Saturday, 20 March 2021 11:45

በአገራችን ከአራት ሰው አንዱ የኮረና ቫይረስ አለበት

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(4 votes)

      • የመንግስትና የግል ጤና ተቋማት በህሙማን ተጨናንቀዋል
       • የኦክስጅንና ቬንትሌተር እጥረት በከፍተኛ መጠን አጋጥሟል ተባለ
       • “አዳዲስ አይነት የኮቪድ-19 ቫይረሶች ገብተው ይሆናል”
           
          ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን በኮቪድ-19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከዕለት ዕለት አስደንጋጭ በሚባል ደረጃ እየጨመረ መምጣቱን የጤና ሚኒስቴር ያስታወቀ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ህሙማንን ተቀብሎ ማስተናገድ በማይችሉበት ደረጃ ላይ መደረሱን ተጠቁሟል። በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ከ4 ሰዎች አንዱ ቫይረሱ እንደሚገኝበት የህብረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መረጃ አመልክቷል። የባለሙያ ድጋፍና እንክብካቤ የሚሹ ህሙማን ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ በመጨመሩ የህክምና ማዕከላት ማስተናገድ ከሚችሉት አቅም በላይ እየሆነ መምጣቱ ተነግሯል።
ሁኔታው ከቁጥጥር ውጪ ወደ መሆኑ እየተቃረበ በመምጣቱ በሽታው ወደ አገራችን በገባበት ወቅት ይደረጉ የነበሩ ዝግጅቶች እንደገና መጀመር እንደሚያስፈልግና ይህንኑም ለማድረግም እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሆነ ምንጮች ጠቁመዋል። እንደ ምንጮቹም ገለጻ፣ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ አዲስ አይነት የኮቪድ-19 ቫይረስ ሳይገባ አይቀርም የሚል ስጋት መኖሩንና የበሽታው በፍጥነት መዛመትም ይህንኑ ችግር የሚያሳይ እንደሆነ ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙትና ለኮቪድ-19 ህክምና  የተዘጋጁ የግልም ሆነ የመንግስት የጤና ተቋማት በህሙማን በመሞላታቸው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ህሙማን በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ ሆነው ወረፋ ለመጠባበቅ እንደተገደዱ ተነግሯል።
በኮቪድ-19 በሽታ መከላከል ኮሚቴ ውስጥ በመስራት ላይ የሚገኙት ዶ/ር ሰለሞን ወርቁ  እንደሚናገሩት በአሁኑ ወቅት ያለው የበሽታ ስርጭት መጠን እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር  በየዕለቱ በእጥፍ እየጨመረ መሆኑን ያመለከቱት  ዶ/ር ሰለሞን ይህም የህብረተሰቡ ቅጥ ያጣ መዘናጋትና  ወደ ቀድሞው የህይወት ሂደት መመለሱ ያስከተለው ችግር ነው ብለዋል። “ሰርግ፣ ለቅሶ፣ ስብሰባዎችና  ሰላማዊ ሰልፎች ምንም ያልተፈጠረና የሌለ በሚመስል ሁኔታ እየተካሄዱ መሆናቸው ለበሽታው ስርጭት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው” ያሉት ባለሙያው ከኮቪድ ህሙማን ቁጥር በከፍተኛ መጠን መጨመር ጋር ተያይዞ የኦክስጅንና ቬንትሌተር እጥረት ማጋጠሙን ተናግረዋል። የበሽታው የስርጭት መጠን መጨመር የሚያመለክታቸው ነገሮች መኖራቸውን የጠቆሙት ዶ/ር ሰለሞን ፤ምንም እንኳን ተጨማሪ ጥናት የሚያስፈልግ ቢሆንም  አዳዲስ አይነት የበሽታው ዝርያዎች ወደ አገራችን ገብተው ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን ገልጸዋል።
በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በጨመረ መጠን ፅኑ ታማሚዎችና ጥብቅ የህክምና ክትትል የሚያስፈልጋቸው ህሙማን ቁጥር እየጨመረ የሚሄድ መሆኑን የሚያመለክቱት ዶ/ር ሰለሞን፤ ይህንን ደግሞ አገሪቱ ባላት አቅም ፈጽሞ የማትችለው ጉዳይ ነው ብለዋል።  በአሁኑ ወቅት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች በቤታቸው ሆነው ራሳቸውን ለመንከባከብ እንዳይችሉ በአገሪቱ ከፍተኛ የኦክስጅን እጥረት እያጋጠመ ነው ብለዋል። ከመተንፈሻ መሳሪያ እጥረት በተጨማሪም ወደ ማዕከሉ ለመግባትና ህክምና ለማግኘት የሚያስችል አቅም መጥፋቱንም ተናግረዋል።
በሽታው ተጠንቶ ያላለቀ፣ ዓይነቱ የሚቀያየርና ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ የሚገኝ በሽታ መሆኑንህብረተሰቡ ሊገነዘብ ይገባል ያሉት ዶ/ር ሰለሞን አብዛኛዎቻችን ስለበሽታው ያለን ግንዛቤ እጅግ የተሳሳተ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የኮቪድ-19 በሽታ ማን ላይ እንደሚጸና የማይታወቅ ከመሆኑም ሌላ ኩላሊትን ከጥቅም ውጭ ማድረግ፣ በልብ ላይ ከባድ ችግር ማስከተልና የመተንፈሻ አካላት ላይ ጉዳት ማድረስ በአሁኑ ወቅት በኮሮና ታማሚዎች ላይ እየታየ ያለ የጤና ችግር እንደሆነ አመልክተዋል። በሽታው ምልክቶቹ በየጊዜው የሚቀያየሩ በቀናት ውስጥ ለከፍተኛ ህመም ስቃይን ሞት ሊዳርግ እንደሚችልም ታውቆ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
ሰዎች በጋራ ከሚሰበስቧቸው ስፍራዎች ራስን ማራቅ፣ ለበሽታው መከላከል የሚደረጉ የጥንቃቄ እርምጃዎችን መተግበር በበሽታው ላለመያዝ ብቸኛው ዋስትና በመሆኑ ሰው እነዚህን ተግባራት መፈፀም እንዳለበት መክረዋል።
የበሽታው የስርጭት መጠን በዚሁ ከዘለቀና የእኛም መዘናጋት ባለበት የሚቀጥል ከሆነ ለከፋው ጊዜ ራሳችንን ማዘጋጀት ይኖርብናል ያሉት የህክምና ባለሙያው ህክምናውን የማይሳጡ የግል ጤና ተቋማት ህክምናውን እንዲሰጡ ማበረታታትና ተጨማሪ የህሙማን መቀበያ የጤና ማዕከላትን በቶሎ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። የፅኑ ህሙማን  ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት እያሻቀበ መምጣቱን የጠቆሙት ሃኪሙ፤ ቁጥሩ ከ600 በላይ መድረሱን አመልክተዋል። ከእንግዲህ በኋላ በበሽታው የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ይቀንሳል የሚል እምነት እንደሌላቸውም ነው የተናገሩት።
በአሁኑ ወቅት በየግላቸው የተደራጁና በሚሊኒየምና የካ ኮተቤ የኮቪድ ህክምና መስጫ ማዕከላት ውስጥ የሚሰሩ ዶክተሮች ለኮቪድ-19 ህሙማን ቤት ለቤት ህክምና እየሰጡ የሚገኙ ሲሆን ይህም በጤና ተቋማት ውስጥ የሚፈጠረውን ጭንቀትና ጫና በእጅጉ እንደሚያቃልል ተመልክቷል። እስከ ትናንት ድረስ በበሽታው ሳቢያ ህይወታቸውን ካጡ 2,602 ሰዎች መካከል 1,852 ወይም 73 በመቶ የሚሆኑት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙ ናቸው ተብሏል።  

Read 11738 times