Print this page
Monday, 01 March 2021 19:41

የአድዋ ድል አከባበር፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት

Written by  ሔዋን ስምዖን
Rate this item
(5 votes)

 ባለፉት ሁለት ዓመታት የተከበሩት 123ኛው እና 124ኛው የአድዋ ድል በዓሎች ለየት ያሉ ናቸው፡፡ ከቀድሞዎቹ በተለየ መልኩ የከተማዋ መንገዶች በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራ አሸብርቀው፣ የየሰፈሩ ልጆች የየራሳቸውን ቲ-ሸርቶችና ልብሶች አሠርተውና ለብሰው ነው ያከበሩት። የየካ ክ/ ከተማው አድዋ ድልድይም የአጼ ምኒልክ፣ የጣይቱ፣ ራስ አሉላ፣ ራስ መኮንን፣ ደጃዝማች ባልቻ ወዘተ ፎቶዎችንና ምስሎችን በግዙፍ ወረቀት በማተም አሸብርቆ ታይቷል፡፡
ለ123ኛው በዓል ዋዜማ፣ በጣይቱ ሆቴል በአድዋ ላይ የሚያጠነጥን ቲያትር ታይቷል፤ ይህ ቲያትር በ124ኛው በዓል በብሔራዊ ቲያትር ቀርቧል። የመድረክ ሥራው ወደ አድዋ ጦርነት ያመሩትን ሁኔታዎች የሚያሳይ ነበር። በሁለቱም ዓመታት፣ የካቲት 23 ማለዳ ላይ የመዲናዋ ነዋሪዎች፣ ከየአቅጣጫው ወደ ምኒልክ አደባባይ በማቅናት በዓሉን ሲያከብሩ ታይተዋል፡፡ ይሄ ሁሉ ደሞ በመንግሥት ከሚዘጋጀው የበዓል አከባበር በተጨማሪ ነው፡፡ የመንግሥቱ የበዓል አከባበር፤ የከተማዋ ምክትል ከንቲባ በሚያቀርቡት ንግግር፣ የኢትዮጵያ አርበኞች በሚያደርጉት ሰልፍና ጉዞ ታጅቦ፣ ከአዲስ አበባ መዘጋጃ ጋር
በመተባበር ከሚቀርቡ የመድረክ ሥራዎች ጋር (አንዳንዴ) የሚከናወን ነው፡፡ የሕዝቡን አከባበር ከዚህ ለየት የሚያደርገው ዝግጅቱን የሚያስተባብረው
አንድ ማዕከላዊ ቡድን አለመኖሩ ነው። ሕዝብ በየሰፈሩና ከየጓደኞቹ ጋር በመሆን ይዘጋጃል፣ ወደ ምኒልክ አደባባይም ይጓዛል። ከ123ኛው የአድዋ በዓል ጀምሮ ደግሞ ሕዝብ የሚይዘው ባንዲራ ተቀየረ - ኮከብ አልባው የኢትዮጵያ ባንዲራ ነበር በምኒልክ አደባባይ ዙሪያ የሚታየው። ይኽም አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ የተፈጠረ አዲስ ክስተት ነው። ወደ ፒያሳ ከሚመጡት ቡድኖች መካከል ገሚሱ ቡድን ቡድን ሰርቶ የየራሱ ምኒልክ፣
ጣይቱ፣ የእግረኛ ጦር፣ ሴት ወታደሮች፣ ሙዚቀኞችን አሰልፎ ነው የሚመጣው፡፡ እነዚህ የበዓሉ ታዳሚዎች ሽለላ፣ ፉከራና ቀረርቶ በማሰማት በዓሉን ያደምቁታል፡፡ ወታደሮቹ የካርቶን መሣሪያዎችንም ይይዙ ነበር። ከነዚህ መካከል ባዶ እግራቸውን የነበሩ አያሌ ናቸው። እንዲህ የጦርነት ፉከራና ሽለላ ከሚያቀርቡት ውጪ ደግሞ ባህላዊ ልብሶችንና የተለያዩ ተመሳሳይ ቲ-ሸርቶችን የለበሱ፣ የሚዘፍኑና የሚደንሱ ሰዎች ያሉባቸው ቡድኖችም ብዙ ነበሩ።
ከዚህም በተጨማሪ የከተማዋ ሁለት ታላላቅ ተፎካካሪዎች፣ የኢትዮጵያ ቡናና ቅዱስ ጊዮርጊስ የእግር ኳስ ቡድን ደጋፊዎችም፣ በየራሳቸው ቀለማትና
ባንዲራዎች አሸብርቀው በዓሉን ሲያከብሩ ተስተውለዋል፡፡ ቀኑ ብዙም ሳይገፋ በርካታ ሰው ያለው የጦር ሰልፍ ከፒያሳ ተነስቶ በአራት ኪሎ፣ አቧሬ አካባቢ ዞሮ ወደ መሃል ፒያሳ ይመለሳል። ይህ ቡድን ነጋሪት የተሸከሙ ባዶ እግራቸውን የሆኑ ወታደሮች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ ሴት አርበኞች፣ አህዮች፣ ፈረሶች፣
የጓዳ ዕቃ ተሸካሚዎች ወዘተ ያካተተ ነው። ከሰዓት ደግሞ የእንጦጦ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ግብር ስለሚያዘጋጅ የሚችል ወደዛ ያቀናል። ቤተ መንግሥቱ ብዙም ዕድሳት ስላልተደረገለት በጊዜ ወደ ኋላ ዘመን ይመልሳል፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ፤ በ2011 እና 2012 ዓ.ም. የታየውን፣ መንግሥት ያልቀሰቀሰውንና
ሕዝብ በፍላጎቱ የተሳተፈበትን የአድዋ ድል አከባበር መቃኘት ነው፡፡ ፍላጎቴ በብሔር ፌዴራሊዝም ሥር ተወልዶ ያደገ ትውልድ፣ አድዋን እንዴት እንደሚያስታውስና እንደሚዘክር ማሳየት ሲሆን ይህም በግል የታዘብኳቸውን፣ የመዘገብኳቸውንና የቀዳኋቸውን ጽሑፎችና ግጥሞችን ያካተተ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን እንደመጣ ሰሞን ስለ አድዋ የተጻፉ ጽሑፎችንም ይዳስሳል፡፡ የጥናቱ ግምት፤ ኢትዮጵያውያን በ1888 ዓ.ም. አንድ
ሆነው ጠላትን ማሸነፍ እንደቻሉት ሁሉ፣ አሁንም ወጣት ኢትዮጵያውያን የብሔር ማንነቶችን ሳይደመስሱ፣ ከዛ ያለፈ ማንነት ፍለጋ ላይ እንደሆኑ ማየት ይቻላል የሚል ነው። ከዚህም ባላነሰ በዚህ ጥናት ውስጥ የተካተቱት ስነ ቃሎች (ግጥሞች፣ አባባሎች ወዘተ) የኢትዮጵያ የቃል ሥልጣኔ እንዴት ከዘመን ዘመን ሲወራረስ እንደዘለቀ ማሳያም ናቸው ባይ ነው። መመዝገባቸውም ለታሪክ ይጠቅማል። እኚህ ወጣቶች ለበዓሉ ድምቀት ይዘዋቸው ከሚሄዱት ቁሳቁሶች በተጨማሪ፣ ዝማሬያቸው፣ ግጥሞቻቸው፣ ሙዚቃዎቻቸው ሁሉ ኢትዮጵያውያን እራሳቸውን እንዴት እንደሚገልጹ ማሳያዎች ናቸው። አንዳንዶቹ ተስፋ ሲያንጸባርቁ፣ ሌሎቹ የፖለቲካ ትንታኔም አላቸው። አዲስ አበባ ከኢህአዴግ ጋር የነበራትን ግንኙነትም በነዚህ ሁለት ዓመታት የአድዋ አከባበሮች
ለማየት እንሞክራለን። መንደርደሪያ የአድዋ መቶኛ ዓመት በሚከበርበት ወቅት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት እና ምርምር ማዕከል Adwa: Victory Centenary Conference የሚል የጽሑፎች ስብስብ አሳትሟል። ከእነዚህም መካከል አሰፋ አብርሃ የጻፉት ለእኛ ርዕስ ጠቃሚ ስለሆነ በአጭሩ እንዳስሰዋለን፡፡ የአቶ አሰፋ ጽሑፍ፤ የአድዋ 100ኛ ዓመት በዓል ምን ይመስል እንደነበርና ኢትዮጵያውያን እንዴት እንዳከበሩት የሚያሳይ ነው፡፡ አሁን 125ኛውን ዓመት እያከበርን በመሆኑ ለንጽጽር ያመቻል። የመቶኛውን ዓመት በዓል ልዩ የሚያደርገው፤ ይላሉ አቶ አሰፋ፡- «እየተከበረ ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ መንግሥት አቋቁመው ባሉበት ሰዓት ላይ እና የታሪካቸውን አዲስ ምዕራፍ የከፈቱበት መሆኑ ነው። በዚህም ምዕራፍ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት አግኝተውና የአድዋ ድል ያጠናከረውን መንግሥት ተክተው ይገኛሉ።» (አሰፋ አብፍሃ 1998 እ.ኤ.አ.፣ ገጽ 129). አቶ አሰፋ 25 ዓመታት አንድን ትውልድ እንደሚወክልና 100ኛውን የአድዋ በዓል፣ ከአድዋ ጦርነት ጀምሮ 4ኛው ትውልድ እያከበረ እንደነበር ጽፈዋል፡፡ በዚህ ስሌት አሁን አድዋን የሚያከብረው ትውልድ የአድዋ 5ኛ ትውልድ ነው ማለት ነው። ይሄ አምስተኛ ትውልድ ደግሞ ያለፉት ሁለት ዓመታትንም የአድዋ ድሎች
አክብሯል። ከዚህ ቀጥሎ እንደምናየው አቶ አሰፋ በተስፋ የተናገሩትን የአዲስ አበባ የአድዋ ድል አክባሪዎች ሲቃረኑ እንመለከታለን፣ ራስን በራስ ማስተዳደር፣ የብሔር ፌዴራሊዝም፣ የኢትዮጵያ ባ ንዲራና የ እነ አ ጼ ም ኒልክ ስ ም መጠልሸት ሁሉ በአክባሪዎች ዘንድ እንዴት እንደሚታዩ እንቃኛለን።
   ወደ ምኒልክ አደባባይ፡
በምኒልክ አደባባይ የአንበሳ ጎፈሬ ያደረጉ፣ ጋሻና ጦር የያዙ፣ የጥጥ ልብስና የሀር ካባ የደረቡ ዘራፍ እያሉ የሚሸልሉና ግጥም የሚገጥሙ ቡድኖች ይታያሉ፡፡ የዘራፍ ግጥሞች ጥንት ከጦርነት በፊትና በኋላ እንዲሁም በግብር ጊዜ የሚሰሙ ነበሩ። አሁን በአዲስ አበባ እምብዛም የተለመዱ አይደሉም፤ ከባህላዊ ምግብ ቤቶችና መዝናኛዎች ውጪ። እምቢልታ፣ መለከትና ነጋሪትም ይዘው የሚጎሽሙ ነበሩ። ነጋሪት አዳዲስ አዋጆችና ሕጎች በየገበያውና አደባባዩ የሚነገሩበት፣ እንዲሁም ጦርነት ሲታወጅ የሚታወቅበት መሣሪያ ነበር። እስከ ኃይለ ሥላሴ ኢትዮጵያ ድረስም ዘልቋል። ወይዘሮ ፀሐይ ብርሃነሥላሴ እንዲህ ትላለች፡-
«የነጋሪት ከበሮዎች ‘ተናጋሪ’ ከሚለው የመጡ ሲሆን የባለሥልጣናት ከበሮዎች ነበሩ። [ወደ ጦርነት እየተጓዙም ሳለ ቢሆን ለግጭት እየተዘጋጁ ከበሮዎቹ] ትእዛዝ ተሰጥቶ ምታቸውን እስኪቀይሩ ድረስ ያለማቋረጥ ይመታሉ። ከበሮውን የሚመቱት ወይ ከቡድኑ ጥግ ጋር ሆነው ነው ወይንም ከበሮውን
ከተሸከመው እንስሳ ጎንና ጎን በመሆን ነው፤ ሰው የከበሮውን የተለያዩ ምትና ስልት ያውቃል። በጦር ሜዳ ላይም የጦር መሪዎች የት ጋ እንዲሄዱ እንደተፈለጉ ይጠቁማሉ፣ የዘመቻውን አቅጣጫም ይቆጣጠራሉ። ሰዎች ታዲያ በፍጥነት መሄድ እንዳለባቸው ወይም ቀስ ማለት እንዳለባቸው እንዲሁም እንዲገሰግሱ
ወይንም እንዲወጡ፣ እንዲወሩ ወይንም ሌ ሎች ነገሮችን እንዲያደርጉ ይጠቀሙበታል።» (ፀሐይ 2018 እ.ኤ.አ.፣ ገጽ 199) በአድዋ ድል አከባበር ጊዜ ታዲያ ነጋሪቶቹና ነጋሪት መቺዎቹ አብረው አሉ። ቢሆንም አሁን ነጋሪት ለአዲስ አበባ ሕዝብ ጥቅም የለውም። እኚህን ከበሮዎች በመሸከም የአድዋን ድል
የሚያከብሩት የአድዋን ክተት አዋጅና ዘመቻ ዳግም ለማስታወስ ነው። የጦርነቱን ብቻ ሳይሆን ነጋሪትን እንደ ዋና የማኅበረሰቡ አካል ይገለገሉበት የነበሩ የዚያን ጊዜ ኢትዮጵያውያንንም እያስታወሱ ነው።
    ግጥሞች፣ ዘፈኖች
  ከእነዚህ ባሕላዊ ቁሳቁሶች በተጨማሪም በምኒልክ አደባባይ የሚደመጡት ግጥሞችም ይማርካሉ። የዘራፍ እና ፉከራ ግጥሞቹ በተለይ ከአድዋ ድል በፊት ኢትዮጵያውያን ያሏቸው መሆናቸው ይበልጥ ገራሚ ነው። የ19ኛው ክ/ ዘመን የፉከራ ግጥሞች በብዛት በጀግንነት የተወጡትን ተጋድሎ ማስታወሻና ወደፊት
ሊያደርጉት ስለሚፈልጉት ነገር መናገሪያ ሆነው አገልግለዋል። እነዚህ ተጋድሎዎች በጦር ሜዳ ብቻ መሆን የለባቸውም፤ አዳኞችም ሊፎክሩ ይችላሉ። በዘልማድና በምኒልክ አደባባይ ዙሪያ በተደጋጋሚ የሚስተጋባና የ19ኛው ክ/ ዘመን ለአዳኞች የተባለ የፉከራ ግጥም የሆነው የሚቀጥለው አንድ ምሳሌ ነው፡
ዱብ ዱብ ይላል እንደበረዶ፤
ልጅነቱ በረሃ ለምዶ።
ይህ ቃል በቃል በምኒልክ አደባባይ በአድዋ
በዓል ጊዜ ይሰማ ነበር። ሌሎችም አሉ፤ በአሁኑ
ጊዜ የሚደመጡ ፉከራዎች፡
እነዚህ እነዛ
እነማን ናቸው
የምኒልክ ልጅ
አርበኞች ናቸው
ዘራፍ አካኪ ዘራፍ
አሁንም ዘራፍ ቅድምም ዘራፍ
ማን ይዳፈራል የጀግናን በራፍ
ጠብመንጃ አንግቶ ከነጥይቱ
ወዮልህ ጥላት አለች እናቱ
እንኳን እናቱ የወለደችው
ፈራች አማቹ የተጋባችው
ለመድገም ያህል እኚህ ግጥሞች የ19ኛውን
እና 20ኛውን ክ/ዘመን መልክ ሳይቀይሩ እኛ
ዘመን ላይ መድረሳቸው ነው የሚገርመው።
ከታሪክ ከተወሰዱት በተለየ ደግሞ ሌሎች
የሚያስገርሙ ግጥሞችም አሉ፤ ለምሳሌ፡
ተነሳ ተራመድ
ክንድህን አበርታ
ለሀገር ብልጽግና
ለወገን መከታ
ሀሁ ኢትዮጵያ ትቅደም
ሀሁ ኢትዮጵያ ትቅደም
ይሄ ግጥም በ1967 ዓ.ም. በአየር ኃይል ሙዚቃ ቡድን በደርግ ዘመነ መንግሥት ከተቀነቀነ ዜማ የተወሰደ ነው። በደርግ ዘመን ያልተወለዱ፣ ቢወለዱም ዕድሜያቸው ትንሽ የነበሩ ወጣቶች አሁን ላይ ይሄንን ግጥም ዳግም ማዜማቸው ያስደምማል። ደግሞ ይሄም ብቻ አይደለም፤ ሌሎችም አሉ። ከደርግ ዘመን የፕሮፓጋንዳ ሙዚቃዎች ሌላ ደግሞ በኢህአዴግ ዘመን የተዘፈኑ ሙዚቃዎችም ለአድዋ ክብረ በዓል ግጥሞችን ሲለግሱ ይታያሉ። ትልቁ ምሣሌ የቴዲ አፍሮ
  #ጥቁር ሰው; ነው።
ወይ ሳልለው ብቀር ያኔ
እኔን አልሆንም ነበር እኔ
ምኒልክ
ጥቁር ሰው
ይሄ በምኒልክ አደባባይ ዙሪያ ብዙ ጊዜ ተደጋግሞ ይዜማል፡፡ ለአጼ ምኒልክ ክብርና ታዛዥነትን መግለጻቸው ነው።
ከሙዚቃዎቻችን ውጪ ሕዝብ በራሱ የሚገጥማቸውም አሉ። ለምሣሌ፡-
የአዲስ አበባ ልጅ የሸገር
የለውም ዘር
እንዲህ በራሳቸው የሚገጥሟቸው ግጥሞች የነዋሪውን ሃሳብ ያንጸባርቃሉ። በዚህ አጭር ግጥም አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ብሔር የሚለው ወይንም ዘር የሚለው እንደማይወክላቸው እየተናገሩ ነው። ተያይዞም ብሔርን እንደ መንግሥት መዋቅር አድርጎ የሚሠራውን መንግሥት እየተቃወሙ እንደሆኑም መገመት ይቻላል። ዞሮ ዞሮ ዋናው ነገር ግን በአድዋ በዓል ጊዜ ሰው የልቡን መናገሩን ለመጠቆም ነው። ሌሎች ምሣሌዎችም አሉን፡
ጣልያን ብትመጣ አለ መመለሻ
እንግሊዝ ብትመጣ አለ መመለሻ
እኛን የቸገረን አበሻ ለአበሻ
እንዲህ ስለ ሀገራቸው ሁኔታ ከሚያንጸባርቁ ግጥሞች አለፍ ብሎም ስለ ጎረቤት ሀገራትም ይገጠማል። በ124ኛው በዓል ላይ እንዲህ ሲባል ነበር፡-
ይለያል ይለያል ይለያል ዘንድሮ የግብጽ ኑሮ ከነዚህ ግጥሞች ስንወጣ የምኒልክ አደባባይን ከሚጎበኙ ታዳሚዎች መካከል የእግር ኳስ ደጋፊዎች መኖራቸው ሌላው በዓሉን የሚያደምቀው ነገር ነው። የኢትዮጵያ ቡና እና የጊዮርጊስ ደጋፊዎች በብዛት የየራሳቸውን ባንዲራዎችና መለያዎች ይዘው ሲዘምሩ ሲፎክሩና ሲሸልሉ ታይተዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ቡድን ጣልያን ለሁለተኛ ጊዜ ስትወረን ቡድኑ ተመሥርቶ ጣልያኖችን 4 ለ 1 በማሸነፉ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክም ሆነ በሀገሪቷ ፋሺስትን የመቃወም ታሪክ ውስጥ ትልቅ ሥፍራ ያለው ቡድን ነው። (ጳውሎስ ሚልኪያስ 2011 እ.ኤ.አ.፣ ገጽ 375)
የቡድኑም መጠሪያ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ የኢትዮጵያ ጠባቂ ሰማዕት እንደሆነ ስለሚታመንና በአድዋ ላይም ወርዶ ኢትዮጵያን አግዟል የሚል የሕዝብ እምነት ስላለ፣ ከኢትዮጵያ ክብር ጋር የተቆራኘ ቡድን ነው። ቡና በአዲስ አበባ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቀንደኛ ተቀናቃኝ ቡድን ቢሆንም፣ እንደ እግር ኳስ ቡድን አድዋን ለማክበር የተለየ ምክንያት የለውም። ነገር ግን ደጋፊዎቹ ልክ እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ከልብ ሲያከብሩና ሲዘምሩ ይውላሉ፤ የቡናን ባንዲራና ቀለማት ለብሰው። ቅዱስ ጊዮርጊሶች እንዲህ እያሉ ይዘፍናሉ፡-
የሀገር ፍቅር ስሜት መለኪያ
ተስፋ በሌለበት ተስፋቸው
ቅዱስ ጊዮርጊስ ነበር ወኔያቸው
አያሆሆ አያሆሆ የአርበኛው ነኝ እኔ
ፋኖ በጦር ጋሻ
ሳንጃው በእግር ኳሱ
ወኔ እየለበሱ
ከሕዝብ ልብ ላይመቼም ሳይረሱ
ለቡድናቸውና ለአድዋ፣ ለአድዋ ጀግኖችና ለቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲሁም ለእግር ኳስ ተጫዋቾቻቸው ተመሳሳይ ሙገሳ ያቀርባሉ። የቡድናቸውን ታሪክ ከአድዋና ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር ያያይዙታል። እራሳቸውንም የአርበኛ ልጆች ይላሉ።
ቡናዎች እንዲህ ይላሉ፡-
ሳዜም ነው ያደግኩት በጨቅላ አንደበቴ
የልቤ ማኅተም መቼም አይወጣም አድዋ ሕይወቴ
የቡድናቸውን መዝሙር ነው ለአድዋ የሚያደርጉት። ፍቅራቸውን መግለጫ እንጂ የተለየ ነገር የለውም።
      በመጨረሻም
የአዲስ አበባንና የኢህአዴግን ግንኙነት በደንብ የሚገልጸው ግን የኢትዮጵያ ባንዲራ ጉዳይ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በተከበሩት ሁለት አድዋዎች ላይ የታዩት የኢትዮጵያ ባንዲራዎች ሁለት አይነቶች ናቸው። ሕዝብ ኮከብ አልባውን ይዞ ሲወጣ፣ መንግሥት ባለ ኮከቡን ይዞ
ይገኛል። ኮከብ አልባው ባንዲራ በኢህአዴግ ዘመን ሕገ ወጥ መሆኑ ሕዝብ ለባንዲራው ያለውን ፍቅር የጨመረበት ይመስላል፤ አንድ ነገር ሲከለከል
ይበልጥ እንደሚማርከው ሁሉ። ግን ይህ ብቻ ሳይሆን የኢህአዴግን ባንዲራ አልይዝም በማለት ሕዝብ ኢህአዴግንና ሕግጋቱን፣ ሥርዓቱን አልፈልግም እያለ እንደሆነ መገመትም ይቻላል። ኮከቡ የብሔር ፌዴራሊዝም ምልክት ስለሆነ፣ ቅድምም እንዳየነው ወጣቱ ብሔር የለኝም እያለም ስለሆነ፣ ብሔር አልባ የፖለቲካ መዋቅርን ይዟል ብሎ የሚያምነውን ባንዲራ ለብሶ ይወጣል፤ አድዋን ለማክበር። መጀመሪያ ላይ የቀረበው ባለ ብዙ ተስፋው የአቶ አሰፋም ጽሑፍ ትልቁን መቀናቀኛ የሚያገኘው እዚህ ላይ ነው። አምስተኛው ትውልድ የኢህአዴግን ባንዲራ አልፈልግም ብሎ ትቷል። ታሪክና ምልክቶች የጊዜውን
ትኩሳት መወጣጫ እንደሆኑ ማሳያ አንድ መንገድ ነው ይሄ።
       መሰናበቻ
የአድዋ ድል አከባበር ብዙ ነገሮችን ያሳየናል። አንድ/ አከባበሩ ላይ ሰው ከብሔር አስተሳሰቦች መውጣት እንደሚፈልግ ይናገራል። ሁለት/ ምልክቶቹ እንደ ፖለቲካ መቃወሚያ ያገለግላሉ። ሦስት/ በክብረ በዓሉ ላይ የሚደጋገሙት ግጥሞችና ስንኞች፣ ሰዉ ታሪኩን፣ አኗኗሩን፣ ሐሳቡንና አስተያየቱን የሚገልጽባቸው ስለሆኑ እኚህን መሰብሰብ አስፈላጊ ነው። የአድዋ ድል አከባበር የኢትዮጵያን ስነ ቃል ከትውልድ ወደ ትውልድ መሻገርንም ያሳየናል።
በ19ኛው እና 20ኛው ክ/ዘመን የተገጠሙ ግጥሞች፣ ዛሬ ጊዜውና የአኗኗር ስልታችን በተለወጠበት ዘመን በድጋሚ ሲስተጋቡ ይደመጣል፡፡ የከተማዋን ወጣት የእግር ኳስ ቡድን ፉክክርም እ ንመለከታለን። ከ ዚህም አ ልፎ የደርግ ዘመን መዝሙሮች የአሁን ዘመን ወጣት ሲጠቀምባቸው እናያለን። የሙዚቃን
ታሪክ ለሚያጠኑ ግለሰቦች እስከአሁን ደርግ የኢትዮጵያን የሙዚቃ ባህል አጥፍቷል ተብሎ የሚታሰበውን ዳግም እንዲያጠኑትና እንዲመረምሩት የሚጋብዝ ነው። በመጨረሻም ባለ ኮከቡን የኢትዮጵያ ባንዲራ አልይዝም ባይነታቸው፣ ምኒልክ አደባባይ ሄደው የአድዋን ድል የሚያከብሩትን የአዲስ አበባ ሕዝብ (ከአድዋ ዘመን አምስተኛው ትውልድ) ከኢህአዴግ ጋር ያለውን ግንኙነት ማንጸባረቂያም ሆኖ ያገለግላል። የ123ኛው እና 124ኛው የአድዋ ድል አከባበር
በአጠቃላይ አድዋ ጣልያን ድል የተደረገበት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያውያን የመንፈስና የሀገር አንድነት ዋጋን ይበልጥ የሚያንጸባርቁባቸው በዓሎች ነበሩ ለማለት እንደፍራለን።

Read 1638 times