በከተሞቹ ላይ በተካሄደው ጥናት መሠረት፤ ለኑሮ አመቺ ናቸው ተብለው ከተመረጡ አስር አገሮች ውስጥ ከአውስትራሊያ ሜልቦርን፣ አዴልአይሌ፣ ሲድኒ እና ፐርዝ ሲገኙበት፤ ከካናዳ ቫንኩቨር፣ ቶሮንቶ እና ካልጋሪ ተመርጠዋል፡፡ የአውሮፓ ከተሞቹ ቪየና እና ሔልሲንኪ እንዲሁም የኒውዚላንዷ ኦክላንድም በዚሁ ምድብ ተካተዋል - ለኑሮ አመቺ ከተማ በመሆን፡፡
የመካከለኛው ምስራቅ እና የሠሜን አፍሪካ አገራት (ከተሞች) ለኑሮ ከማይመቹት መካከል የተመደቡ ሲሆን ካቡል፣ ባግዳድ እና ሞቃዲሾ ግን በጥናቱ አልተካተቱም ተብሏል፡፡ የሶሪያ ዋና ከተማ ደማስቆስ ደግሞ የአንድ መቶ ሰላሳኛ ደረጃን አግኝታለች - ከ140 ከተሞች፡፡ ከእንግሊዝ ከተሞች ለኑሮ አመቺ ተብላ ቀዳሚውን ሥፍራ የያዘችው ማንቸስተር ስትሆን ሀምሳ አንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡ ኦሎምፒክን በተሳካ ሁኔታ ያስተናገደችው ለንደን ደግሞ በሀዋሳ አምስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች - በኑሮ አመቺነት፡፡
ጥናቱ ለኑሮ የማይመቹ በሚል ከለያቸው ከተሞች ውስጥ ቴህራን፣ ትሪፖሊ፣ ካራቺ፣ አልጀርስ እና ሀራሬ የሚገኙበት ሲሆን የባንግላዴሽ ዋና ከተማ ዳካ ግን ለኑሮ እጅግ በጣም የማትመች ተብላለች፡፡
ከተማዋ ጥሩ ጎኖች እንዳሏት የጠቆመው ሪፖርቱ፤ የኢኮኖሚዋ ጥንካሬ እየተሻሻለ መምጣቱን፣ የትምህርት ዕድሎችን እያስፋፋች እንዲሁም የባህል ትስስሯም እጅግ ጥሩ እንደሆነ ቢጠቅስም በየአመቱ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚጨምረው የህዝብ ብዛቷ የአራት መቶ አመት እድሜ ያላትን ዳካ የተጨናነቀች ከተማ እንድትሆን አድርጓታል ብሏል፡፡