Saturday, 06 March 2021 13:22

አረና፤ በትግራይ የተፈጸሙ ሰብአዊ ጥቃቶች በገለልተኛ አካል እንዲጣሩ ጠየቀ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በክልሉ ዘላቂ መረጋጋት እንዲመጣ የመፍትሄ ሃሳቦችን ጠቁሟል

               ከወራት ዝምታ በኋላ ከሰሞኑ በትግራይ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ ያወጣው አረና፤ በክልሉ ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ የተፈፀሙ ሰብአዊ ጥቃቶች፣ የንብረት ዘረፋና ውድመት በገለልተኛ አካል እንዲጣራ እንዲሁም የኤርትራ ወታደሮች ከአካባቢው እንዲወጡና ክልሉ ቀድሞ ሲያስተዳድረው የነበረው ግዛቱ እንዲከበርለት ጠይቋል፡፡
የህወኃት ቡድን በነፍጥ መሸነፉን ተከትሎ፣ በትግራይ ተጨባጭ መረጋጋት ያልመጣባቸውን ምክንያቶች  የዘረዘረው አረና፤ ከጦርነቱ በኋላ መጠነ ሰፊ ውድመት፣ ዘረፋ እንዲሁም የሴቶች መደፈርን ጨምሮ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች መፈጸማቸውን በሰበብነት ይጠቅሳል፡፡ ቀደም ሲል ክልሉ ሲያስተዳድራቸው የነበሩ አካባቢዎች ከህገ መንግስቱ ውጪ በአማራ ክልል ቁጥጥር ስር መሆናቸው እንዲሁም  በዚሁ ሂደት የአካባቢው ነዋሪ በትግራይ ተወላጆች ላይ ወከባና ዘረፋ መፈፀሙም ላለመረጋጋቱ ምክንያት  ነው ብሏል - ፓርቲው፡፡  
በተመሳሳይ፤ የኤርትራ ሰራዊት የትግራይ የተለያዩ አካባቢዎችን ተቆጣጥሮ መገኘቱ፣ ይህን ተከትሎም ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች መፈፀማቸውም ላለመረጋጋቱ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን አረና ይገልጻል፡፡  
የክልሉን ሰላምና መረጋጋት ለማረጋገጥ ይበጃሉ ተብለው በፓርቲው በመፍትሄነት ከተዘረዘሩት መካከልም፤ ሁሉን አቀፍ ሰብአዊ ድጋፍ በትኩረት ማከናወን፣ የመንግስት ተቋማት ወደ ስራ እንዲገቡና በአስቸኳይ የሰው ሃይልና የሃብት ምደባ እንዲደረግላቸው፣ ህገ መንግስታዊ እውቅና ያለውን የትግራይ ግዛት እንዲረጋገጥ እንዲሁም የአማራ ክልል ልዩ ሃይል ከትግራይ አካባቢዎች እንዲወጣ ማድረግ የሚሉት ይገኙባቸዋል፡፡  
በተጨማሪም የኤርትራ ጦር አካባቢውን ለቆ እንዲወጣ፣ ተፈፅሟል የተባሉ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶችም በገለልተኛ አካል ተጣርተው እውነታው እንዲታወቅ፣ አጥፊዎችም እንዲቀጡ ጠይቋል፤ አረና በመግለጫው፡፡


Read 11963 times