Saturday, 06 March 2021 13:05

ሂዩማን ራይትስዎች በትግራይ የጦር ወንጀል ተፈጽሟል የሚል ጥርጣሬ አለኝ ብሏል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

     በትግራይ ክልል በተካሄደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ  ወቅት ሰላማዊ ሰዎችን ከመግደል ጀምሮ የጦር ወንጀል ሳይፈጸም እንዳልቀረ ትናንት አርብ ባወጣው ሪፖርቱ ያመለከተው ሂውማን ራይትስዎች፤ ጉዳዩ በአፋጣ በገለልተኛ አካል እንዲያጣራ ጠይቋል።
የሰብአዊ መብት ተቋሙ ትናንት ባወጣው ሪፖርቱ፤ ህዳር 10 ቀን 2013 ዓ.ም የኤርትራ ወታደሮችና መከላከያ በአክሱም ከተማ ላይ በፈፀሙት የከባድ መሳሪያ ድብደባ ሰላማዊ ሰዎች ለሞትና ለጉዳት መዳረጋቸውን፣ ከተማዋ ከተያዘች በኋላም ለሳምንት ያህል ሰላማዊ ሰዎች በጥይት መመታታቸውንና ንብረት በገፍ መዘረፉንና መውደሙን አመልክቷል።
በአክሱም ከተማ የሚገኙ 28 ሰዎችን በስልክ በማናገርና ቪድዮዎችን በማጣራት ሪፖርቱን  ማጠናቀሩን የጠቆመው  ሂውማን ራይትስዎች በከተማም በሁለት ቀናት ጥቃት ከ2 መቶ በላይ ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀረ አስታውቋል።
በተመሳሳይ ቀደም ባለው ሳምንት በጉዳዩ ላይ ሰፋ ያለ ሪፖርት ያወጣው ሌላኛው የመብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል በአክሱም በኤርትራ ወታደሮች በተፈጸመ ጥቃት ከ2 መቶ በላይ ሰዎች መገደላቸውን ማስታወቁ ይታወሳል።
ሂውማን ራይትስዎች ይህን የምርመራ ሪፖርቱን ከሁለት ሳምንት በፊት ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ባለስልጣናት አቅርቦ አስተያየታቸውን እንዲያካትቱ ጠይቆ እንደነበር ነገር ግን ምላሽ እንዳልተሰጠው ገልጿል።
ባለፈው ሳምንት፤ በተመሳሳይ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያወጣውን ሪፖርት ተከትሎ መንግስት  የኤርትራ መንግስት የተለመደ የስም ማጥፋት ሀሰተኛ ሪፖርት ሲል ያጣጣለው ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ፤ ማጣራት  እንደሚያደርግ መግለፁ  አይዘነጋም። ከጠቅላይ አቃቢ ህግና ከፖሊስ የተውጣጣ አጣሪ  ግብረ ሃይል ፤ አደራጅቶ ማሰማራቱ ተገልጿል።


Read 905 times