Thursday, 11 March 2021 00:00

“የሞላ! 8 ሰው የሞላ ወደ ጨረቃ! አብረን አንሄድም?” - ቢሊየነሩ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 በአሜሪካው ኩባንያ ስፔስኤክስ አማካይነት ወደ ጠፈር ሊጓዙ ትኬት የቆረጡት ጃፓናዊው የፋሽን ኢንዱስትሪ ዘርፍ ቢሊየነር ዩሳኩ ሜዛዋ፣ በመንኮራኩሯ በቀሩት 8 ክፍት ወንበሮች አብረዋቸው ወደ ጠፈር መጓዝ የሚፈልጉ ሰዎች ካሉ ፈጥነው እንዲመዘገቡ ለመላው አለም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ሜዛዋ ከ5 አመታት በፊት ከስፔስኤክስ ኩባንያ ጋር በፈጸሙት ስምምነት ወደ ጠፈር ለመጓዝ የመጀመሪያው ሰው መሆናቸው በተዘገበበት ወቅት፣ አብረዋቸው ወደ ጠፈር እንዲጓዙ ለ8 ታዋቂ አርቲስቶች ግብዣ እንደሚያደርጉ አስታውቀው እንደነበር ያስታወሰው ዘ ኢንዲፔንደንት፤ ባለፈው ረቡዕ ግን በትዊተር ገጻቸው ባሰራጩት አጭር የቪዲዮ መልዕክት መሄድ የምትፈልጉ ተመዝገቡ ሲሉ ጥሪ ማቅረባቸውን ዘግቧል።
“ለሁሉም የመንኮራኩሯ ወንበሮች ከፍያለሁ! ስምንት ወንበሮች ክፍት ናቸው!... ከየትኛውም የአለም ክፍል አብራችሁኝ መሄድ የምትፈልጉና የተለየ የፈጠራ ክህሎት አለን የምትሉ ተመዝገቡ” ያሉት ቢሊየነሩ፤ ከሁለት አመት በኋላ ወደ ጠፈር ለሚያደርጉትና በጨረቃ ዙሪያ ለሚንቀሳቀሱበት ጉዞ ምን ያህል ገንዘብ እንደከፈሉ የታወቀ ነገር እንደሌለ ዘገባው ገልጧል፡፡
የ45 አመቱ ጃፓናዊ ቢሊየነር “ዲርሙን” የሚል ስያሜ በተሰጠው በዚህ የጠፈር ጉዞ አብረዋቸው ለመሄድ ፍላጎቱ ያላቸው ግለሰቦች እስከ መጪው ሳምንት መጨረሻ በድረገጻቸው አማካይነት እንዲመዘገቡ ጥሪ ማቅረባቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ የመጀመሪያው ዙር ማጣሪያ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ መናገራቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡


Read 950 times