Monday, 22 February 2021 08:22

ኑዛዜ ጸሃፊው ሽማግሌ

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(12 votes)

 ‹‹… በአንጎሌ የሚፈጠሩ ብዙ ቀልዶች አሉ፡፡ … ይፈጠሩና ራሴው ስቄባቸው ይረሱኛል፡፡ ለማስታወስ ስሞክር ተመልሰው ትዝ አይሉኝም .. ስለዚህ እንደ ዳየሪ ነገር ገዝቼ ልፅፋቸው ቅድም አሰብኩኝ፡፡ … ችግሩ ደብዳቤ እንኳን ፅፌ አላውቅም.. ቀ ልድ ደግሞ በ ደንብ ካ ልቀረበ ከ ስድብ የ ባሰ ያ ሸማቅቃል…›› ብ ላ ዝ ም አ ለች፡፡;
      
            ስብሰባው ላይ እየተካፈለች ነው። እየተካፈለች ያለችው ግን በአካል እንጂ በመንፈስ አይደለም፡፡ … ‹‹እናለማለን! … ለምተናል! … እንበለፅጋለን! በልፅገናል!...›› ወዘተ ነው ስብሰባው፡፡ በኢህአዴግ ዘመን ነው ተወልዳ ያደገችው… ጆሮዋ መስማት ሲጀምር ትዝ የሚላትም… የልማት ወሬ ነው። አሁንም ሥራ ይዛ መስራት ስትጀምርም ያው ነው፡፡ ስለዚህ የምታውቀው ዘፈን ስለሆነ አብራ አትዘፍንም፡፡
ሙሉ ጥሞናዋ ያለው ተንቀሳቃሽ ስልኳ ላይ ነው፡፡ ወንድ ስልክ ነገር ነው፡፡ ቀለሙም የሌሎቹን ሴቶች አይመስልም፤ ጥቁር ነው። ስክሪኑ ላይ በተጫነችው ቁጥር የመንዘር ምላሽ ይሰጣል፡፡ ስልኳ ወንድ ነው … እሷ ሴት ናት፡፡ ሚስጥር አይደባበቁም። በቁስ መልክ የተቀረፀ ነፍሷ ነገር ነው፡፡ በእጇ የሚያዝ ነፍስ፡፡ ከኤሌክትሪክ ቻርጅ በስተቀር ምንም ነገር አይፈልግም፡፡
አሁን ስብሰባው ውስጥ ከጎኗ የተቀመጠው ሽማግሌ፣ ሂሳብ ክፍል ሠራተኛ ነው፡፡ ለምን እስካሁን ጡረታ እንዳልወጣ አታውቅም፡፡ መነፅርና ፂም የለውም እንጂ መላጣው የሲግመንድ ፍሮይድን ይመስላል… ብላ ከሳቀች ቆይታለች፡፡
መስሪያ ቤቱ ውስጥ ጥግ ጥጉን ጃንጥላውን ይዞ ሲጎተት ታየዋለች፡፡ … የሚያደርገውን የሚያውቅ አይመስላትም ነበር፡፡ በእርጅና ምክንያት በህይወትና ሞት መሀል ነገር አለሙን ረስቶ የሚመላለስ ነበር የሚመስላት፡፡
ግን በስብሰባው እለት ከጎኗ ተቀምጦ በአርቴፊሻል ጥርሱ ሲያወራላት … በአእምሮ እንዳለና ብዙ ነገር እንደሚያውቅ ተረዳች። እሷ እንደሚመስላት አራት መንግስታት ቆርጥሞ የበላም አይደለም፡፡ በንጉሱ ዘመን እንደሷ እድሜ ሳለ ገዳም ነበረ፡፡ ነበርኩ ብሎ አጫወታት፤ በስብሰባው መሀል፤ በአርቴፊሻል ጥርሱ፡፡ ሼባውም እንደሷው ስብሰባው ውስጥ በአካል እንጂ በመንፈስ የለም፡፡ የለም እንጂ… ያሉት የሚያወሩትን በሌለበት ሆኖ ልቅም አድርጎ እንደሚሰማ አኳኋኑ ያስታውቅበታል፡፡ … አንዳንዴ በመሀል ትንሽ ደብተር ከጉያው ያወጣና በሚንቀጠቀጥ እጁ የሆነ ነገር ይከትባል፡፡
የሚፅፈውን አይኗን አሻግራ ለማየት ሞክራ አልነበብ ሲላት ትታዋለች፡፡ ብቻ የሚፅፋቸው ፊደሎች እግራቸው በሆነ ሞገድ የተመቱ ይመስል ዚግዛግ ናቸው፡፡ በተረፈ ግን ከግራ ጀምሮ ወደ ቀኝ እንደሚፅፉ (ፍ?) … ቀኝ ሲደርሱ (ስ) እንደሚመለስ (ሱ) አስተውላለች፡፡ … “እሱ” ወይንስ“ እሳቸው” ብላ ለመወሰን በሥራ በመወጠሯ ምክኒያት እስካሁን  አልቻለችም፡፡
‹‹ጋሽ ፋንቱ ምንድነው የምትፅፈው?›› ብላ ስትጠይቀው… ድምፅዋ በአዳራሹ ውስጥ እንዳይጎላ፣ ጆሮዋ ላይ ያደረገችውን ማዳመጫ ነቀለችው፡፡ ሽማግሌው አልሰማትም፡፡ ጆሮው ችግር ሳይኖርበት አይቀርም ብላ ትገምታለች፡፡ ሲፅፍ ግን የሆነ ከረሜላ እየበላ ነው፡፡ አፉን በየአቅጣጫው ጅምናስቲክ ያሰራዋል፡፡
ፅፎ ከጨረሰ በኋላ ወደሷ ጆሮ ተጠግቶ ‹‹ኑዛዜዬን እየፃፍኩ ነው›› ብሎ ጠቀሳት። የእነሱ ዘመን አጠቃቀስ ሁለቱንም አይን አንድ ላይ በመጨፈን የሚከናወን ነው፡፡ አይኑን እየጨፈነ ከገለጠ በኋላ፣ በአንድ እጁ መዳፍ ያሞጠሞጠውን ከንፈሩን እየደበደበ ‹‹ለማንም እንዳትተነፍስ…›› እንደ ማለት አስጠነቀቃት፡፡ ቅድም የጆሮውን ብቃት ተጠራጥራ ነበር፡፡ ከዚህ ቀደም ደግሞ… በህልውና ላይ እየተሳተፈ ስለመሆኑ ያውቃል ወይ? ብላ ትጠራጠረው ነበር፡፡ ሁለቴ ተሳስታለች፡፡ ሰውየው የዋዛ አለመሆኑን መቀበል ጀምራለች፡፡ እንዲያውም ትንሽ ትንሽ እሱን መውደድ ሳትጀምርም አልቀረችም፡፡… እንጃ ገና ስለምኑም እርግጠኛ አይደለችም፡፡ በመስሪያ ቤት ህይወቷ ስለ ማንም ሰው ያላት ስሜት ፍዝ ነው፡፡ ሁሉንም እኩል ነው የምታያቸው፡፡ በሁሉም እኩል ነው ሙድ የምትይዝባቸው። ሰው አይመስሏትም፤ እሷን ለማዝናናትና ቀልድ ፈጥራ በውስጧ እንድትስቅ ለማድረግ ፈጣሪ ‹‹አንች የዋልሽበት ይዋሉ›› ብሎ የሰጣት አሻንጉሊቶቿ ናቸው፡፡ ከሁሉ የሚያስቃት ደግሞ የቅርብ አለቃዋ ነው፡፡ በትንሽ በትልቁ መጨነቅ የሚወድ ነው፡፡ አንድ ቀን የሴቶች ሽንት ቤት ተበላሽቶ የነበረ ጊዜ፣ የወንዶቹ ሽንት ቤት ስትገባ አጅሬው ሽንቱን ቆሞ መሽናት አቃተው፡፡ እሷም አውቃ.. .ሆን ብላ በመስታወት ፊቷን የምታይ መስላ… ማፍጠጥ ቀጠለች፡፡ ሽንቱን ሳይጨርስ ዚፑን ቆልፎ እየተመናጨቀ ወጣ፡፡
የአለቃዋ የዛ ቀን ሁኔታ ወር ከመንፈቅ አሳቃት፡፡ … ለራሷ … ‹‹ሽንቱን ሳይጨርስ ደንብሮ እንደሮጠው ግርዛቱንም መሀል ላይ ሳያቋርጠው አልቀረም›› እያለች በሳቅ ስትፈነዳ ከረመች፡፡ … ከሽንት መሽኛው ቅርፅ ተነስታ ቅፅል ስም አወጣችለት፡፡
‹‹ትንሽ ይሄ ቤንች (*ሽማግሌ) ግን ከሌሎቹ ይሻለኛል›› አለች ለራሷ፤ እዛው ስብሰባው መሀል ተቀምጣ በስልኳ የዘፈን ክሊፕ በጆሮ ማዳመጫ አድርጋ እየሰማች፡፡ እግሯን በመጠኑ ከዘፈኑ ጋር እያወዛወዘች... ትንሽ ስለ ሽማግሌው ማሰብ ጀመረች፡፡ ማሰብ የጀመረችው ስለምታውቀው የሱ ታሪክ አይደለም፡፡ ገንዘብ ክፍል የትርፍ ሰዓት የሰራችበትን ሂሳብ ለማሰራት ስትሄድ፣ ብቻውን አንድ ክፍል ተነጥሎ ተሰጥቶት፣ ጠረጴዛ ላይ አጎንብሶ ሲፅፍ ታየዋለች። ከዚህ በተረፈ ስለሱ የምታውቀው ነገር የለም፡፡ ምናልባት እንደሷ ነገር አለሙ የማይጥመው ሰው መስሎ ስለታያት ሊሆን ይችላል የተመቻት… ለጊዜው ስለ ምንም ነገር እርግጠኛ አይደለችም፡፡ … ስሜቶቿን ገና መርምራ ኢንቨንተሪ አልሰራችም፡፡ … ሳያቋርጥ ከረሜላ የሚያላምጠው ለምን እንደሆን ድንገት ማወቅ ፈለገች፡፡
‹‹ጋሽ ፋንቱ፤ ይሄንን ከረሜላ መቼስ ከጠዋት የጀመርክ ትለዋለህ… እንደው በባህላችን እንብላ ይባላል እኮ›› አለችው፡፡
ጋሽ ፋንቱ ከት ብሎ ሳቀ፡፡ በአርቴፊሻል ጥርሱ፡፡ እሷ ግን ጥርሱ አርቴፊሻል መሆኑን ገና አላወቀችም፡፡ ‹‹ይሄ ሽማግሌ እንዴት ጥርሱ ያምራል፡፡ … ጥርሱን ሳያጎድል ነው እድሜውን እንደ ሙዝ ልጦ የበላው›› እያለች እየተገረመችበት ነበር፡፡
‹‹አይ ከረሜላ … ከረሜላማ እናንተ እናንተ ናችሁ… ጣፋጭ ከረሜሎቹ፡፡ እኔ ይሄንን ሰው ሰራሽ ጥርሴ ውስጥ የገባውን የምግብ ቁርጥራጭ ለማፅዳት ስሞክር ነው … ከረሜላ እያላመጥኩ የመሰለሽ… ምነው ሰቀጠጠሸ… አስፈራሁሽ እንዴ?››
መልሳ ጆሮዋ ላይ ሙዚቃዋን አደረገችው። በእውነትም በጥቂቱ አስፈርቷታል፡፡ የሆነ ሆረር ፊልም ነገር አለው፡፡ ድንገት ከአፉ ውስጥ መደዳ ጥርሱን አውጥቶ እጁ ላይ ይዞ… በድሮው የስሙኒ፣ በዘንድሮው የብር መፋቂያ እንደ ሊስትሮ ሲወለውል ታያትና … ሳቅ አመለጣት፡፡ ከብዙ የሚያስፈሩ ወይንም ያልገቧት ነገሮች የምታመልጠው በምናቧ ያንን ያስፈራትን ነገር ወደ ሳቅ ስትቀይረው ብቻ ነው፡፡ በተረፈ አለሙ በሙሉ ኮስተር ብሎ ልመልከተው ካሉት፣ ከላይ ታች ሆረር ነው፡፡ ግን እሷ ያንን የአለም መአት ሆረር፣ ወደ ሙሉ ቀልድ ትለውጥና እፎይታን ታገኛለች፡፡
… እና ሳቀች… ካልሆነማ በየት በኩል መኖር ይቻላል? …
 ለሶስተኛ ጊዜ መሳሳቷን አረጋገጠች፡፡ … ቤንቹ ከረሜላ እየበላ ነው ብላ ያሰበችውም ልክ እንደ ቀድሞ ግምቶቿ ስህተት ሆነ፡፡ ያም ሆነ ይህ ሽማግሌውን አልጠላችውም፡፡ ‹‹… ለነገሩ ጥርስ ምን ያደርግለታል?… የሚጋጥ ነገር በአገሩም አልቋል ...እሱ እንዲያውም እድለኛ ነው… በደህና ዘመን ከራሱ ትውልድ ጋር በጥሩ ጥርስ ተናክሰው ተናጭተው… ተገልግለውበት እፎይ ብለዋል፡፡ … እኛ አለን አይደል… ጥርሳችን ደክሞብን … በወጉ መናከስ እንኳን ያልቻልን፡፡ … እንደ አለቃዬ … እንደ ‹‹ሶምብሬሮ›› የትውልድ ተናጋሪዎቼ በሙሉ ሀሞታቸው የፈሰሰ ነው፡፡… ሽንታም ሆነው እንኳን … ሽንታምነታቸውን አምነው… አንገታቸውን ቀና አድርገው፣ በሰው ፊት መሽናት የሚያፍሩ …›› እያለች እያሰበች…
ሳታስበው ወደ ምሬት ልትዘም መሆኑ ሲገባት፣ አዕምሮዋን ለሌላ ቀልድ ቃኘችው። … ቀልድ ፈጥራ የምታካፍለው ራሷን ነው። እንደ ዘመኑ ወጣቶች በማህበራዊ ድረ ገፅ መገኘት አትፈልግም፡፡ የፌስቡክ ገፁን እንዲያውም ከፍታው አታውቅም፡፡
…አንድ ቀልድ ወዲያው ፈጠረች.. ወይንም ለቀልድ ስትዘጋጅ አእምሮዋ ቀልዱን ፈጥሮ አቀረበላት፡፡ ለሽማግሌው ቀልዱን ልትነግረው ፈለገች፡፡ ግን እንደማይገባው ጠረጠረች፡፡ አፍራው ወይንም ፈርታው አይደለም፡፡ የጎንዮሽ አየችው፡፡ ኑዛዜውን ተግቶ እየፃፈ ነው፡፡ አሁንም ጭንቅላቷ ሌላ ቀልድ ሰነዘረ፡፡ በሁለት እጇ አፏን አፍና ‹‹ኩ…ፍ…ፍ›› ብላ ከመሳቅ ተረፈች። አእምሮዋ አንድን እይታ በቀላሉ ወደ ቀልድ ለመቀየር እንዲችል አድርጋ ለዘመናት አደርጅታዋለች፡፡      
ገና ሰውየው እየፃፈ መሆኑን አይታ … ‹‹ኑዛዜውን እየፃፈ›› ብላ ከማሰቧ ጭንቅላቷ … “ምናልባት ኑዛዜውን መፃፍ የጀመረው በልጅነቱ መፃፍ የቻለ እለት ሊሆን ይችላል” ብሎ አፀፋውን ሲመልስለት ነው፣ ድንገተኛው ሳቅ ያመለጣት፡፡ አፍና… በአፈነችው ቁጥር እየገነፈለ ሰዓት በላባት። … ሳቅ ሳይሆን ስርቅታ ይመስል በስንት ማባበል አረጋጋችው፡፡ … ሊገነፍል ያለውን ሳቅ አረጋግታ … ስትጨርስ ለሳቁ መንስኤ የሆነው ቀልድ ራሱ ተዘንግቷታል፡፡
ስብሰባው እንደቀጠለ ነው፡፡ … ምናልባት እኔም ሙዚቃው ቢበቃኝና እንደ ሼባው … ኑዛዜዬን ብፅፍ ምን ነበረበት… ብላ አሰበች። … የምን ኑዛዜ? … እኔ እንዲያውም መፃፍ ያለብኝ በአእምሮ በቀላሉ የሚራቡትን ቀልዶች ነው፡፡ … ደግሞ እኮ የሚገርመው ቀልድ ሲቀለድ መስማት የምወድ አይደለሁም። የቀልድ ፊልሞችማ ያበግኑኛል፡፡ … እኔ የምወደው የራሴን ቀልዶች ብቻ ነው፡፡ … ታዲያ የራሴን ቀልዶች ለሌላ አድማጭ ለማውረስ ነው የምፅፋቸው? … እንደ እነ ‹‹ሶምብሬሮ›› የመሰሉ ሰዎች መች ቀልድ ይገባቸዋል፡፡ እነሱ ጭንቀትን እንደ አሜባ ማራባት ነው የሚችሉበት፡፡ … ብቻ ልፃፈው … ቢያንስ ለራሴ መልሼ ሳነበው ያዝናናኝ ይሆናል። … የፈጠርኩት ቀልድ ስቄበት ስጨርስ እየጠፋኝ ተቸግሬአለሁ፡፡ እንዲያውም …›› እያለች እያሰበች ሳለ፣ የቀኑ ስብሰባ ተጠናቋል ተባለ፡፡
‹‹ጋሽ ፋንቱ፤ ፅሁፉ እንዴት እንደሚፃፍ እስቲ አጭር ስልጠና ስጠኝ›› አለችው፤ አብረው ተያይዘው ከአዳራሹ እየወጡ ሳለ፡፡ በአርቴፊሻል ጥርሱ ፈገግ እያለ “ምን ልትፅፊ ፈለግሽ” አላት፡፡ ልጅ እንደሚያናግር አዋቂ ሰው …ጉንጯን ቁንጥር አድርጎ ለመሳም እንደቋመጠ… እየተቁነጠነጠ፡፡
አሁንም ጭንቅላቷ መሀል መንገድ ቀልድ ሊፈጥር ሲል፣ የራሷን ግንባር በራሷ እጅ መታ መታ አድርጋ አባረረችው፡፡ ቀልዱ ጭራውን እግሩ መሀል ሸጉጦ የሆነ የአእምሮዋ ጓዳ ያለ ስርቻ ውስጥ ተቀመጠ፡፡ ስርቻው ውስጥ ተሸጉጦ እንደ ውሻ ሲቆጣ ትሰማዋለች፡፡ ፊት ሳትሰጠው ወደ ጋሽ ፋንቱዋ አተኮረች፡፡
‹‹…በአንጎሌ የሚፈጠሩ ብዙ ቀልዶች አሉ፡፡ … ይፈጠሩና ራሴው ስቄባቸው ይረሱኛል፡፡ ለማስታወስ ስሞክር ተመልሰው ትዝ አይሉኝም .. ስለዚህ እንደ ዳየሪ ነገር ገዝቼ ልፅፋቸው ቅድም አሰብኩኝ፡፡ … ችግሩ ደብዳቤ እንኳን ፅፌ አላውቅም.. ቀልድ ደግሞ በደንብ ካልቀረበ ከስድብ የባሰ ያሸማቅቃል…›› ብላ ዝም አለች፡፡
‹‹ልክ ነሽ… ጥሩ አባባል ነው… ቀልድ በደንብ ካልቀረበ ከስድብ የባሰ ያሸማቅቃል.. ምን ችግር አለ አሳይሻለሁኝ፡፡ … ግን እኔ የማውቅበት የኑዛዜ አፃፃፍን ነው… በኋላ ቀልድሽ ኑዛዜ መስሎ እንዳይበላሽብሽ›› አላት ሽማግሌው፡፡ ሽርኳ፡፡
ብዙ እርዳታ እንደማትፈልግ ‹‹ትንሽ መንገዱን ከጠቆምከኝ ይበቃል››… ወዘተ ብላ ለእለቱ ተለያዩ፡፡ ለሚቀጥለው ቀን እንደ ስልኳ… ጥቁር ሽፋን ያለው፣ እንደ ሴታ ሴቶቹ በአበባና በሮዝ አበባ ያልተንቆጠቆጠ ማስታወሻ ደብተር ገዝታ መጣች፡፡

Read 2307 times