Saturday, 13 March 2021 11:40

ቦርዱ እስክንድር ነጋን በእጩነት አልቀበልም በማለቱ ክስ ሊቀርብበት ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

    ባልደራስ በእስር ላይ የሚገኙት  ሊቀ መንበሩን አቶ እስክንድር ነጋን በእጩነት እንዳያቀርብ መከልከሉ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን በፍ/ቤት እንደሚከስ አስታወቀ ቦርዱ በበኩሉ ታሳሪዎችን በእጩነትም በመራጭነትም ያልመዘገብኩት በአቅም ማነስ ምክንያት ነው ብሏል፡፡
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ሊቀ መንበሩን አቶ እስክንድር ነጋን፣ በየካ ምርጫ ወረዳ ለአዲስ አበባ ም/ቤት በእጩ ተወዳዳሪነት  አቅርቧቸው እንደነበር  ያመለከተው ፓርቲው፤ ምርጫ ቦርድ ያለ በቂ የህግ ማስረጃ በህግ ጥላ ስር ያለ ሰው በእጩነት መቅረብ አይችልም ብሎኛል-ብሏል፡፡
በስራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና ምርጫ ስነ ምግባር ደንብ፤ “ማንኛውም ሰው በህግ ወይም በፍ/ቤት ውሳኔ የመምረጥ ወይም መመረጥ መብቱ ያልተገፈፈ እንደሆነ በእጩነት መቅረብ እንደሚችል በግልፅ ይደነግጋል ያለው ባልደራስ፤ በህገ መንግስቱም አንቀጽ 20(3)፤ የተከሰሱ ሰዎች በፍርድ ሂደት ላይ ባሉበት ጊዜ በተከሰሱበት ወንጀል እንደ ጥፋተኛ ያለመቆጠር ወይም ንፁህ ሆኖ  የመገመት መብት እንዳላቸው የሚደነግገውን አንቀፅ  በመከራከሪያነት ጠቅሷል፡፡
“ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እነዚህን የህግ ድንጋጌዎች በጣሰ መልኩ የአቶ እስክንድር ነጋን በምርጫው ተወዳድሮ የመመረጥ መብት ገድቧል፤ ይህም በቦርዱ ገለልተኝነት ላይ ጥያቄ እንድናነሳ አስገድዶናል” ብሏል-ፓርቲው በመግለጫው፡፡
ቦርዱ በሊቀ መንበሩ ላይ የጣለውን ገደብ  አስመልክቶም ፍ/ቤት በመክሰስ ከምርጫ ቦርድ ጋር  እንደሚከራከርበት የገለፀው ፓርቲው፤ በዚያውም የፍትህ ስርአቱን  የምንፈትሽበት ሂደት ይሆናል ብሏል ፡፡
ጉዳዩን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በሰጡት ምላሽ ታሳሪዎችን  በተመራጭነትም በመራጭነትም ለመመዝገብ ያልቻልነው ሂደቱ ውስብስብ ስለሚሆንብንና በአለን ውስን አቅም ተፈጻሚነቱን ለማረጋገጥ ስለሚቸግረን ነው ብለዋል።
ህጉ የፅ/ቤት ውሳኔ ያላገኙ በእስር ላይ ያሉ ሰዎች በእጩነት እንዳይቀርቡ እንደማይከለክል ያመለከቱት ሰብሳቢዋ ለአፈጻጸም የሚመች ባለመሆኑና በአቅም ወስንነት እነዚህን አካላት  ማካተት አልተቻለም ብለዋል።

Read 1223 times