Saturday, 20 February 2021 00:00

ወራሪዋ ጣልያን በአዲስ አበባ የፈጸመችው ጭፍጨፋ (የካቲት 12 ቀን 1929)

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

  “--አየህ! የዚያን ዕለት ብዙ ጣሊያኖች ብዙ ሥራ ሠርተዋል፡፡ ወደ ማታ ገደማ ከአንድ ጓደኛዬ ጋር ስንገናኝ፣ ጓደኛዬ ቦምብ ስጥል የዋልሁበት እጄ ዝሏል ብሎ ነገረኝ። አንዱ ኢጣሊያዊ ሲያጫውተኝ፣ ባንዲት ትንሽ ጣሳ በያዝኳት ቤንዚን አስር ቤቶች አቃጠልኩበት አለኝ፤ በዋናው ጦርነት ጊዜ ጥይት ተኩሰው የማያውቁት ጣሊያኖች ሁሉ በዚያን ቀን ሲተኩሱ ዋሉ--”

           ይህ አንድ ስሙ እንዳይገለጽ የፈለገ ኢጣሊያዊ፣ ለጓደኛው ለሲኞር ዲሰማን የነገረውና  የታሪክ ጸሐፊው አንጄሎ ዲል ቦኮ የመዘገበው ሲሆን ደራሲ ጳውሎስ ኞኞም  “ኢትዮጵያና የኢጣሊያ ጦርነት; በተባለው መጽሐፉ ታሪኩን ለእኛ አድርሶታል። የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ላይ፣ በጣሊያን ወታደሮች የተፈጸመው ጭፍጨፋ ታሪክ ቀርቧል፤ በመጽሐፉ፡፡ በዚህ ወቅት በመዲናዋ  ለሦስት ተከታታይ ቀናት በጣልያን ጨካኝ ወታደሮች በተካሄደው ጭፍጨፋ፣ 30 ሺህ ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል፡፡ አንዳንዶች ይህ ቁጥር የሚታመን ነውን? የሚል ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡ ጥያቄውን ለመመለስ ከላይ የተጠቀሰውን ምስክርነት ይዘን፣ በወቅቱ በአዲስ አበባ የከተመውን የጣሊያን የጦር ሰራዊት ክምችት መመልከት ተገቢ ይሆናል።
ጳውሎስ ኞኞ፣  በወቅቱ የነበረውን የጣሊያን የወታደር ኃይል በመጽሐፉ ሲገልጽ፤ “35ሺ የጣሊያን ሜትሮ ፖሊታንት (የከተማው ወታደሮች)፣ 40ሺ ባለ ጥቁር ሸሚዝ ሚሊሺያ፣ 3ሺ የሊቢያ ተወላጅ ወታደሮች፣ 5ሺ የኤርትራ ወታደሮች ነበሩ፡፡; ብሏል፡፡ በተጨማሪም #የኤርትራ ተወላጅ ወታደሮች፤ “እኛ ወታደሮች ነን፤ መሳሪያ በሌለውና በሴት ላይ አንተኩስም” በማለታቸው ብዙዎቹ በሰፈራቸው ውስጥ ተገደሉ” ሲልም አክሎ ጽፏል፡፡ ከዚህ አንጻር 78ሺ የሚሆነውን የጣሊያን ሠራዊት፣ በጭፍጨፋው ላይ ከማሰማራት የሚያግደው ነገር አልነበረም፡፡
የኒፒልስ ልዕልት መውለዷን ምክንያት በማድረግ ጀኔራል ግራዚያኒ፣ ለድሆች ምፅዋት ለመስጠት በገነት ልዑል ቤተ መንግሥት፣ በአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ግቢ፣ ድሆች  እንዲሰበሰቡ ጥሪ አድርጎ ነበር።   እስከ እኩለ ቀን ባለው ጊዜም ሶስት ሺህ የሚሆኑ ድሆች ተሰበሰቡ፡፡ በዚህ ፕሮግራም ላይ ሰላሳ የሚሆኑ የጣሊያን ከፍተኛ ሹማምንቶች ተገኝተዋል፡፡ ይህን አጋጣሚ ራሳቸውን እያዘጋጁ ይጠብቁ የነበሩት አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም፣ ከነሱ ጀርባ የተሰለፉት ንጉሠ ነገሥቱ አፄ ኃይለ ሥላሴን ጨምሮ፣ ብዙዎች ጄኔራል ግራዚያኒን በመግደል፣ የጣሊያንን የወራሪነት ቅስም ለመስበር ቆርጠው ተነሱ፡፡ ጄኔራል  ግራዚያኒ፣ ለድሆችና በቦታው ለተገኙ ሰዎች ንግግር እያደረገ እያለ፣ እነ አብርሃም አከታትለው የእጅ ቦንብ ወረወሩ፡፡ ግራዚያኒ  ጀርባው ላይ ተመታ፡፡ የአዲስ አበባ ከንቲባ ጣሊያናዊው ጎይዶ ክርስቴና ሌሎች ሰላሳ ሰዎችም ቆሰሉ፡፡ ከሚወረወረው ቦምብ ለማምለጥ መሬት ላይ ተኝተው የነበሩት ከርቤጌሮች ከተኙበት ተነስተው ተኩስ ከፈቱ፡፡ ያገኙትን አበሻ ሁሉ እንዲገድሉ ከንቲባ ጐይዶ ክርስቴ ትእዛዝ ሰጠ፡፡ የጣሊያን ሹፌሮች ሳይቀሩ በአዲስ አበባ ከተማ እየተዟዟሩ ሕዝቡን ፈጁት፡፡ የቤተ መንግሥቱ ዙሪያ መንገዶች በሬሳ ተሞሉ። የመዲናዋ ቤቶች ከነዋሪዎቹ ጋር በእሳት ነደዱ፡፡ ነፍሳቸውን ለማትረፍ የሚሞክሩ ሰዎች እየተያዙ፣ ቤት እየተዘጋባቸው እንዲቃጠሉ ተደረገ፡፡ ለሦስት ተከታታይ ቀናት በተካሄደው በዚህ ጭፍጨፋ፣ ሰላሳ ሺህ ሰዎች እንደተገደሉ ነው የተመዘገበው፡፡  
እኔ በዚህ ቁጥር አልስማማም፡፡ መግቢያው ላይ ያሰፈርኩትን ምስክርነት ይዞ ነገሩን የሚገመግም ሰውም ይስማማል ብዬ አልጠብቅም፡፡ ከጣሊያን ጦር ውስጥ ከ15ሺ እስከ 20ሺ  የሚሆነው ለሰፈር ጥበቃ እንዲቀር ቢደረግና  ቀሪው ሃምሳ ሺህ ወታደር እንኳን አንድ አንድ ሰው ቢገድል፣ ያለ ጥርጥር  የተጨፈጨፉት ኢትዮጵያዊያን ቁጥር ሃምሳ ሺህ ይደርሳል፡፡
አዲስ ዘመን ጋዜጣ በአንድ ወቅት አዲስ አበባ ውስጥ የነበሩ የዓይን ምስክርን አነጋግሮ፣ የሟቾቹ  ቁጥር ከሀምሳ ሺህ እስከ ሰማኒያ ሺህ ሊደርሱ እንደሚችሉ በመጠቆም መዘገቡን አስታውሳለሁ። እኒህ ሰው እንደተባለው ጭፍጨፋው በሦስት ቀናት ውስጥ አለመቆሙንና ለወር ያህል መዝለቁንም ተናግረዋል፡፡  ከዚህ አንጻር የየካቲት ሰማዕታት ቁጥር 30 ሺህ ነው ማለት ትክክል አይመስለኝም፡፡ የደብረ ሊባኖስ መነኮሳት እልቂትም ሊዘነጋ አይገባም፡፡ የየካቲት 12 አንድ ገጽታ ነውና፡፡
ከሃምሳ ሺህ ሰዎች በላይ የተጨፈጨፉበት፣ ከአስር ሺህ በላይ ደግሞ ደናኔ ተወስደው በእስርና በበሽታ እንዲያለቁ የተደረገበት የየካቲት 12 ቀን መስዋዕትነት በከንቱ አልቀረም፡፡ ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም ለኢጣሊያ መንግሥት አልገዛም በማለታቸው፣ በአደባባይ በጥይት ተደብድበው በተገደሉት በአቡነ ጴጥሮስ ሞት ያኮረፈውን የአዲስ አበባን ነዋሪ፣ በየካቲት 12 ጭፍጨፋ፣ ጨርሶ ልቡ እንዲቆርጥና እንዲነሳሳ አድርጎታል። እጅግ የሚበዛውም ፊቱን ወደ አርበኝነት አዞረ፡፡ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ሳይቀር ለነፃነት በሚደረገው ትግል፣ የውስጥ አርበኛው እየተናበበ ሔደ፡፡
እንደ ሚያዚያ 27 የድል ቀን ሁሉ፣ በየዓመቱ ብሔራዊ በዓል ሆኖ ሲከበር የነበረው የየካቲት 12 ሰማዕታት ቀን፣ እየታሰበ መዋል ከጀመረ አርባ ስድስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ባለፉት ዓመታት አንድም የመንግሥት ባለሥልጣንም ሆነ መንግሥት ወደ ቀድሞ ክብሩ ሊመልሰው አልቻለም፡፡  
“ኢትዮጵያ የቆመችው በልጆቿ መስዋዕትነት ነው; እያልን እንዴት  ዓመታዊ  የሰማዕታት ቀን አይኖረንም?
ከ1928 እስከ 1933 ዓ.ም ድረስ በዱር በገደሉ ደማቸውን አፍስሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው ነፃነታችን ተከብሮ እንዲቆይ ያደረጉ የአምስት ዓመቱ አርበኞች፣ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ሰማዕት ናቸው፡፡
ሁለት ጊዜ የተቃጣውን የሞቃዲሾ ወረራ የመከቱ፣ የተጣሰውን ድንበር ያስከበሩና የሀገር ታሪክ እንዳይደፈር የተሰዉ ወገኖቻችን ሰማዕቶቻችን ናቸው፡፡
የጦርነቱ ምክንያት በግልጽ ባይታወቅም፣ ከኤርትራ ጋር በተቀሰቀሰው ጦርነት፣ ከአካል እስከ ሕይወት መስዋዕትነት የከፈሉ ወገኖቻችን ለሀገራችን ሰማዕት ናቸው፡፡
 ሰማዕታት ትናንትም ዛሬም አሉን፤ነገም መስዋዕትነት የሚከፍሉና ሰማዕታት የሚሆኑ ወገኖቻችንን  የምንዘክርበት የሰማዕታት ቀን የሚኖረን መቼ ነው? ሺህ ጊዜ የሚነሳ ጥያቄ!

Read 1445 times