Saturday, 13 March 2021 11:46

በየመን ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በጅምላ ያቃጠሉት የሁቲ አማፅያን መሆናቸው ተነገረ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

    “በቃጠሎው ከ180 በላይ ኢትዮጵያውያን ሞተዋል”

           ባለፈው እሁድ በየመን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በጅምላ በእሳት አቃጥለው የገደሉት የሁቲ አማፂያን ናቸው ሲሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችና  የየመን የመንግስት ቃል አቀባይ ተናገሩ፡፡
በኢራን የሚደገፈው የሁቲ አማፂያን፣ ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች ወዳሉበት ቦታ በመግባት፣ ውጊያውን እንዲቀላቀሉ እንደጠየቋቸውና  ፍቃደኛ አለመሆናቸውን ተከትሎም፣ አማፂያኑ በእሳት አቃጥለው እንደገደሏቸው የየመን  መንግስት ቃል አቀባይ ለአረብ ኒውስ ተናግረዋል፡፡
 በጅምላ በእሳት ተቃጥለው የሞቱት በሙሉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች መሆናቸውን የጠቆሙት ቃል አቀባዩ፤ ቁጥራቸው ግን በውል እንደማይታወቅ የገለፁ ሲሆን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አክቲቪስቶች በበኩላቸው፤ ማቾቹ ከ180 በላይ እንደሚሆኑ ተናግረዋል፡፡
ቃል አቀባዩ ሙአመር አል አርያኒ፤ ሁቲዎች ስደተኞቹን በዘግናኝ ሁኔታ አቃጥለው ከገደሏቸው በኋላ በአካባቢው የጅምላ መቃብር ቆፍረው እንደቀበሯቸውም ጠቁመዋል፡፡
የሁቲ አማፅያኑ፤ ኢትዮጵያውያኑን ከመንገድ ላይ እና ከገበያ ቦታዎች ከሰበሰቧቸውና በአንድ ማዕከል ካጎሯቸው በኋላ ውጊያውን እንዲቀላቀሏቸው ማግባባት መጀመራቸውን፣ ነገር ግን ኢትዮጵያውያኑ ፍቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረታቸው፣ በማዕከሉን  እንዳሉ በእሳት እንዳገዷቸው ነው ቃል አቀባዩ ለአረብ ኒውስ ያስረዱት፡፡
በወቅቱ በማዕከሉ  9 መቶ ያህል ኢትዮጵያውያን እንደነበሩና በርካቶቹ እንደሞቱ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩትም ክፉኛ መቁሰላቸውን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡
ባለፈው እሁድ የካቲት 28 ቀን 2013 በየመን ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ የደረሰውን የጅምላ  ጭፍጨፋ ተከትሎ ኦፌኮ ባወጣው መግለጫ፤ በሁኔታው በእጅጉ ማዘኑን ገልፆ መንግስት ጉዳዩን በጥብቅ እንዲከታተል አሳስቧል፡፡ ኢዜማም በአደጋው የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን በመግለፅ መንግስት ለጉዳዩን ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ፤ ጉዳዩን እየተከታተለ  መሆኑን አስታውቋል፡፡


Read 11501 times