Saturday, 06 March 2021 13:38

ካራማራ - ሌላዋ አድዋ!

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

https://youtu.be/YQQj3D5F4bM?t=98

 ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቃት በኋላ በእንግሊዝ ሞግዚት አስተዳደር ሥር የቆየችው የኢጣሊያ ሶማሌ ላንድና የእንግሊዝ ሶማሌ ላንድ፤ ሶማሌ በሚል መጠሪያ፣ በ1951 ዓ.ም አንድ አገር ሆና ነፃነቷን አገኘች።
እንግሊዞች በኢትዮጵያ፣ በጅቡቲና ኬንያ ውስጥ የሚገኙ የሶማሊኛ ቋንቋ ተናጋሪዎችን ወደ አንድ የመሰብሰብና አንድ አገር የማድረግ ሃሳብ ስለነበራቸው፣ የነፃዋ የሶማሌ መንግሥት ይህን ሃሳብ ተቀብሎ፣ ሰንደቅ ዓላማው ላይ ባለ አምስት ጫፍ ያለው ኮኮብ በአርማነት ይዞ ተነሳ። የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመሥረቻ ቻርተር፤ “አገሮች ነፃነታቸውን ባገኙ ጊዜ በያዙት ድንበር ይወሰናሉ” የሚል ድንጋጌ ቢኖረውም፣ ሶማሌ በኢትዮጵያ ላይ የግዛት ይገባኛል ጥያቄዋን ማራገብ ተያያዘችው። በ1956 ዓ.ም የመጀመሪያውን ወረራ በኢትዮጵያ ላይ ከፈተች።
በዚህ ዘመን የጎጃም ጠቅላይ ግዛት እንደራሴ፣ የአምስት ዓመቱ አርበኛ ደጃዝማች ፀሐይ እንቁ ሥላሴ ነበሩ። እኔም በወቅቱ ደብረ ማርቆስ በሚገኘው በንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ትምህርት ቤት፣ የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ነበርኩ። የሶማሌን ወረራ በመቃወም ተማሪዎች ተሰልፈን ወደ ደብረ ማርቆስ ቤተ-መንግሥት ሄድን። ጠንከር ጠንከር ያሉት ጓደኞቻችን አዝምቱን ብለው ደጃዝማች ፀሐይን ጠየቁ። ገናናው መሐሪ የተባለ ጓደኛዬ፡-
 “እነዚያን ወይፈኖች ዳገት ላይ ጠምዳችሁ
አመላለሱ ላይ እንዳይቸግራችሁ።”… ሲል አቅራራ።
በእርግጥም ሶማሌ መመለሻው ቸገራት። ነፍሳቸውን ይማረውና፣  እነ ጄኔራል አማን አንዶም ሶማሌ ግዛት ዘልቀው ገብተው ወደ ኋላ እንዲመለሱ የተደረጉት በንጉሡ ትእዛዝ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ሶማሌን ይህ ሽንፈቷ እጇን ሰብስባ አርፋ እንድትቀመጥ አላደረጋትም። እንደ ሰሜን ሶማሌ ነፃ አውጪ ድርጅት ያሉትን የደፈጣ ተዋጊ ቡድኖችን በማቋቋምና ሌሎችንም በትጥቅ በመደገፍ ኢትዮጵያን ሰላም መንሳት ቀጠለች።
አዲሱ የደርግ መንግሥት፤ በሰሜን በሻዕቢያና በጀብሃ፣ በምሥራቅ በሶማሌ ሰርጎ ገቦች ተወጥሮ ተያዘ። የሻዕቢያና የጀበሐ እንቅስቃሴ መንግሥትን እያሰጋው በመምጣቱ ዘጠነኛ መካናይዝድ ብርጌድን ከምሥራቅ ወደ ሰሜን አንቀሳቀሰ። ይህም ለሶማሌዎች የተመቸ ሁኔታ ፈጠረ። ሰኔ 7 ቀን 1969 ዓ.ም የኢትዮጵያን ድንበር በመጣስ  የቶጎ ውጫሌን ፖሊስ ጣቢያን ደመሰሱ። ውጊያው በየቀኑ ክበቡን እያለፈ ሄደ። ዋርዴር ቀበሬ ደሐር፣ ደጋሃቡር፣ ወዘተ-- የመዋጊያ አካባቢዎች ሆኑ። የሶማሌን ጦር ባለበት እንዲገደብ ማድረግ ቀላል ሆነ አልተገኘም።
ሶቭየቶች እስከ አፍንጫው ያስታጠቁት የጄኔራል ዚያድ ባሬ ጦር፣ በሰው ኃይልም ሆነ በመሳሪያ  ከፍተኛ ብልጫ እንደነበረው ብርጋዴል ጄኔራል ካሣዬ ጨመዳ “የጦር ሜዳ ውሎዎች፡- ከምሥራቅ እስከ ሰሜን” በተባለው መጽሐፋቸው፤ “አንድ ለስምንት ነበርን” በማለት ገልጸዋል። የሶማሌ ጦር 180 ሺህ መደበኛ ወታደር መያዙን፣ 250 ታንኮች ፣ 340 ብረት ለበስ፣ 600 መድፍ መታጠቁን እንዲሁም  12 ሞተራይዝድ ብርጌድ ማሰለፉን ጄኔራሉ ዘርዝረዋል።
ጦርነቱ እየሰፋ ሄደ። ጎዴ፣ ኮምቦልቻ፣ ፈዲስ፣ ባቢሌ፣ ጉርሱም ወዘተ አሁንም የጦር ሜዳዎች ሆኑ። ጅጅጋ አካባቢ አዝማች የነበሩት ኮሎኔል ኃይሌ ተስፋ ሚካኤል፣ ረዳት ጦር እንዲላክላቸው ወትውተው ወትውተው የሚደርስላቸው ባጡ ጊዜ “ሱልጣን ኢብራሃም አሰብን እንደሸጠው ሁሉ ኃይሌ ተስፋ ሚካኤል ጅጅጋን ሸጠ ተብዬ በታሪክ መወቀስ አልፈልግም። ኃላፊነቱን ተረከቡኝ።” በማለት ለፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ድብዳቤ እስከ መላክ መገደዳቸውን ታሪክ ዘግቦታል።
የሠራዊቱ ችግር ይህ ብቻ አልነበረም። “የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው” የሚል ፍልስፍና ይከተሉ የነበሩ እንደ ኢሕአፓ ያሉ ማርክስስ ሌኒኒስት የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ ደርግን ለመጣል በማሰብ “ጠላትህ ያለው መሐል አገር ነው፤ ፍልሚያህን ወደ እሱ አዙር” የሚል ቅስቀሳ በማካሄዳቸው፣ የሠራዊቱ ልብ ለሁለት ተከፍሎ እንደነበር የጻፉት ብርጋዴር ጀኔራል ካሣ ጨመዳ፤ ከጦር ሜዳ በሸሹና እራሳቸውን ከውጊያ ባገለሉ ላይ መንግሥት እርምጃ መውሰዱን አውስተዋል፡፡
ሚያዚያ 4 ቀን 1969 ዓ.ም ፕሬዚዳንት መንግሥቱ፣ የእናት አገር ጥሪ አቀረቡ። አገሬን ያሉ ወጣቶችና የቀድሞ ወታደሮች ከከተማና ከገጠር ወደ አዲስ አበባ ተመሙ። የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እድሮች፣ ድንኳናቸውን ለሠልጣኙ ሠራዊት መጠለያ እንዲሆን ሰጡ። የድሮው ሥጋ ሜዳ “ታጠቅ” የሚል ስም ተሰጥቶት 300 ሺህ  ሕዝባዊ  ሠራዊት የሚሰለጥንበት ካምፕ ሆነ። ለጦሩ እንጀራ በመጋገር፣ ወጥ በመሥራት፣ የበሶ እህል በማዘጋጀት የአዲስ አበባ ሴቶች  ቀጥ ብለው ተሰለፉ።
ሰኔ 18 ቀን 1969 ዓ.ም ሕዝባዊ ሠራዊቱ በአብዮት ማለትም በአሁኑ መስቀል አደባባይ የሰልፍ ትርኢት አቀረበ። ከፖሊስ  ሰራዊት ተመርጠው ጦሩን እንዲቀላቀሉ ከተደረጉት የመቶ መሪዎች አንዱ ትልቅ ወንድሜ ም/መቶ አለቃ ዳኛቸው አስረስ ነበር።  ለእሱ የተሰጠው ግዳጅ ወደ ሰሜን ስለነበር ከዚያ ቀን በኋላ ዳግሞ ሳላየው በመቅረቴ ዛሬም ድረስ አዝናለሁ።
ከኩባና ከየመን ወታደራዊ ድጋፍ ያገኘው የኢትዮጵያ መንግሥት፤ ድሬደዋና ሐረርን ለመያዝ የተደረገውን የማጥቃት ዘመቻ ከህዝብ ጋር ሆኖ በመቀልበስ፣ የሶማሌን ጦር እያሳደደ መቅጣቱን ጀመረ። ወደ አንድ ወር ለሚጠጋ ጊዜ የዘለቀው የፈዲስ ጦርነት፣ በኢትዮጵያ አሸናፊነት መጠናቀቅ፣ ሐረርን እፎይ ከማሰኘቱ በላይ ካራማራን ለማስለቀቅ ለተደረገው ውጊያ አስተዋጽኦ ነበረው።
የካቲት 26 ቀን 1970 ዓ.ም ካራማራ በኢትዮጵያ ሰራዊት እጅ ገባች። የካራማራ ነፃ መሆን ከዚያ በኋላ የሶማሌን ጦር እያሳደዱ ለመቅጣት የተመቸ ሁኔታ ተፈጠረ። ካራማራ በኢትዮጵያ የጦርነት ታሪክ ውስጥ ሌላዋ አድዋ ለመሆን በቃች፤የአድዋም ድል እየተከበረ እንዲቀጥል አስቻለች፡፡
ይህ ዝም ብሎ የተሰነዘረ ሃሳብ አይደለም። ዚያድባሬ ተሳክቶለት ቢሆን ኖሮ፣ ጣናንም የመቆጣጠር ሃሳብ እንደነበረው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
እንኳን ለ43ኛው የካራማራ ድል አደረሳችሁ!
ክብር በዚህ ጦርነት መስዋዕት ለሆኑ ወገኖቻችን ሁሉ!


Read 3738 times Last modified on Monday, 08 March 2021 18:39