Saturday, 20 March 2021 11:56

ውሾቹ ይጮሃሉ፤ ግመሎቹ ግን መንገድ ቀጥለዋል

Written by 
Rate this item
(8 votes)

       ከእለታት አንድ ቀን በርካታ ጅቦች  የተራቡና  የሚበላ ነገር ለማግኘት ዞር ዞር ሲሉ፣  አንድ እጅግ ግዙፍ ዝሆን ገደል ወድቆ ገብቶ አገኙ።
እርቧቸዋልና አንደኛው፡- “እጅግ እድለኞች ነን። ልክ በሰዓቱ የተገኘ መና ነው። ከሰማይ የተላከልን ጸጋ ነው።”
ሁለተኛውን፡- “ዘለን እንግባና ዝሆኑን እንቀራመተው” አለ።
ሶስተኛው፡- መግባቱንስ  ገባን መብላቱንስ በላን፤ ከጠገብንና ሆዳችን ከሞላ በኋላ እንዴት አድርገን ነው ከዚህ አዘቅት ወደ አቀበቱ የምንወጣው። ተው አያዋጣንም” አለ።
አራተኛው፡- “ወደ ገደሉ እንግባና በኋላ እናስብበታለን” አለ።
ለተወሰነ ሰአት ከተወያዩበት በኋላ “ገብተን እናስብበታለን” በሚለው ሃሳብ ላይ ሁሉም ተስማሙ። ስለዚህ ተንደርድረው ወደ ገደሉ ገቡ።  ዝሆኑን እየተሻሙ ተቀራመቱት። ጥጋብ መጣ። ሆኖም ለመውጣት እንደተፈራው መላው መላው ጠፋው። ደሞ የመውጫ ዘዴ መመካከር ቀጠሉ። በመጨረሻም አንዱ አንዱን እሽኮኮ በማለት እየተደጋገፉ ለመውጣት ተስማሙ። እየተገፋፉ አብዛኞቹ ጫፍ ደረሱ።
የመጨረሻውን ጅብ ግን ማን ያውጣው፤ ሌላ ጅብ አልነበረም። አንደፈረደበት እዚያው በረሃብ ሞተ!
*   *   *
ሆዱን ያየ ሆዱን ተወጋ የሚለው ተረት የዋዛ አይደለም። የሞተ ዝሆን ላይ መረባረብ ሃያልነትን አያሳይም። ቢያንስ ቢያንስ የወደቀ ዛፍ፤ ምሳር ይበዛበታል የሚለውን ከማመላከት  በስተቀር።
“አስረው ደበደቡት ያን የዝሆን ጥጃ
ዛሬም ደስ አላቸው የነገውን እንጃ”
(እንደ አጋዥ ስንኙን እንጨምር)
“ገዴ ዞራ ዞራ በእንቁላሏ ላይ
ጊዜ የሚጠብቅ ሰው ጅብ ሊባል ነው ወይ”
…የሚለውንም አለመዘንጋት ነው።
በረዥሙ የሀገራችን ጉዞ ውስጥ ከሎሬት ጸጋዬ ቴዎድሮስ ጋር፡-
“ያለፈ ተረታችንን ሳስታምመው ትዝ ሲለኝ
ከሞከርነው ነገር ይልቅ ያልሞከርነው ነው የሚቆጨኝ”… ማለትም ያባት ነው።
መንገድን አጥርቶ ማየት፣ ሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ ከመሆን ይገላግለናል። እንዲህ ያለውን ነገር ለመተግበር ታታሪነትንና አስተውሎነትን ይጠይቃል። ይህን አስተውሎት እውን ለማድረግ ደግሞ መማር፣ ማንበብ፣ መወያየት፣ የተወያየነውን ማውጠንጠን፣ ያውጠነጠነውንም አለመርሳት መሰረታዊ ነገር ነው።  ይህ አይነት የማሰብ ባህል ካልዳበረ ትውልድ አሁን እያዘቀዘቀና እየወረደ ባለበት ቁልቁለት መገስገሱን ይቀጥላል። ትውልዱ በዚሁ ከቀጠለም የሀገርን ውድቀት ከማፋጠን ሌላ የሚፈይደው አንዳች ተስፋ እድል አይኖርም። ጉዞው የእውር የድንብር ነውና። የለዋጭ ተለዋጭ፣ የተማሪ አስተማሪ እምንፈጥረውና የምናፈራው  ነባራዊውንና ህሊናዊውን ሁኔታ እያሟላን ስንታትር ነው።
ይሄ ማሟላት ደግሞ ህብረተ ሱታፌን ይጠይቃል። እውነታን እውን ማድረግ ይጠይቃል።
እንቅፋቶችን ልብ ማለት ለአንድ መንግስት ግዴታም ጥበባዊ ክህሎትም ነው።
እነዚህን ክህሌቱ ተክህኖዎች ካቀናጀን፣ አንድ እርምጃ በእድገት አውራ መንገድ ላይ መጓዝ ነው። ያም ሆኖ  እንቅፋት ተፈርቶ እርምጃን ማቋረጥ፣ የዋህነት ነው! ውሾቹ ቢጮሁም ግመሎቹሆነን መንገድ መቀጠል አለብን።



Read 13465 times