Saturday, 20 March 2021 11:48

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት በትግራይ ጉዳይ ላይ የሚነጋገር ልዩ መልዕክተኛቸውን ወደ ኢትዮጵያ ልከዋል

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(1 Vote)

  • ሴናተር ክሩስ ኩንስ ከጠ/ሚ ዶ/ር አቢይ አህመድ ጋር ይወያያሉ።
     • አሜሪካ ለትግራይ ክልል የ52 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አድርጋለች።
                
            አሜሪካ በትግራይ ክልል ተካሄደ የተባለውን “የዘር ማጽዳት” ጉዳይ አስመልክቶ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ጋር የሚነጋገር ልዩ መልዕክተኛዋን ወደ ኢትዮጵያ የላከች ሲሆን ለትግራይ ክልል የሰብአዊ እርዳታ የሚውል የ52 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አድርጋለች። መልዕክተኛው ሴናተር ክሩስ ኩንስ በኢትዮጵያ በሚያደርጉት ቆይታ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ ከአፍሪካ ህብረት የሥራ ኃላፊዎች ጋርም ይነጋገራሉ ተብሏል።
የፕሬዚዳንቱ ልዩ መልዕክተኛና የአሜሪካ ምክር ቤት አባል የሆኑት ሚስተር ክሩስ ኩንስ፣ ከጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ጋር በሚያደርጉት ውይይት በትግራይ ክልል ስለተከሰተው ቀውስ፣ ተፈጽሟል ስለተባለው የሰብአዊ መብት ጥሰትና  በሱዳንና ኢትዮጵያ መካከል ስላለው የድንበር ውዝግብ ጉዳይ ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን፣ ለአገሪቱ ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ፣ ኢትዮጵያን በሚመለከት በሰጡት ማብራሪያ ፤ “በትግራይ ክልል የዘር ማጽዳት ድርጊት ተፈፅሟል” ብለው መናገራቸውን ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ጉዳዩን በጥብቅ በመቃወም ክሱ ተጨባጭነት የሌለውና ሃሰተኛ መሆኑን ገልጿል፡፡ ይሄን ሁኔታ ተከትሎም ፕሬዚዳንት ጆይ ባይደን፣ ስለጉዳዩ በጥልቀት ለመረዳት ልዩ መልዕክተኛቸውን ለመላክ መገደዳቸውን ገልፀዋል፡፡ ሴናተር ክሩስ ኩንስ በኢትዮጵያ በሚያደርጉት የቀናት ቆይታ በትግራይ ክልል ተፈፀመ የተባለውን የዘር ማጽዳት፣ የፆታ ጥቃትና የንፁሃን ሞት በተመለከተ ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር እንደሚወያዩ ተገልጿል።
በአጠቃላይ በትግራይም ይሁን በኢትዮጵያ ያለው ግጭትና ውጥረት ተወግዶ ሀገሪቱ ወደ ሰላማዊና የተረጋጋ ሁኔታ እንድትመለስ ጫና ለማድረግ ጥረት ያደርጋሉ ተብሏል።
የአሜሪካ የውጭ ግንኙነት ሴኔት አባል የሆኑት ሴናተር ክሩስ ስለጉዳዩ ከጉዳዩ ባለቤቶች ጋር በመነጋገርና ትክክለኛ መረጃዎችን በማሰባሰብ ለፕሬዝዳንት ጆይ ባይደን ሪፖርት እንደሚያደርጉም ተናግረዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘም አሜሪካ በትግራይ ክልል ለሚከናወነው ሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት የሚውል የ52 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ማድረጓን በውጭ ጉዳይ መ/ቤቷ በኩል ይፋ አድርጋለች። ይኸው ድጋፍ በክልሉ ከተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ ጋር በተያያዘ ለተለያዩ ሰብአዊ ቀውሶች ለተጋለጡ የክልሉ ነዋሪዎች ድጋፍ የሚውል ነው ተብሏል፡፡



Read 11682 times