Sunday, 14 March 2021 00:00

ታላቅ ክብር ለአባት አርበኞች!

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

     (ግልፅ ደብዳቤ ለሶስቱ ተቋማት)
                     
              ይህ ግልጽ ደብዳቤ እንዲደርሳቸው የምፈልገው ሶስቱ ተቋማት፡- የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የጥንታዊ ኢትዮጵያ አርበኞች ማኅበር፣ እነሱን በሚመሩት ዶ/ር  ሂሩት ካሳ (ሚኒስትር)፣ ወይዘሮ አዳናች አቤቤ (ምክትል ከንቲባ) እና ልጅ ዳንኤል ጆቴ (ፕሬዝዳንት) ነው። የደብዳቤው ዋና ጉዳይ በመጪው ሚያዝያ 27 ቀን 2013 ዓ.ም የሚከበረው የንጉሠ ነገሥቱ አፄ ኃይለ ሥላሴና አምስት ዓመት ሙሉ በዱር በገደሉ የአገራቸውን ነፃነት እንደተከበረ ለማቆየት ሲታገሉ የኖሩት አርበኞቻችን በድል አድራጊነት፣ አዲስ አበባ ከተማ የገቡበት 80ኛው የድል ቀን ነው፡፡
ይህ የድል ቀን በቀላሉ የተገኘ የድል ቀን አይደለም። የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም ለሶስት ተከታታይ ቀናት አዲስ አበባ ላይ የተጨፈጨፉትን ሃምሳ ሺህ የሚሆኑ ወገኖቻችንን ጨምሮ በጦር ሜዳ ላይ፣ በምርኮኝነት፣ በእስር ቤት፣ በረሃብ፣  አገራችን የ760 ሺ 300 ንፁሐን ዜጎቿን ሕይወት ገብራ ያገኘችው ትልቅ ድል ነው፡፡ ሰዎች በመኪና ተጎትተው ተገድለዋል። እንደ ከብት ቆዳቸው ተገፏል፤ አንገታቸው እየተቆረጠ ለጣሊያን መኮንኖች መጫወቻ ሆኗል። መስዋእትነቱን አርበኛው ብቻ አልከፈለውም፤ ጣሊያንና ባንዳ፤ “የአርበኛ መጠጊያ ሆነሃል” ብሎ ቤቱን የሚያቃጥልበት፣ አርበኛው በተራው “ለባንዳ መንገድ መርተሃል” ብሎ የሚገርፈው ባላገርም ገበሬም መስዋዕትነት ከፍሏል፡፡ ይህን “ማቃጠሉን ሁላችሁም ታቃጥሉናላችሁ፤ ነፃነትና ባንዲራ መመለሱን ብቻ እግዚአብሔር እውነት ያድርገው” ያለውን የአንድ ባላገር ትዝብት መጥቀስ ይበቃል- እውነቱን ለማሳየት።
የድል በአሉ ትልቅና እጅግ ከፍተኛ መስዋዕትነት የተከፈለበት ቢሆንም፣ ባለፉት 46 ዓመታት ተገቢውን ቦታ አግኝቶ አያውቅም። የድል በዓሉ ተገቢውን ቦታ እንዳያገኝ ያደረገው የአምስት ዓመቱ አርበኞች አገር የጠየቀችውን መስዋዕትነት ሳይከፍሉ ቀርተው ሳይሆን፣ የዘመኑ የፖለቲካ ሰዎች የአርበኞችን ድል ከፍ አድርጎ ማሰብ፣ በወቅቱ የኢትዮጵያ መሪ የነበሩትን የአፄ ኃይለ ሥላሴን ማንነት ማግነን እንዳይሆን ተብሎ ነው። ሊነጣጠሉ የማይችሉትን ለመነጣጠል መሞከራቸው፣ ከአድዋ እኩል፣ ከተቻለ ከአድዋም በላይ መግነን የነበረበትን የድል ቀጋ ሊያጠፉት ባይችሉም እደብዝዘውታል።
ደርግ የንጉሡን መንግሥት በአዝጋሚ ኩዴታ ከሥልጣን በማውረድ ብቻ አልተወሰነም። በንጉሡ ስም የተሰየሙ ተቋማትን ስም በመቀየርም አልቆመም። የንጉሠ ነገሥቱ መሠደድ የጦርነቱን ባህሪ በመለወጥ፣ የጦር ማዕከሉን በመበተን፣ በሺህ የሚቆጠሩ የየአካባቢው አርበኞችን በመፍራት፣ የፊት ለፊት ውጊያውን ወደ አጥቅቶ መሸሽ (ደፈጣ) እንዲለወጥ በማድረግ ያስገኘውን ለውጥ ቁብ በመንፈግ፣ ንጉሡ ከአርበኛው ጋር የነበራቸውን ያልተቋረጠ ግንኙነት፣ የአርበኛውን ለንጉሠ ነገሥቱ የነበረ መታመን ዋጋ በመንፈግ፣ ድሉ እንግሊዞች አዲስ አበባ በገቡበት ቀን  መጋቢት 28 እንዲከበር አድርጎ ቆይቷል።
እንግሊዞች በኦሜድላ በኩል ወደ ኢትዮጵያ የገቡት፣ ንጉሠ ነገሥቱና በየቦታው የተቀላቀላቸውን አርበኛ  ይዘው ደብረ ማርቆስ ላይ እንዲቆይ ያደረጉትና ከኬኒያ የተነሳ በጀኔራል ኪንግሃም የተመራው ጦራቸው ቀድሞ አዲስ አበባ እንዲገባ ያስቻሉት፣ ጣሊያኖች የተዋቸውን ፋብሪካዎችና ልዩ ልዩ ንብረቶች ወደ ኬንያ ለማሸሽ  ጊዜ ለማግኘት ነበር። ጄኔራል ኪንግሃም አዲስ አበባ ከገባ በኋላ አንድ ወር ሙሉ ያደራጀው የእንግሊዝን የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ መሆኑም የታወቀ ነው። የእጅ አዙር የቅኝ አገዛዝን ለመስበር፣የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ዲፕሎማሲዊ ትግል ማድረጉ አይዘነጋም።
ደርግ ወድቆ ሕውሓት ኢሕአዴግ የመንግሥት ሥልጣን በያዘ ጊዜ፣ የድል በዓሉ የሚከበርበት ቀን ወደ ትክክለኛ ቀኑ፣ ሚያዚያ 27  ቢመለስም፣ አከባበሩ ለበዓሉ ተገቢውን ቦታ የሰጠ አልነበረም።
በ1933 ዓ.ም ሚያዝያ 27 ቀን የተገኘውን የድል ቀን ክብርና ቦታ መንፈግ፣ የአምስት ዓመቱ አርበኞቻችንና  የውስጥ  አርበኞች እንዴት ወደ ትግል እንደገቡ አለመገንዘብ ይሆናል። ለምሳሌ የጎንደር ሕዝብ ወደ አርበኝነት ትግሉ የገባው አርባ ስምንት በሚሆኑ ዋና ዋና አካባቢዎች እራሱን አደራጅቶ እንደነበር ገሪማ ተፈሪ “ጎንደሬ በጋሻው” በተባለው መፅሐፋቸው ገልፀዋል።  ከአንድ ወረዳ ለአርበኝነት የወጣው አንድ ሰው ብቻ መሆኑም ይጠቀሳል። ደጃዝማች ገለታ ቆርቾ ወደ አርበኝነቱ የሄዱት፣ አንድ ቤልጀግና አንድ ዲሞትፈር ይዘው መሆኑም ይታወቃል።
ይህ ብቻ አይደለም፡፡ እያንዳንዳቸው በየአካባቢው የነበሩ አርበኞች፣ በስራቸው በአስር ሺህ የሚቆጠር ጦር፣  የሚያስተዳድሩት የታወቀ አካባቢ የነበራቸው ሲሆን  በጣሊያን ላይ እንደ አመጹት ሁሉ በንጉሡ ላይ ሊያምጹ የሚችሉ ነበሩ። ጉልበታቸውን ያጠፉት፣ ክንዳቸውን የሰበሰቡት፣ ንጉሠ ነገሥቱን አክብረው የተቀበሉት፣ ለአገር አንድነትና ነፃነት ከፍ ያለ ቦታ በመስጠታቸው መሆኑ መዘንጋት የለበትም።
“በመካከላችን ጠብ  የሚነሳው በሌባ ነገር ስለሆነ፣ ከእርሳቸው አገር ክፍል መጥቶ ከእኔ ክፍል አገር ከብት እንዳይነዳ፣ ከእኔም አገር ከብት ወደ እሳቸው አገር ቢገባ ላልቀበል አሳልፌ ልሰጥ፤ እኔም ከምገባበት ክፍል ወደ እሳቸው አገር ክፍል ከብት እንዳይነዳ፣ ከእርሳቸውም ክፍል ከብት ተሰርቶ ቢመጣ አሳልፌ ልሰጥ ተስማምቻለሁ” ሲሉ ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ለልጅ ኃይሉ በለው (ራስ) የላኩት የአርቅ መልእክት የሚያሳየው፣ አርበኞች በየአካባቢያቸው የነበራቸውን አይደፈሬነት መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል።
ንጉሠ ነገሥቱን ተከትሎ የራስ አበበ ጦር አዲስ አበባ እንዳይገባ ለማድረግ፣ ጀኔራል ኪንግሃም ያዘጋጀው ሴራ የፈረሰውም በዚሁ ሚያዝያ 27  እለት በራስ አበበ አረጋይ እምቢ ባይነት መሆኑም ሊሰመርበት ይገባል። ጣሊያንን አስወጥተን ሌላ ቅኝ ገዢ አንቀበልም የማለት እምቢተኝነትም የታየበት ቀን ነው።
የሚያዝያ 27 የድል ቀንን የወለደው የአምስት ዓመቱ የአርበኞቻችን ትግል፣ ለአለም የደፈጣ ውጊያ ስልትን ያስተማረ መሆኑም ይነገርለታል፡፡
ስለዚህም ከላይ በስም የጠቀስኳቸው መስሪያ ቤቶችና የጠከበሩ መሪዎቻቸው፣ በመጪው ሚያዝያ 27 ቀን 2013 ዓ.ም የሚከበረው 80ኛው የድል በዓል፣ ተገቢውን ቦታ አግኝቶና ክብሩ ተጠብቆ እንዲከበር ያደርጉ ዘንድ ጥያቄና ማሳሰቢያዬን በትህትና አቀርባለሁ።
ታላቅ ክብር ለአባት አርበኞች!!

Read 2719 times