Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 18 August 2012 12:24

የ30ኛው ኦሎምፒያድ ማስታወሻ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የጀግኖች አቀባበልና የተገኘው ውጤት

በለንደን ኦሎምፒክ ተሳትፈው የነበሩ የኢትዮጵያ ኦሎምፒያኖች ባለፈው ሐሙስ ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡ ጀግኖቹን ኦሎምፒያኖች በአዲስ አበባ ስቴዲየም በሺህ የሚቆጠረውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድ አይነት ስሜት ዳግም ለመሰብሰብ በቅተዋል፡፡ የስፖርት ቤተሰቦቹ በስቴዲየሙ ተሰብስበው የአትሌቶቻችንን መምጣት በጉጉት የሚጠባበቁት ከግል ጉዳያቸው ይበልጡኑ የጋራ የሆነውን ስሜታቸውን ለመግለጽ ነበር፡፡ ሁሉንም በአንድነት፣ ሊያመሳስላቸውና አንድ ሊያደርጋቸው በቻለው ኢትዮጵያዊነት አትሌቶቹን ከወንበሮቻቸው ተነስተው በደማቅ ሆታ እና እልልታ አከበሯቸው፡፡ አገራዊ ስሜታቸውን፣ አድናቆታቸውን፣ ምስጋናቸውን፣ ክብራቸውን ኃይል ባለው የፍቅር ቃላቶቻቸው ገለፁላቸው፡፡ አትሌቶቹም አድናቆቱንም፣ ምስጋናውንም፣ ክብሩንም መቀበላቸውን እጆቻቸውን በማወዛወዝ በፊት ፈገግታቸው ምላሻቸውን ለሚወዷቸና ለሚያከብሯቸው ሁሉ ሰጡ፡፡

 

ለንደን ባስተናገደችው 30ኛው ኦሎምፒያድ 3 የወርቅ፤ አንድ የብርና 3 የነሐስ በአጠቃላይ 7 ሜዳልያዎችን የሰበሰበችው ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሁለተኛ እንዲሁም ከዓለም 25ኛ ደረጃ ለማግኘት በቅታለች፡፡ ከተገኙት 7 ሜዳልያዎች 3 የወርቅ እና 2 ነሐስ ሜዳልያዎችን ሴት ኦሎምፒያኖቻችን በመጎናፀፍ ከፍተኛውን ድርሻ ሲወስዱ ወንድ ኦሎምፒያኖች የወርቅ ሜዳልያ ድል ሳይሆንላቸው ቀርቶ ቀሪዎቹን አንድ የብርና ሌላ የነሐስ ሜዳልያ በማግኘት ተወስነዋል፡፡ በአፍሪካ ደረጃ በለንደን ኦሎምፒክ በአንደኛነት የተቀመጠውን የሜዳልያ ስብስብ ያገኘችው 3 የወርቅ፤ ሁለት የብርና 1 የነሐስ ሜዳልያ ያገኘችው ደቡብ አፍሪካ ስትሆን በዓለም 24ኛ ደረጃ አግኝታበታለች፡፡ የኢትዮጵያ የቅርብ ተቀናቃኝ ኬንያ ደግሞ በ2 የወርቅ፤ 4 የብርና 5 የነሐስ ሜዳልያዎች ሜዳልያዎችን በማግኘት ከአፍሪካ 3ኛ እንዲሁም ከዓለም 28ኛ ደረጃ ወስዳለች፡፡

ስፖርት ሪፈራንስ በተባለ ድረገፅ በሰፈረው መረጃ መሰረት ኢትዮጵያ እስከ 30ኛው የለንደን ኦሎምፒያድ በ12 አገራት በተካሄዱ 12 ኦሎምፒያዶች በ5 የተለያዩ ስፖርቶች በተደረጉ 35 የውድድር መደቦች ተሳትፋለች፡፡ በእነዚህ ተሳትፎዎቿም 210 ኦሎምፒያኖች 164 ወንዶችና 46 ሴቶችን ለውድድር አብቅታለች፡፡ በ1980 እኤአ ላይ በሞስኮ ኦሎምፒክ የኢትዮጵያ   ወጣቷ ኦሎምፒያን በመሆን በ16 ዓመት ከ221 ቀናት እድሜዋ የተመዘገበችው ፋንታዬ ሲራክ ስትሆን፤ በ172 እኤአ በተካሄደው የሙኒክ ኦሎምፒክ ማሞ ወልዴ በ40 አመት ከ91 ቀናት እድሜው አንጋፋው ኦሎምፒያን ነበር፡፡ ከለንደን ኦሎምፒክ በኋላ በምንግዜም የኦሎምፒክ የሜዳልያ ስብስብ በተለይ በአትሌቲክስ ውድድሮች በወጣ ደረጃ አሜሪካ 328 የወርቅ፤ 2511 የብርና 202 የነሐስ በአጠቃላይ 781 ሜዳልያዎች በመሰብሰብ 1ኛ ስትሆን እንግሊዝ በ203 ሜዳልያዎች 56 የወርቅ 84 የብርና 63 የነሐስ እንዲሁም ራሽያ በ193 ሜዳልያዎች 64 የወርቅ፤ 55 የብርና 74 የነሐስ በማስመዝገብ እስከ 3ኛ ደረጃ ይዘዋል፡፡ ኬንያ በ7 ሜዳልያዎች በ24 የወርቅ፤ በ31 የብርና በ24 የነሐስ ስብስብ 8ኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ ኢትዮጵያ በ45 ሜዳልያዎች በ21 የወርቅ፤ በ7 የብርና በ17 የነሐስ ስብስቧ ከዓለም 16ኛ ደረጃ ኖሯታል፡፡

ቢቢሲ በ30ኛው ኦሎምፒያድ የተሳተፉ 205 አገራት ባወዳደሯቸው አትሌቶች ልክ ከፍተኛውን የሜዳልያ ድርሻ አስመዝግበዋል በሚል ባወጣው የደረጃ ስሌት የኢትዮጵያን ውጤታማነት በአራተኛነት አስፍሮታል፡፡ ሰርቢያና ሞንቲኔግሮ ካሳተፈቻቸው 34 ኦሎምፒያኖች 14 የሜዳልያ ድል ያስመዘገቡ በማስቆጠር በ41 በመቶ አንደኛ ደረጃ አግኝታለች፡፡ 542 ኦሎምፒያኖችን አወዳድራ 208 የሜዳልያ ድል የወሰዱ አትሌቶችን በማስመዝገብ በ38 በመቶ አሜሪካ ሁለተኛ ደረጃ ሲሰጣት፤ ጃማይካ 50 ኦሎምፒያኖችን ለውድድር አቅርባ 18 የሜዳልያ ድል ያገኙ አትሌቶችን በማስመዝገብ በ36 በመቶ ውጤታማነት ሶስተኛ ሆናለች፡፡ ኢትዮጵያ ከነበሯት 35 አትሌቶች ስድስት ለሜዳልያ ያበቁ አትሌቶችን በማግኘት  በ17 በመቶ ውጤታማነት ለአራተኛ ደረጃ በቅታለች፡፡

የኬንያ ኪሳራ

ከ4 አመት በቤጂንግ ኦሎምፒያድ ያስመዘገበችውን ውጤት በእጥፍ ለማሳደግ እና እስከ 12 የወርቅ ሜዳልያዎች በለንደን ኦሎምፒክ ለማስመዝገብ አቅዳ የነበረችው ኬንያ በ30ኛው ኦሎምፒያድ ያልተጠበቀ የውጤት ኪሳራ ገጥሟታል፡፡ ከኬንያ ኦሎምፒክ ቡድን አባላት አንዳንዶቹ ለዳይመንድ ሊግ ውድድር በአውሮፓ ሲቀሩ ሌሎች ደግሞ በተዘበራረቀ የጉዞ ፕሮግራም ካለፈው ረቡእ አንስቶ አገራቸው ሲገቡም የገጠማቸው ቀዝቃዛ አቀባበል ነው፡፡ በለንደን 11 ሜዳልያዎችን የሰበሰበችው ኬንያ ለገጠማት የውጤት ኪሳራ ዝርዝር ሪፖርት በአጭር ግዜ ተዘጋጅቶ ለመላው ህዝብ ይፋ እንደሚሆን የስፖርት ሚኒስትር ተወካይ መናገራቸውን የዘገበው ካፒታልኤፍኤም የተባለ የአገሪቱ ሚዲያ ነው፡፡ የኬንያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ሊቀመንበር ኪፕቾጌ ኬኖ በተመዘገበው ያልተጠበቀ ውጤት የተሰማቸውን ቁጭት አገራቸው እንደገቡ በለቅሶ ገልፀዋል፡፡ ኪፕቾጌ ለቀጣይ የኦሎምፒክ ተሳትፏችን ከወዲሁ መዘጋጀት አለብን ብለው ሲናገሩ የኬንያ ሚዲያዎች በበኩላቸው ኬንያ ለገጠማት የውጤት ኪሳራ በውድድሩ አመራር የነበረው ድክመት ተጠያቂ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የኬንያ ኦሎምፒክ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ጁለዬስ ኪሪዋ በበኩላቸው ለታየው የውጤት ችግር አሰልጣኞች ተጠያቂ መደረጋቸው አግባብ አለመሆኑን በመናገር የኬንያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ እና የአትሌቲክስ ፌደሬሽኑ መቃቃር ተፅእኖ ማሳደሩ እንዲመረመርላቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ዋና አሰልጣኙ በተጨማሪ በሰጡት አስተያየት ለተፈጠረው የውጤት ኪሳራ የኦሎምፒክ ኮሚቴው አትሌቶች ለኦሎምፒኩ የመጨረሻ ዝግጅታቸውን እንግሊዝ ውስጥ በሚገኘው የብሪስቶል ካምፕ እንዲያከናውኑ ጫና ማድረጉን ሰበብ እንደሚሆን አመልክተው አትሌቶችና አሰልጣኞች ለውድድሩ የሚያደርጉትን የመጨረሻ ዝግጅት በአገራቸው ለማድረግ የነበራቸው ፍላጎትን ማስፈፀም አለመቻላቸው ክፍፍል እንደፈጠረባቸው በምሬት አውስተዋል፡፡ አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች ደግሞ በኬንያ የኦሎምፒክ ቡድን የተያዙ አትሌቶች በነፍስወከፍ በተለያዩ ማናጀሮችና አሰልጣኞች የመስራት ልማድ እያበዙ መምጣታቸው በኦሎምፒኩ በተዘበራረቀ ታክቲክ እና አስተሳሰብ እንዲሰለፉ ተፅእኖ ፈጥሮ የቡድን ስራቸውን በማዳከም ለኪሳራ እንደዳረጋቸው ተናግረዋል፡፡

 

የአፍሪካ መዳከም

አፍሪካ በለንደን ኦሎምፒክ ከአራት አመት በፊት ቤጂንግ ላይ ካስመዘገበችው ውጤት ያነሰ የሜዳልያ ስብስብ ሊኖራት የቻለው በአትሌቲክስ ስፖርት ብቻ ከተወሰነው የኦሎምፒክ ተሳትፎዋ ጋር በተያያዘ መሆኑን አንዳንድ መረጃዎች ይገልፃሉ፡፡ ለንደን ላይ አፍሪካ በቤጂንግ ካገኘችው ድል በአራት ወርቅ እና በአንድ የብር ሜዳልያ ያነሰ ውጤት ተመዝግቦባታል፡፡ በ30ኛው ኦሎምፒያድ ከኢትዮጵያ ሴት አትሌቶች የረዥም ርቀት አንፀባራቂ ድሎች ባሻገር በ1500 ሜትር በአልጄሪያዊው ታውፊክ ማኩልፊ የተገኘው የወርቅ ሜዳልያ ድል፤ በ23 አመቱ ኡጋንዳዊ የማራቶን ጀግና ስቴፈን ኪፕሮቺች የተገኘው የወርቅ ሜዳልያ እና በ800 ሜትር የኬንያው ዴቪድ ሩዲሻ አዲስ የዓለም ሪከርድ አስመዝግቦ የወርቅ ሜዳልያ ሲወስድ እሱን ተከትሎ በመግባት የብር ሜዳልያ በተጎናፀፈው የቦትስዋናው አትሌት ኒጄል አሞስ የተፈፀሙ ገድሎች ተደንቀዋል፡፡ግብፅ በሁለት የብር ሜዳልያዎች፣ ቱኒዚያ በ3ሺ መሰናክል 1 ብር እና በ1500 1 ነሐስ እንዲሁም በተመሳሳይ ውድድር ሞሮኮ የነሐስ ሜዳልያ በማግኘት በሰሜን አፍሪካ ላለው የኦሎምፒክ ተሳትፎ መነቃቃት ፈጥረዋል፡፡ በቅርጫት ኳስ፤ በቦክስ፤ በጠረጴዛ ቴኒስ፤ በቴክዋንዶ፤ በክብደት ማንሳት በነፃ ትግልና በአጭር ርቀት የሩጫ ውድድሮች ሰፊ ተሳትፎ ያደረገችውቨ ናይጄርያ ያለአንዳች የሜዳልያ ስኬት ባዶዋን መመለሷ አሳዛኙ ውጤት ተብሏል፡፡ በሌላ በኩል በ30ኛው ኦሎምፒያድ ከተሳተፉ የአፍሪካ አገራት 21 አትሌቶች እና የልዑካን ቡድን አባላት በእንግሊዝ ጥገኝነት በመጠየቅና በመጥፋት ወደ አገራቸው ሳይመለሱ ቀርተዋል፡፡ በእንግሊዝ ጥገኝነት ከጠየቁት እና ከጠፉት የአፍሪካ ኦሎምፒያኖች እና ሌሎች የልዑካን አባላት 1 የኢትዮጵያ፤2 የሱዳን፤ 3 የጊኒ፤3 የአይቬሪኮስት፤ 5 የኮንጎ እንዲሁም 6 የካሜሮን ቦክሰኞች ይገኙበታል፡፡

 

የአፍሪካ የኦሎምፒክ መስተንግዶ ለመቼ?

ከ30ኛው የለንደን ኦሎምፒያድ መጠናቀቅ በኋላ በርካታ የአፍሪካ ኦሎምፒክ ልዑካን ቡድኖች አመራሮች አህጉሪቱ ኦሎምፒክን የማስተናገድ ጊዜ ላይ መድረሷን ገልፀዋል፡፡ የደቡብ አፍሪካ የኦሎምፒክ ቡድን መሪ በሰጡት አስተያየት አገራቸው የአለም ዋንጫን ካዘጋጀች በኋላ በቀጣይነት ለኦሎምፒክ መስተንግዶ ተስፋ በማድረግ ባደረገችው ሙከራ ከ2020 እና ከ2024 እኤአ ከሚካሄዱ ኦሎምፒኮች አዘጋጅነት ፉክክር ውጭ መሆኗን ገልፀው በቀጣይ ለመስተንግዶ ያላቸውን ራእይ በመግለፅ በተለይ ግብፅ፤ናይጄርያና ኬንያ ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪ አድርገዋል፡፡ የኬንያው ጠቅላይ መኒስትር ራኢላ ኦዲንጋ በለንደን ኦሎምፒክ ክብር እንግዳ ሆነው በተገኙበት ወቅት አገራቸው በ2024 ኦሎምፒክን ለማስተናገድ ፍላጎት እንዳላት ብይፋ ሲገልፁ የኡጋንዳ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ዋና ፀሃፊ ሃብታሟ አህጉር አፍሪካ በስራቴጂካዊ እቅድ የኦሎምፒክ መስተንግዶን ማሳካት ትችላለች ብለው ድጋፍ ሰጥተዋል፡፡ ለንደን 30ኛው ኦሎምፒያድን ለማስተናገድ እስከ 15 ቢሊዮን ዶላር ወጭ ማድረጓን የገለፁ በበኩላቸው በራሃብ በበሽታና በተለያዩ ማህበረሰባዊ ችግሮች ለምትዳክረው አፍሪካ የኦሎምፒክ መስተንግዶ ቅደሚያ የሚሰጠው ጉዳይ አይሆንም ብለው በመቃወም ምናልባት ከ4 እና አምስት ኦሎምፒኮች በኋላ የአፍሪካ አገራት ለኦሎምፒክ ዝግጅት ተስፋ ቢያደርጉ እንደሚመረጥ መክረዋል፡፡ ዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በ2016 እኤአ ላይ የብራዚሏ ሪዮ ዲጄኔሮ፤ በ2020 ደግሞ የራሽያዋ ሞስኮ 31ኛውንና 32ኛውን ኦሎምፒያድ እንደሚያዘጋጁ ወስኗል፡፡ በ2024 እኤአ የሚቀጥለው 33ኛው ኦሎምፒያድን ለማስተናገድ ደግሞ የአፍሪካ ወይንም የመካከለኛው ምስራቅ አገራት አህጉሮቻቸው ውድድሩን ለመጀመርያ ጊዜ የማስተናገድ እድል እንዲኖራቸው ተስፋ ያደርጋሉ፡፡

 

ጥሩዬ የኢትዮጵያ አንደኛ ኦሎምፒያን

በ30ኛው ኦሎምፒያድ የአትሌቲክስ ውድድሮች ከ1 ሳምንት በኋላ ሲጀመሩ ከመክፈቻው ውድድሮች አንዱ የ10ሺ ሜትር ሴቶች ነበር፡፡ ይህንን ውድድር 22 አካባቢ በሚገኝ ሆቴል ከበርካታ ሰዎች ጋር የተመለከትኩት ከጓደኞቼ  ደራሲ ሌሊሳ ግርማ እና ከሰዓሊዋ ትዝታ ብርሃኑ ጋር ነበር፡፡ በወቅቱ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በ10ሺ ሜትር በሁለት ተከታታይ ኦሎምፒኮች ሁለተኛ የወርቅ ሜዳልያዋን በፍፁም የበላይነት በማስጠበቅ ስታሸንፍ ሁላችንም የተሰማን ደስታ ወሰን አልነበረውም፡፡ እኔ እንደ ስፖርት ጋዜጠኝነቴ ጥሩነሽ በኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ታሪክ ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገበች አትሌት እንደሆነች ገለፅኩላቸው፡፡ ደራሲ ሌሊሳ ግርማ በበኩሉ ጥሩነሽ ይቻላል በሚል በኃይሌ ገብረስላሴ የተነገበውን መርህ በሴቶች እውን በማድረጓ ትችላለች ያስብላል ሲል ተናገረ፡፡ ሰዓሊዋ ትዝታ በበኩሏ በጣም ተደስታ ምን ላድርግ ብላ ተጨነቀች፡፡ ለምን ድሏን የሚያንፀባርቅ ባለሙሉ ቀለም የመታሰቢያ ስእል አትሰሪላትም አልኳት፡፡

ይህ ሃሳብ ሁላችንንም ተስማማንበት፡፡ ሰዓሊ ትዝታ ብርሃኑ ከልብ በመነጨ አድናቆት ጥሩነሽን በቀለሞቿ ልታደምቃት የአሸናፊነቷን ምስል በብሩሿ ልትቀምር ቃል ገባች፡፡ ከጥሩነሽ ዲባባ አስገራሚ ድል ከ2 ሳምንት በኋላ በሸራ ላይ ወጥራ በሙሉ ቀለም የሳለችው ስእል ጀግኖቹ ኦሎምፒያኖች ከለንደን ወደ አገራቸው ሲመለሱ በገባችው ቃል መሰረት እነሆ ይሄው ስጦታዬ ብላ ለስፖርት አድማስ አበረከተች፡፡ ወጣቷ ሰዓሊ ትዝታ ብርሃኑ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ  የስነጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት በቀለም ቅብ የአራተኛ ዓመት ተማሪ ናት፡፡

በኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ተሳትፎ ታሪክ በ2004 እኤአ በአቴንስ፤ በ2008 እኤአ በቤጂንግ እንዲሁም በ2012 እኤአ በለንደን በተሳተፈችባቸው ሶስት ኦሎምፒኮች የ27 አመቷ ጥሩነሽ ዲባባ 5 (3 የወርቅና ሁለት የነሐስ) ሜዳልያዎችን በማግኘት በአንደኛ ደረጃ የከፍተኛ ውጤት ክብረወሰን ይዛለች፡፡

እነዚህ ሜዳልያዎች ላይ በ5ሺ ሜትር ነሐስ፤ ላይ በ10ሺ እና በ5ሺ ሁለት ወርቆች እንዲሁም ላይ በ10ሺ ወርቅ እና በ5ሺ ነሐስ ያገኘቻቸው ናቸው፡፡

አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በኦሎምፒክ ታሪክ በአትሌቲክስ ውድድሮች በ10ሺ እና በ5ሺ ሜትር በሰበሰበቻቸው 3 የወርቅና 32 የነሐስ ሜዳልያዎች ከዓለም አትሌቶች በ25ኛ ደረጃ ላይ ደርሳለች፡፡

 

መሲ የ5ሺ ንግስት

ከ8 አመት በፊት በአቴንስ በኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ታሪክ በሴቶች 5ሺ ሜትር ፈርቀዳጁን የወርቅ ሜዳልያ ያስመዘገበችው አትሌት መሰረት ደፋር በለንደን ኦሎምፒክ ለሁለተኛ ግዜ በወሰደችው የርቀቱ ሁለተኛ የወርቅ ሜዳልያ የርቀቱ ንግስት መሆኗ ተረጋግጧል፡፡

አትሌት መሰረት ደፋር በ3 ኦሎምፒኮች የተሳትፎ ታሪኳ በ5ሺ ሜትር ሁለት የወርቅ እና አንድ የነሐስ ሜዳልያ በማግኘት በዓለም አቀፍ ደረጃ ግንባር ቀደሙን ውጤት ለማስመዝገብም በቅታለች፡፡

በኦሎምፒክ መድረክ በሴቶች የ5ሺ ሜትር ውድድር መካሄድ የጀመረው በ1996 እኤአ ላይ አትላንታ ኦሎምፒክ ላይ ሲሆን ከዚያን ግዜ ወዲህ በተካሄዱ 5 ኦሎምፒኮች የኢትዮጵያ ሴት አትሌቶች ከፍተኛውን ውጤት በማስመዝገብ ይመራሉ፡፡

የኢትዮጵያ ሴቶች በ5 ኦሎምፒኮች 4 የወርቅና 5 የነሐስ ሜዳልያዎች አግኝተዋል፡፡ በ1996 እኤአ ላይ በአትላንታ ኦሎምፒክ የሴቶች 5ሺ ሜትር ውድድር ሲካሄድ አሸናፊዋ የቻይናዋ አትሌት ነበረች፡፡ በ2000 እኤአ ላይ በሲድኒ ኦሎምፒክ የሮማንያዋ ጋብሬላ ዛቦ የወርቅ ሜዳልያውን የአየርላንዷ ሶኒያ ሱሊቫን የብር ሜዳልያውን ሲወስዱ አትሌት ጌጤ ዋሚ የነሐስ ሜዳልያውን በመውሰድ ፈር ቀደደች፡፡ በ2004 እኤአ አቴንስ ላይ አትሌት መሰረት ደፋር ወርቅ ሜዳልያውን ስትቀዳጅ፤ የብር ሜዳልያውን ኬንያዊ አትሌት ወስዳ የነሐስ ሜዳልያው ደግሞ የጥሩነሽ ነበረ፡፡ ከ4 ዓመት በፊት ቤጂንግ ላይ የወርቅ ሜዳልያውን ጥሩነሽ ዲባባ ስትወስድ ደግሞ ለቱርክ የምትወዳደረው ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ኤልቫን አብይ ለገሰ ብሩን ወሰደችና ለመሰረት ደፋር የነሐስ ሜዳልያው ድል ተመዘገበ፡፡ በ30ኛው ኦሎምፒያድ ደግሞ የወርቅ ሜዳልያው ተራ ለመሰረት ደፋር ሲሆን የኬንያዋ ቪቪያን ቼሮይት ብሩን ወስዳ ጥሩነሽ ዲባባ ደግሞ የነሀስ ሜዳልያውን ልትጎናኘፍ ችላለች፡፡

በሌላ በኩል በወንዶች 5ሺ ሜትር የኦሎምፒክ ውድድር ላይ ኢትዮጵያ 3 የወርቅ ሜዳልያዎችን በታሪኳ በማስመዝገብ ነበር በለንደን ኦሎምፒክ የተሳተፈችው፡፡ እነዚህ ወርቆች በ1980 እኤአ በሞስኮ ኦሎምፒክ በምሩፅ ይፍጠር፤ በ2000 እኤአ ሲድኒ ኦሎምፒክ ላይ በሚሊዮን ወልዴ እንዲሁም ከ4 ዓመት በፊት ቤጂንግ ላይ በቀነኒሳ በቀለ የተገኙ ነበሩ፡፡ በ30ኛው የለንደን ኦለምፒያድ ላይ የወርቅ ሜዳልያው ባይገኝም ወጣቱ አትሌት ደጀን ገብረመስቀል የብር ሜዳልያውን ሊያገኝ ችሏል፡፡

በ5ሺ ሜትር በሁለቱም ፆታዎች ተይዘው ያሉት የዓለም ሪከርዶች በኢትዮጵያ አትሌቶች የተመዘገቡ ናቸው፡፡ በወንዶች ሪከርዱ የአትሌት ቀነኒሳ በቀለ ሲሆን በ12 ደቂቃ ከ37.35 በሆነ ጊዜ የተመዘገበ ነው፡፡ በሴቶች የዓለምን ሪከርድን የያዘችው ደግሞ በ14 ደቂቃ ከ24.53 ሰኮንዶች በሆነ ግዜ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ናት፡፡ በ5ሺ ሜትር የኦሎምፒክ ውጤቷ በሁለት ወርቅና 1 ነሐስ ከኢትዮጵያ ኦሎምፒያኖች ከፍተኛውን ውጤት የያዘችው መሰረት ደፋር ብርቀቱ የምንግዜም ፈጣን ሰዓቶች ደረጃ በሁለተኛ ደረጃ የተመዘገበ ሰዓት ያላት ስትሆን የዓለምን ሪከርድ ለመጀመርያ ግዜ ወደ ኢትዮጵያ ያስገባችና ለሁለት ግዚያት ያሻሻለች ብርቅዬ አትሌት ነች፡፡ በ2006 እኤአ ላይ በአሜሪካ ኒውዮርክ በ14 ደቂቃ ከ24.53 ሰኮንዶች በሆነ ግዜ የመጀመርያውን የኢትዮጵያዊ የ5ሺ ሜትር ሪከርድ ያስመዘገበችው መሰረት ከዓመት በኋላ ይህን ክብረወሰኗን በኖርዌይ ኦስሎ በ14 ደቂቃ ከ16.63 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ አሻኽላ እንደነበር አይዘነጋም፡፡

 

ቦልት፤ የዓለምና የኦሎምፒክ ሪከርዶች

ዩሲያን ቦልት በቤጂንግ ኣሎምፒግ ያገኘውን የ100 ሜ፣ የ200 እና የ4 100 ሜትር ዱላ ቅብብል ውድድሮች በለንደን ኦሎምፒክ በማስጠበቅ 3 የወርቅ ሜዳሊያዎችን በድጋሚ ወስዶ በአጭር ርቀት በውድድሩ ታሪክ ከፍተኛውን የውጤት ክብረወሰን አስመዝግቧል፡፡ በ100 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያውን ሲያሸንፍ ርቀቱን በ41 ርምጃዎች ሸፍኖ በ9.63 ሰኮንዶች የጨረሰው የ25 ዓመቱ ዩሲያን ቦልት አዲስ የኦሎምፒክ ሪኮርድ ሊያስመዘግብ ችሏል፡፡ በ200 ሜትር ሲያሸንፍ ደግሞ በሁለት ተከታታይ ኣሎምፒኮች በ100 እና 200 ሜትር የአጭር ርቀት ውድድሮች ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎችን በመውሰድ በታሪክ የመጀመሪያው አትሌት ሆኗል፡፡ 3ኛውን የወርቅ ማዳልያ ከሌሎች 3 የአጭር ርቀት ጃማይካዊየን ሯጮች ጋር ሲያስመዘግብ ደግሞ የ4 100 ሜትር የዱላ ቅብብል ውድድርን አዲስ የዓለም ሪከርድ በ36.84 ሰኮንዶች አስመዝግበዋል፡፡

 

ኡጋንዳዊው የማራቶን ጀግና

“ፀሎት አድርጉልኝ፡፡ ከባድ ፉክክር ወደ የሚደረግበት ኦሎምፒክ መሄዴ ነው፡፡ በርግጠኝነት ወደ አገሬ የምመለሰው የሜዳልያ ድል ይዤ ነው፡፡ ካሸነፍኩ ደግሞ በቀጥታ ከፕሬዚዳንቱ ጋር ተገናኝቼ የህይወት ዘመን የጡረታ ዋስትና መብቴ እንዲከበርልኝ እጠይቃለሁ” በማለት ለሚስቱ ፓትሪሺያ ቼሮፕ የመጨረሻ መልዕክቱን ያስተላለፈው የለንደን ኦሎምፒክ የማራቶን ጀግና ኡጋንዳዊው  ስቴፈን ኪፕሮቺች ነበር፡፡ ከድሉ በኋላ ደግሞ  አዛውንቶቹ የስቴፈን ወላጆች የኡጋንዳ መንግስት መኖርያ እና የቤት መኪና እንዲሰጣቸው በይፋ ጠይቀዋል፡፡

የማራቶን ጀግናው ወላጆች ለመንግስት በይፋ ባቀረቡት ጥያቄ በግብርና እና በእርዳታ በመያገኙት አነስተኛ ገቢ ቤተሰባቸውን እንደሚያስተዳድሩ ገልፀው አሁን ግን እርጅና ስለተጫጫናቸው አርሰው ልጆቻቸውን መመገብ እንደማይችሉ በመናገር አሁን ያሉበት የኑሮ ሁኔታ ለአንድ ታላቅ ጀግና ቤተሰብ የማይመጥን በመሆኑ ይታሰብልን ማለታውን የኡጋንዳው ጋዜጣ ዘ ቪዥን ዘግቦታል፡፡

 

 

Read 77372 times Last modified on Saturday, 18 August 2012 12:28