Print this page
Monday, 22 February 2021 08:36

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(2 votes)

 ብዙዎቻችን “ማየት ማመን ነው” ብለን እናስባለን። ታላቁ ሞርቲ ግን ላቅ ብሎ ነገሮችን የመመርመር ችሎታና ልምድ ነበረው። በዓይን ስላየን ወይም በጆሮ ስለሰማን ብቻ ነገሮች እንዳሰብነው ወይም እንደገመትነው ይሆናሉ ማለት ምክንያታዊነታችንን ያጎድለዋል ባይ ነው። ለዚህ ደግሞ በስነ-ፍጥረት ባህሪያት፤ በማህበራዊ ሳይንስም ሆነ በጥበብ መድረኮች የተከናወኑ ምሳሌዎችን መጥቀስ አይገደውም። ለምሳሌ እንጉዳዮች ስናያቸው አንድ አይነት ይመስላሉ። ስንመረምራቸው ግን አንዳቸው ለህይወት መኖር ሲጠቅም ሌለኛው ይገድላል። ይኸ ልዩነት እንደ ቫይረስና ባክቴሪያ በመሳሰሉ ጥቃቅን ህዋሳት ላይም የተለመደ እንደሆነ ሰውየአችን ያስታውሰናል።
ወዳጄ፡- የምናያቸውና የምንቀምሳቸው ነገሮች ብቻ ሳይሆኑ በጆሯችን በኩል ወደ አእምሯችን የሚሾልኩ ወይም የምንሰማቸው ነገሮችም ካልተመረመሩ ጥቅምና ጉዳታቸው የዛኑ ያህል ነው። ሊገድሉም ፣ ሊፈውሱም ፣ ሊያሳዝኑም ሊያስደስቱም ይችላሉ።
የትልልቆቹ ባህላዊ እምነቶች አባት (THe great patrarich) የሚባለው አብርሃም በመቶ አመት እድሜው ወንድ ልጅ የተፀነሰለት መሆኑን ጆሮዎቹ የምስራች ሲያሰሙት የተሰማውን ደስታና እስከ ዛሬ ድረስ የቀጠለውን ህያውነት ወይም በኦቴሎ ጆሮዎች ሲዥጎደጉድ የነበረውን የሃሰት መርዝና ያስከተለውን ዘግናኝ ትእይንት ማሰብ እንደ ምሳሌ ኢምንት ነው። ለፈላስፋው ሞርቲ ማየትና መስማት እውነትን ፈልጎ ከማግኘትና ካለማግኘት ወይም ከማወቅና ካለማወቅ ጋር የሚጣረስበት አጋጣሚ ብዙ እንደነበር ይነገራል።
የሞርቲ ስም ሲነሳ ብድግ ቁጭ ከሚሉ የፍልስፍና ቀልዶች አንዷን ላውራችሁ፡- አንድ ቀን ሰውየው ከነበረበት ቆይታ ወደ መኖሪያ ቤቱ ሲመለስ፣ ሚስቱና የቅርብ ጓደኛው ሉ (Lou) ራቁታቸውን ሲጨዋወቱ አገኛቸው። ሞርቲ በተመለከተው ነገር ተደናግሮ ሳለ ሉ ፈጠን ብሎ፡-
“ሞርቲ አንዲት ቃል ሳይወጣህ በፊት ጥያቄ አለኝ” አለው።
“ምንድን ነው?” ሲለው አስተሳሰቡን የሚፈትን ነገር ጠየቀው።… ምን ይሆን?
***
ወዳጄ፡- ጦርነት በዚህ ዘመን የማያዋጣ ቢዝነስ እየሆነ ነው።… አያተርፍም። ትርፍ የሚገኘው ሃሳብን ቴክኖሎጂ ላይ ኢንቨስት በማድረግ የብዙሃኑን ችግር መቅረፍ ሲቻል ሆኗል። ቴክኖሎጂ በትንሽ ቦታ ላይ ብዙ ማምረት አስችሏል፣ ሸቀጥ ግብይትን በማቀላጠፍ ጊዜን ከማባከን አድኗል። የፈለጉትን ሰውና መረጃ በቀላሉ ማግኘት አያዳግትም። ግን ደግሞ ከተፈበረከበት አላማ ውጭ ልንገለገልበት እንችላለን። የሃሰት ማስረጃ የማሰራጨት ተግባርና የመሳሰሉ ወንጀሎች መተግበሪያ ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ አለ። በሌላ አነጋገር፤ ውሃ፣ ቡና ወይም ወተት በምንጠጣበት እቃ መርዝ መበጥበጥ እንደ ማለት ነው። መርዝ ቀማሚዎችን ሽሽት ደግሞ  ብርጭቆውን የሚሰብር የለም።
ወዳጄ፡- ባለፉት ዓመታት የኢንተርኔት አገልግሎትን ተጠቅሞ የሃሰት መረጃ የሚያሰራጭን ሰው ወይም ድርጅት ፈጥኖ መለየት ቀላል አልነበረም። አሁን ግን ማን ምን እንዳለና የት ሆኖ እንዳደረገ ማወቅ ተራ ነገር እየሆነ ነው። በሺ በሚቆጠሩ ማይሎች ርቀት ላይ ሁኖ አጥፊው ይለያል።… እንደ ስፔስ አርኪዎሎጂ!
ስፔስ አርኪዎሎጂ ቀደም ሲል የነበረውን የሰው ልጅ የአኗኗር ባህል ፣ ታሪክና እምነት፣ ከተፈጥሮ ጋር ያለውን ቁርጠኝነት ለማጥናት ለቁፋሮና ለምርምር የሚሆኑ መገልገያዎችን በማጓጓዝ ንዳድ በሚያመነጩ በረሃዎችና አጥንት በሚሰብሩ ቀዝቃዛ ቦታዎች የሚደረገውን መንከራተት አስቀርቷል፡፡
ስፔስቴክኖሎጂ ረቂቅ መሳሪያዎች በመጠቀም ከአየር ላይ በተነሱ የሳተላይት ምስሎችን በማደራጀትና በመመርመር ታሪክን በተጨባጭ ማስረጃ ማረጋገጥ የቻለ አዲስ ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት ዶክተር ሳራ የተባለች ባለሙያ፣ ለቢቢሲ ሬዲዮ በሰጠችው መግለጫ፤ የሰው ልጅ እስከዛሬ ድረስ ስለ ራሱ፤ ስለ አካባቢውና ስለ ተፈጥሮ ካወቀውና ከተረዳው ይልቅ የማያውቃቸው ነገሮች በልጠው እንደተገኙ በጥናትና በአዳዲስ ግኝቶች መረጋገጡን አስረድታለች፡፡
ወዳጄ፡-“ፋኖ ተሰማራ” የሚዘመርበት፣ ዋሻ ውስጥ ተደብቆ በጄኔሬተር በሚሰራ ሬዲዮ የፖለቲካ ቅስቀሳ የሚደረግበት፣ በስቴንስል በተባዛ ፓምፍሌት መረጃ የሚተላለፍበት ጊዜ አልፏል፡፡ በዚህ ዘመን የሃሳብ ልዩነትን በውይይት መፍታት አለመቻል፣ በግድያና በማስፈራራት በተቃዋሚ ወገን ላይ የበላይነት ለማሳየት መሞከር ፍፁም ውንብድና እንጂ ፖለቲከኛ አያሰኝም፡፡ ምክንያቱም የዚህ ዘመን ታሪክ የሚመዘገበው እንደ አቲላ ዘሀን፣ እንደ ጂንጂስካን ወይም እንደ እስማኤል አልፓሻ  የግለሰቦች ታሪክ ሳይሆን የቴክኖሎጂና  የሃሳብ ብልጫ በማህበረሰቡ ኑሮ ላይ ያመጣው ዕድገት ተመዝኖ ነው፡፡
ወዳጄ፡- ሞባይል ስልክ በኪስህ ይዘህ ተደብቄአለሁ ማለት ያለንበትን ዘመን ወይም የሰው አእምሮ የደረሰበትን የዕድገት ደረጃ አለመረዳት ነው፡፡ “ዝሆን ሰርቆ አጎንብሶ” እንደ ማለት ነው፡፡
ጣዖታት እንዴት እንደተፈረካከሱ፣ ሁዋላ ቀርነት ለስልጣኔ መንገዱን ተገዶ እንደለቀቀ ስፔስ አርኪዮሎጂ ይነግረናል፡፡
ወዳጄ፡- ቴክኖሎጂ ለዘመናት የነበረውን የቢዝነስ አሰራር ስርዓትና ደንብ ቀይሮታል፡፡ አሮጌው የንግድ ልውውጥ “ማኑዋል” በአዲስ ተተክቷል፡፡ ለምሳሌ፡- አንድ አገር ላይ የተፈበረከ ዕቃ (መኪና፣ቲቪ፣ ልብስ ወዘተ ሊሆን ይችላል) ለሌሎች ሀገራትና ህዝቦች የሚደርሰው በባህርና በየብስ በሚጓዙ ትላልቅ የጭነት ማጓጓዣዎች አማካይነት ነበር። ከትራንስፖርት፣ ኢንሹራንስና የተለያዩ አገልግሎት ክፍያዎች በተጨማሪ ለጊዜ ብክነት፣ ለተፈጥሮ ሰው ሰራሽ አደጋዎች (የሶማሌ ፒሬቶችን ልብ ይሏል) የተጋለጠ ነው፡፡ አሁን ግን ሸማች አገሮች የሚገዙት ወይም የሚያሰመጡት ዕቃውን ሳይሆን የሚያመርቱበትን ፈቃድና የብራንድ ሰርተፊኬቱን ብቻ እየሆነ ነው፡፡ እዚህ ጋ ልብ ማለት የሚያስፈልገው የመጀመሪያዎቹ አምራቾች ስራውን ለሌሎች እያስተላለፉ እነሱ ስለ ተሻለ ቴክኖሎጂ የሚያስቡበት ጊዜ ማትረፍ መቻላቸው ነው፡፡ አንዳንድ አገሮች ራሳቸው እንዲሰሩፈቃድ ከሰጧቸው ሌሎች አገሮች ወይም ነጋዴዎች የራሳቸውን ዕቃ መልሰው ሲገዙ ብናይ፣ ለምሳሌ የቻይና ዕቃ የአሜሪካንን ገበያ ማጥለቅለቁን ብንመለከት ልንገረም እንችላለን…. ሚስጢሩ የተደበቀው የሃሳብ ብልጫ ወድድር ውስጥ መሆኑን እስካልገባን ድረስ!
ወዳጄ፡- ኮረና ቫይረስ ከቻይና ሁዋን ተነሳ ወይም ከአሜሪካ ላብራቶሪ አፈተለከ የሚባለው ንትርክ ወይንም ከትናት ወዲያ እንዳየነው የአሜሪካ መንኮራኮር በሰዓት 20,000 ማልይስ እየከነፈች በሰባት ደቂቃ ወስጥ ማርስ ላይ ቂብ ብላ ጥናት ላማካሄድ መዘጋጀቷ የሃሳብ ብልጫ እሽቅድድም እንጂ ከቶ ምን ሊሆን ይችላል?.... የኛስ ፖለቲከኞች መሽቀዳደሚያቸው የሃሳብ ብልጫ ለማምጣት ካልሆነ ምን ይበጃል?
***
ወደ ቀልዳችን ስንመለስ፡- ለጓደኛው ሞርቲን “እኔን? ወይስ ዓይንህን ነው? የምታምነው? “ በማለት ነበር የጠየቀው?
ሰላም!



Read 1431 times