Sunday, 28 February 2021 00:00

ስትወቃ የዘፈነች ስትፈጭ ምን ልትል ይሆን?

Written by 
Rate this item
(5 votes)

  አንድ የቻይና ተረት አለ።
አንዲት ዝይ (Goose) ሣር ቅጠል ባለበት ቦታ ስትለቃቅም አንድ ፈረስ ከጎኗ ሲግጥ ትመለከታለች። ወደሱ ጠጋ ብላ ኩራት ባለበት ቅላጼ፡- “እንደምታውቀው እኔ በጣም የተከበርኩና ፍጹም የሆንኩ የዶሮና የወፍ ዘር ነኝ። ያንተ ችሎታ አንድ ብቻ ነው። እኔን ግን እስቲ አስተውለኝ። እንዳንተ በመሬት ላይ መንቀሳቀስ እችላለሁ። በአየር ላይ ለመንሳፈፍ ብፈልግም ይኸው ቆንጆ ቆንጆ ክንፎች አሉኝ። ባስፈለገኝ ሰዓት ደግሞ በኩሬ ወይም በሐይቅ ውስጥ ገብቼ አየዋኘሁ እራሴን በቀዝቃዛው ውሃ ውስጥ ለማዝናናት እችላለሁ። አየህ እንግዲህ ሲሻኝ የወፎችን፣ ሲሻኝ የአሳዎችንና ሲሻኝ ደግሞ የባለአራት እግር እንስሳትን ችሎታ የተካንኩ በመሆኔ የሶስቱንም ስልጣን እጠቀምበታለሁ” አለችው። ፈረሱም በጥላቻ መንፈስ መለሰ፡- “እርግጥ ነው ሶስት ችሎታዎች አሉሽ። ነገር ግን ከሶስቱ በአንደኛውም ይህ ነው የሚባል ተለይተሽ የምትታይበት ስራ ሰርተሽ ስትመሰገኝበት አላየሁም። በአየር ትበሪያለሽ። ግን
አበራረርሽ የትም የሚደርስ አይደለም። በዚያ ላይ እንዳው በግዙፍ ሰውነትሽ መንደፋደፍ ነው እንጂ ቁልጭ ባለ ሁኔታ የምትከንፊ አይደለሽም። እንደ ወፎቹ ከፍ ያለ ዛፍ ላይ ወጥተሽ አትታይም። በውሃ ላይ መንሳፈፍ ትችያለሽ ግን እንደ አሣዎች በውስጡ ለመኖር አትችይም። ም ግብሽንም ከ እዚያው
አትመገቢም። ወ ይም ማ ዕበል ሲ መጣ ው ስጥ ለውስጥ ለመሄድ አትችይም። በመሬት ላይ ስትሄጂም አቅል ባለው ሁኔታ መሄድ ሳይሆን ውልግድ- ውልግድ እያልሽ መንደባደብ ነው እንጂ በአግባቡ ቀጥ ብለሽ ስትሄጂ አልታየሽም። በዚህ በሰፋፊ እግርሽ ደምበር ገተር እያልሽ አንገትሽን አስግገሽ ስትሄጂ
ከመንገደኛ ጋር ስትጋጪና ስትተሻሺ ነው የምትውይው። እኔ በእርግጥ በመሬት ላይ ብቻ ለመሄድ የተፈጠርኩ እንስሳ ነኝ። ግን ግርማ ሞገሴን እስቲ ተመልከቺው! የአግሮቼን ቅርጽና ጥንካሬ ተመልከቺ! የመላ አካላቴን ቅርፅና ቁመና ተመልከቺ! ጉልበቴን አጢኚ! ፍጥነቴ ምን ያህል እንደሆነ እስቲ ልብ በይ! እንዳንቺ በሶስት በአራት ነገር ታውቄ ፣ በአንዱ በቅጡ ሳይሳካልኝ ከመቅረት፣ በአንዱ በደንብ ታውቄ ብጠራ ይሻለኛል! “ ሲል ነገራትና እየተጎማለለ ጥሏት ሄደ።
* * *
በሀገራችን የታዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ድርጅቶች ቢያንስ ሶስት መሰረታዊ ደካማ ባህሪያት እንዳሏቸው ለመገመት ይቻላል። አንደኛው ቅድመ- ዝግጅት አለማድረግና ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ ማለት ነው። ሁለተኛው የመቻቻል ዲፕሎማሲ ማጣት ነው። ሶስተኛው ዛሬም ትኩረት ይፈልጋል። አስተውሎትን ሰብስቦ፣ አቅል ግዝቶ አንዱን ተግባር በአንድ ወቅት ማከናወን እጅግ አስፈላጊ ነው። አለበለዚያ እንደ ዝይዋ መብረርም፣ መዋኘትም፣ መሮጥም እችላለሁ ብሎ አንዱን ሳያጠብቁ ያለመያዝ አደጋ ላይ ይጥላል። በተነሱ ጥያቄዎች ላይ ሁሉ ቀልብንና አካልን መበታተን ዋናውን መንገድ እንደሚያስት ማስተዋል ተገቢ ነው። በተደገሰበት ሁሉ ተገኝቼ ልብላ ማለት አይገባም። የራሱን ቤት ምግብ እንዳያዘጋጅ ብለው “ና የእኛን ድግስ ብላ፣ ና የእኛን ጠበል ቅመስ” የሚሉትን ልብ ማለት ይገባል። አለበለዚያ ይሄንኑ በጣም ይለምድና “የት ነህ ያላሉት ቀላዋጭ እዚህ ነኝ ይላል” እንደሚባለው ይሆናል። ድርጅቶችም ሆኑ ግለ-ሰቦች በዚህ ዓመት ለሚካሄደው ምርጫ ስንቃቸውን መሰነቅ፣ መንገዳቸውን መጠራረግ፣ አካባቢያቸውን በነቃ ጆሮ ማዳመጥ ይጠበቅባቸዋል። ከላይ እንደተጠቀሰው ፈረስ ጠንካራ አቋምና በአንድ ጉዳይ ላይ ብርቱ ትኩረት ሊያደርጉ እንደሚገባ መገንዘብ ይኖርባቸዋል። ስለ ጦርነት እስትራቴጂ የላቀ ዕውቀት አላቸው የሚባሉ ባለሙያዎች እንዲህ ይላሉ፡- #ምርጡ ስትራቴጂ በወሳኙ ቦታ ጠንካራ ሆኖ መገኘት ነው! በራስ ኃይል ላይ አተኩሮ፣ ጥንካሬን አካብቶ መገኘትን የሚያክል ምንም ነገር የለም። ስለሆነም ስትንቀሳቀስ ሙሉ ኃይልህን አከማችተህና ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተህ
መጓዝ ይኖርብሃል።; ሾፕነር የተባለው ፈላስፋም፤ “አዕምሮአችን ለጥልቅ ትኩረት (Intensity)” እንጂ ለመስፋፋት (Extensity) የምንጠቀምበት አይደለም; የሚለንም ለዚሁ ነው። ብዙ የምንጓዝባቸው መንገዶች ቢኖሩም እንኳ አንዱን አውራ-መንገድ የመምረጥ ኃላፊነት አለብን። በአንድ ጊዜ በአንድ ቀስት ሁለት የተለያዩ ዒላማዎችን መምታት አይቻልም። መምረጥ፣ መጠንከር፣ ማለም የወቅቱ ጥሪ ነው። የሚያሳስቱ፣ የትኩረት ኃይልን የሚከፋፍሉ አያሌ ነገሮች አሉ። የአሸናፊነት ፍጹምነት የሚገኘው ብዛት ውስጥ ሳይሆን ጥራት ውስጥ ነው። በያዝነው መስመር ወይም መንገድ ጊዜያዊ ድል ስናገኝ አለመፈንደቅም አንዱ የዘላቂነት መርህ ነው። ጧት-ማታ በሚገኙ ትናንሽ ድሎች በመፈንጠዝ ከዋናው ዲሞክራሲያዊ ድል እንዳንናጠብ ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ያሻል። ያ ካልሆነ “ስትወቃ የዘፈነች፣ ስትፈጭ ምን ልትል ይሆን?” የሚያሰኝ ትዝብት ላይ ይጥለናል!!


  ስትወቃ የዘፈነች ስትፈጭ ምን ልትል ይሆን?

Read 9842 times