣ የመገናኛ ብዙኃን በልዩነትና በጥራት መስራት ይኖርባቸዋል። በመሆኑም የመገናኛ ብዙኃን ምርጫን የዜና ፍጆታ ከማድረግ በዘለለ ሰፊ ሽፋን በመስጠት፤ ዜጋው በጥልቀት ስለ ምርጫው ብሎም ስለ ፖለቲካ ፓርቲዎች ቁመና የሚኖረውን መረዳት የሚያዳብርበት መረጃ በማስረጃ መስጠት ይኖርባቸዋል፡፡ ነገር  ግን ቁም ነገሩ ሽፋን መስጠት ብቻ ሳይሆን በምን አይነት አግባብ የሚለው ነው፡፡ ለምሳሌ በጋዜጠኞች የሚሰጡ ቅድመ ሆነ ድህረ ምርጫ ትንተና፤ ብሎም የሚቀርቡ አስተያየቶች፣ በጥንቃቄና ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ምክንያቱም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሚዛናዊነት የጎደላቸው የፕሮግራም አዘጋጆች፣ የጋዜጠኝነት ስነምግባር የሌላቸው ግለሰቦች በአንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን ውስጥ እየተስተዋሉ በመሆኑ ነው፡፡ አንደ ማሳያ የሚሆኑት የድርጅት ልሳን የሚመስሉቱ የመገናኛ ብዙኃን ማለትም ግላዊ/ቡድናዊ አላማ አንግበው ፕሮግራም በመቅረፅ ራሳቸውን የርዕሰ ጉዳዩ አካል በማድረግ፣ ሚዛናዊ መረጃን ከማሰራጨት ይልቅ የግል/የቡድንን አጀንዳ የሚያስፈፅሙት ናቸው። ስለዚህም ስለ ምርጫው ትክክለኛነት ሲባል በምርጫ ዙሪያ ስለሚነሱት ሃሳቦች፤ ስለሚተላለፉበት መንገድ፤ የሰውነት ቋንቋና ድምፀት በአግባቡ መፈተሽና በጥልቀት ማጤን ከመገናኛ ብዙኃን ይጠበቃል። ድርጊቱ ባጠቃላይ ህዝቡ ለዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ እንዲነሳሳና በሰፊው እንዲሳተፍ ያግዛናልና፡፡
መደምደሚያ
ምርጫና መምረጥ መብትና አስፈላጊ ቢሆንም፣ መብትን መጠቀም በራሱ ትክክለኛነቱን አያሳይም፡፡ በመሆኑም ምርጫን ትክክለኛ የሚያደርገው መምረጥ ብቻ ሳይሆን ስለምንመርጠው የምንወስደው ኃላፊነት ነው፡፡ በርግጥ በምርጫው አለመሳተፍ ይቻል ይሆናል፤ ነገር ግን ሰዎች ስህተት በመፈጸማቸው ብቻ ሳይሆን እኛም ትክክለኛውን ነገር ባለማድረጋችን ተጠያቂ እንደምንሆን መገንዘብ ይገባል፡፡ ትክክለኛ ምርጫ በማድረግ፣ ነገ ይፈጠራል ብለን ለምናልመው ሁሉ በሃላፊነት ስሜት ልንወስን ይገባል፡፡ ለዚህም ያግዘን ዘንድ ሁላችንም ስለ ምርጫው ያለንን ንቃተ-ህሊና ማስፋትና ማሳደግ ይገባናል፡፡ ምንም እንኳን አንድ አይነት ስልጣን ቢኖረንም፤ ተመሳሳይ ግንዛቤ ስለሌለን፣ ካርዳችንን የምንጠቀምበት መንገድና የምንጫወተው ሚና የተለያየ ነው፡፡ አንዳንዶች በትክክለኛ ምርጫ ዲሞክራሲያዊ መንግስት ሲመሰርቱ፤ ሌሎች ደግሞ በተቃራኒው፣ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ፣ ኢ-ፍትሃዊ የሆነ መንግስት እንዲቋቋም የድርሻቸውን ያበረክታሉ። ስለዚህም በአስተውሎት ትክክለኛውን አማራጭ ማወቅና የፓርቲዎችን ፕሮግራም ጠንቅቆ መረዳት ለጥቂት ሰዎች ብቻ የሚተው ጉዳይ ባለመሆኑ፣ እያንዳንዳችን ኃላፊነታችንን ለመወጣት እንትጋ፡፡ ትክክለኛ የሆነ ምርጫን በማድረግም የምንሻትን ሀገር እንፍጠር፡፡


Read 1081 times