Sunday, 28 February 2021 00:00

ኑሮን እየተፈታተነ ያለው የዋጋ ንረት

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)


           ብልፅግና ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የኑሮ ውድነቱን አጀንዳቸው አላደረጉትም።
                      
           በሀገራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ የመጣው የዋጋ ንረት የህበረተሰቡን ኑሮን ክፉኛ እየተፈታተነው መሆኑን የኢኮኖሚ ባሙያዎች ገለጹ። የግብርና ሚኒስቴር የስራ ሃላፊ በበኩላቸው፤ በምግብ ሸቀጦች ላይ የሚታየው የዋጋ ጭማሪ፣ በምርት ማነስ የተፈጠረ ሳይሆን፤ የገበያው የሰንሰለት ስርዓት አለመኖር ያመጣው ህገ-ወጥነት ነው ይላሉ። የዋጋ ንረቱ፤ በተለይ በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ዜጎች ላይ ትልቅ ተግዳሮት ሆኖባቸዋል ተብሏል።
የዋጋ ንረቱ በኑሮአቸውን እየተፈታተነባቸው ከሚገኙ ነዋሪዎች መካከል አቶ ወንድማገኝ ስንታየሁ አንዱ ናቸው። በአዲስ አበባ ኮልፌ 18 ማዞሪያ አካባቢ ነዋሪ የሆኑት አቶ ወንድማገኝ፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ የሄደው የዋጋ ንረት፣ ትምህርት ሚኒስቴር ተቀጥረው በሚያገኙት ደሞዝ እራሳቸውን ጨምሮ 8 የቤተሰባቸውን አባላት ለማስተዳደር ፈተና እንደሆነባቸው ይገልጻሉ። ከምግብ ዋጋ በተጨማሪም የትራንስፖርት፣ የመብራት፣ የውሃ፣ የልጆች ት/ቤት ክፍያና የመሳሰሉት ዋጋዎች ንረትም ችግራቸውን እንዳባበሰ ይገልጻሉ። በገበያ የሚታየው የዋጋ ንረት በየቀኑ እየጨመረ መሄዱን የሚናገሩት አቶ ወንድማገኝ፤ አሁንማ እንደውም ጭማሪው ከቀናት አልፎ ጠዋትና ከሰዓት በኋላም የዋጋ ልዩነት ማሳየት ጀምሯል ይላሉ። “አገራዊ ምርጫ በሚከናወንበት በዘንድሮ ዓመት የኑሮ ውድነቱ በአጀንዳነት አለመነሳቱ አስገርሞኛል” የሚሉት አንድ አስተያየት ሰጪ፤ ይህም የፖለቲካ ፓርቲዎች ህዝቡን ጨርሶ የዘነጉት መሆኑን የሚያመለክት ነው ብለዋል። የኑሮ ውድነቱ ዘላቂ መፍትሄ ሳያገኝ በዚሁ ከቀጠለ፣ አገሪቷን ውስብስብ ወደሆነ ችግር ውስጥ ሊያስገባት እንደሚችል የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
     የብር የመግዛት አቅም በየጊዜው እየቀነሰ ሲሆን ከ2010 እስከ 2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ ብር የመግዛት አቅሙ በ54 በመቶ መውረዱን የሚገልጹት የኢኮኖሚ ባለሙያው ዶ/ር ሠለሞን ተስፋዬ፤ የዋጋ ንረቱ ከመርገብ ይልቅ እያሻቀበ፣ የዋጋ ግሽበቱ ባለ ሁለት አሀዝ ላይ ደርሷል ብለዋል። በየጊዜው እያሻቀበ የመጣውን የዋጋ ንረት አስመልክቶ በመንስኤው ላይ ሰፊ ጥናት ማድረጉን የገለፀው ኢዜማ በበኩሉ፤ ችግሩን ሊቀርፍ የሚችል የመፍትሄ ሃሳብ የያዘ በምሁራን የተዘጋጀ ፖሊሲ ማዘጋጀቱን፣ የፓርቲው የብሄራዊ ፖሊሲ ዝግጅት አስተባባሪ አቶ አማን ይሁን ረዳ ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሕዝብን መሰረታዊ ፍላጎት የሚያሟሉ የፍጆታ እቃዎች እንደ ልብ አያመርቱም ያሉት አስተባባሪው ባለፈው ዓመት ብቻ 700 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ስንዴና 500 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ የምግብ ዘይት ከውጪ አገር ማስገባታችንን እንዲሁም ነጭ ሽንኩርትና ምስር ሳይቀር ከውጪ አገር ማስመጣታችን
መሆኑ ይህንኑ አመላካች ነው ብለዋል። ኢዜማ፤ የስራ አጥነት ችግርን በማስወገድ ለወጣቱ ስራ፣ ለህዝቡ በቂ ቀለብ ማግኘት በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል። የዋጋ ንረቱ፤ የህዝቡ ገቢ ከኑሮ ውድነቱ ጋር ያልተመጣጠነ መሆኑ፣ ዘመናዊ የገበያ ሰርዓቶች
ባለመኖሩ ሳቢያ በሚፈጠር አርተፊሻል እጥረት ሳቢያ የሚከሰት ነው የሚሉት አቶ አማን ፤ ይህንን የሚቀይር ኢትዮጵያ በዘመኗ ኖሯት የማያውቅ
የመጀመሪያው የንግድ ፖሊሲ አዘጋጅተናል ብለዋል። መንግስት የአለም አቀፉን የገንዘብ ድርጅት ያልተገባ ምክር በመስማትና በተግባር የዶላር ምንዛሬ ዋጋ እንዲጨምር በማድረግና የብርን መግዛት አቅም በማዳከም ህዝብን ለዚህ ችግር አጋልጧል ያሉት አቶ አማን፤ ይሁን፤ ከለውጡ በኋላ የገንዘብ የመግዛት አቅም በ35% ተዳክሟል ብለዋል። የዶላር ምንዛሬ ዋጋ ጭማሪው በሁሉም የፍጆታ ዕቃዎች ላይ ጭማሪ እንዲፈጠር አድርጓልም ሲሉ ተናግረዋል። ይህ
ሁኔታም ጊዜ ሳይሰጠው ሊስተካከል እንደሚገባ ገልፀዋል። በዳቦ ላይ የሚደረጉ የጥቂት ሳንቲም ጭማሪዎች አብዮት አቀጣጥለው ያደረሱትን ጉዳይ የምናውቀው ነው። ካርቱም የተቀጣጠለው ተቃውሞና አልበሽር ከስልጣን የወረዱበት ጉዳይም ይኸው የዳቦ ዋጋ ጭማሪ ነው። ስለዚህም በቸልተኝነት ሊታይ የሚገባው ጉዳይ አይደለም። መንግስት የባለሙያ እጥረት ሳይኖርበት በውጪ አገራት ምክር ላይ ጥገኛ ሆኖ ህዝቡን ለዚህ ችግር ማጋለጥ የለበትም ብለዋል። በማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ መሰረት፤ የምግብ ዋጋ ግሽበት 23.7 በመቶ የደረሰ ሲሆን ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 24 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። ይህ ቁጥር በ7 ዓመታት ጊዜ ውስጥ የታየ ትልቁ አሃዝ ነው ተብሏል። ለቁጥሩ ከፍ ማለት የምግብ ዋጋ በተለይም የእህል ሰብል ዋጋ ንረት ምክንያት መሆኑን የስታቲስቲክስ መረጃዎች ያመለክታሉ። ወደ 80 በመቶ የሚጠጋው ኢትዮጵያዊ መደበኛ ባልሆነ ስራ ውስጥ ተሰማርቶ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ገቢ በማግኘት ኑሮውን እንደ የሚገፋ የሚናገሩት ዶ/ር ሰለሞን ፤የዋጋ ንረቱ የበርካታ ኢትዮጵያውያን ኑሮን ፈታኝ እንዳደረገው ይገልጻሉ። ለፖለቲካዊ ጉዳዮች እየተሰጠ ካለው ትኩረት ጋር የሚመጣጠን አትኩሮት ለዋጋ ንረትና የስራ አጥነትን ለመሳሰሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻችን ሊሰጥ ይገባልም ብለዋል ባለሙያው። በአገሪቱ በየጊዜው የሚከሰቱት የእርስ በርስ ግጭቶችና የሰላም መደፍረስ በምርት ሰንሰለት፣ በግብዐት አቅርቦትና በምርት ስርጭቶች ላይ ከፍተኛ ችግር እየፈጠሩ ነው ያሉት አንድ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የግብርና ሚኒስቴር
የስራ ሃላፊ፤ በአሁኑ ወቅት እየታየ ላለው የዋጋ ንረትና በምግብ ሸቀጦች ላይ ለሚታየው የዋጋ ጭማሪ መነሻ ምክንያቱ በምርት ማነስ የተፈጠረ ሳይሆን የገበያው ሰንሰለት ስርዓት አለመያዝ ያመጣው ህገ-ወጥ አሰራር ነው ብለዋል። ለዋጋ ግሽበቱ መፍትሄ ለመስጠት ችግሩ ከምን መነጨ የሚለውን መለየት አስፈላጊ ነው ብለዋል። የችግሩ መንስኤ ምጣኔ-ሃብታዊ ሳይሆን ማህበራዊ አለያም ፖለቲካዊ ሊሆን ይችላል ሲሉም ጠቁመዋል። ይህንን ሀሳብ የሚቃወሙት የባልደራሰ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የቢሮ ሃላፊ አቶ ገለታው በለጠ ፤ የዋጋ ንረቱ መነሻ ምክንያቱ የምርት እጥረቱ ነው ይላሉ። “ለዚህ የዳረገን ደግሞ የመሬት ፖሊሲያችን ነው፤ አርሶ አደሩን መሬትን መሸጥ መለወጥ አትችልም ብለን አስረን አስቀምጠን እርዳታ ጠባቂ ካደረግነው በኋላ፣ ስለተሻለ ምርት ማውራቱ የሚዋጥ ጉዳይ አይደለም። ይህንን ችግር ለማስወገድ አርሶ አደሩ የመሬቱ ባለቤት ሊሆን ይገባል፤ በመሬቱ ላይ ማዘዝ አለበት። እርሻውን ማስፋፋት፣ ምርቱን ማሻሻል ይኖርበታል። ስለዚህም የመሬት ፖሊሲያችን ሊለወጥ ይገባል የሚል እምነት አለን” ብለዋል። “ያፈራነው ቁጭ ብሎ ውሎ ማታ የቤተሰቦቹን እንጀራ የሚበላ ትውልድ ነው” ያሉት አቶ ገለታው፤ ፓርቲያቸው የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት ህብረተሰቡን ያሳተፈ መፍትሄ ለመዘየድ እንደሚሰራም ተናግረዋል። የሸማቹን የእለት ተእለት ኑሮ ያከበደውንና ፈተና ላይ የጣለውን ገበያ ለማረጋጋት መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባም ተገልጿል። ምግብ ነክም ሆነ ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦችን ወደ ገበያ በብዛት እንዲገቡ ማድረግና አምራቹና ተጠቃሚው የሚገናኙባቸው መንገዶች ላይ በስፋት መስራት ችግሩን ለመፍታት አይነተኛ መፍትሄ እንደሚሆንም ተጠቁሟል።



Read 8535 times