Print this page
Saturday, 20 March 2021 12:11

ሚያዚያ 27 - እንደ አድዋ!

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

   የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን 125ኛውን የአድዋ ድል በዓል በልዩ ልዩ ፕሮግራሞች አክብሯል። ወደ ውጫሌ የተጓዘው የኢቲቪ ዘጋቢ፣ አንዳንድ የከተማውን ነዋሪዎች ስለ ውጫሌ ውል ሲጠይቃቸው ሰምተናል:: ውሉ በአድዋ ጦርነት ምክንያት መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ የብዙዎች መልስ ግን አናውቀውም የሚል ነበር፡፡ በዘመነ ደርግ ከዚያም በሕወሓት ኢሕአዴግ የገዢነት ዘመን፤ ዓመት እየተጠበቀ ከበሮ የሚመታለትን፣ አድናቂ የሚጎርፍለትን የአድዋ ጦርነት መነሻ የሚያውቁ ሰዎች ከጠፉ፤ ተቆርቋሪና አስታዋሽ የሌለው፣ በየአጋጣሚው ከሚወገዙትና ከሚረገሙት ከቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ጋር የተያያዘው የሚያዚያ 27 የድል ቀንማ በምን ተዓምር ሕዝብ ዘንድ ደርሶ ይታወሳል?
አድዋ ላይ የተሸነፉት ጣሊያኖች፣ መሸነፋቸውን ተቀብለው፣ በኤርትራና በጣሊያን ሶማሌ- ላንድ ተወስነው ለመቀመጥ አልፈለጉም፡፡ የኤርትራ አገረ ገዥ የነበረው ካራ ዞሊ፣ በአፋርና በራያ መካከል በአፄ ዮሐንስ ዘመን የተጀመረውን የራዛ ዘመቻና የአዳል ዘመቻን በመጠቀም የሌለ ግጭት በመቀስቀስ፣ የተፈጠረውን ደግሞ አጋኖ በማስውራት፣ በአካባቢው አገረ ገዢዎች መካከል አለመተማመን በማስረፅ፣ ልዑል ራስ ተፈሪ መኮንን (አልጋ ወራሽ)  ወደ አካባቢው ጦር እንዲልኩ በማድረግ፣ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ለመውረር ብትነሳ ምን ያህል የጦር ሠራዊት እንደሚያስፈልጋት አጠና።
ጣሊያኖች ሐኪም፣ መሐንዲስ፣ የመልክአ ምድር አጥኚ፣ የሐይማኖት አስተማሪ በማለት በአገር ውስጥ  በዘሯችው ሰዎቻቸው አማካይነት አገሪቱን ከዳር እስከ ዳር በማዳረስ የጦር ሜዳ የውጊያ እቅዳቸውን ነደፉ፡፡ በጅማ፣በሶዶና፣በሀገረ ሰላም እንዲሁም በዶሎና በሌሎችም አካባቢዎች ባቋቋማቸው የፕሮፓጋንዳ  ጣቢያዎቻቸው ከፍተኛ ገንዘብ በማፍሰስ፣ ባላባቱን ከንጉሰ ነገስቱ፣ ሕዝቡን ከመንግስት ጋር ለማጋጨት ብዙ ጣሩ፡፡ በሀገራቸው ደግሞ እንደ አልቤን ምንሽር ያሉትን የጦር መሳሪያዎች ጥራታቸው እንዲሻሻል የማድረግ ሥራ ከመስራታቸው በላይ ታንክ፣ መድፍ፣ የጦር አይሮፕላን፣ ቦምብ፣ የመርዝ ጋዝ በገፍ ማምረቱን ተያያዙት። አንድ ቢሊዮን ሁለት መቶ ሰማኒያ አንድ ሚሊዮን ስምንት መቶ ሺህ የጠመንጃና ስድስት መቶ ሺህ የመድፍ ጥይት እንደነበራቸው ለአይነት መጥቀሱ የዝግጅታቸውነን መጠን ለማመልከት ያገለግላል። ዝግጅታቸውን በሚገባ ማጠናቀቃቸውን በተረዱ ጊዜ፣ ኢትዮጵያን ወደ ጦርነት ለማስገባት ጎንደር ላይ ሞከሩ። ሕዳር 10 ቀን 1927 ዓ.ም  ወልወል ላይ ተሳካላቸው። አንድ መቶ ኪሎ ሜትር ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ገብተው ጦርነት ከፈቱ። ዋርዴርን ጋራጎቤን፣ ጎቤን፣ ቆረሄን ቀብሪ ይሐርን፣ ፋፋን ወንዝ አከታትለው ያዙ።  ኢትዮጵያ የዓለም መንግሥታትን ማኅበር መተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ 15ን ጠቅሳ፣ ለማህበሩ አቤት አለች። የዲፕሎማሲ ትግሉ ቀጠለ፡፡
መስከረም 21 ቀን 1928 ጣሊያኖች ጦራቸውን በሰሜን በትግራይ፣ በደቡብ-በቦረናና በምስራቅ- በሀረር በሶስት  ግንባር አሰማርተው፣  በይፋ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት አወጁ። የኢትዮጵያ መንግሥት መስከረም 22 ቀን 1928 ዓ.ም የክተት ጥሪ አዋጀ። ቀደም ብሎ የተጀመረው የመከላከል ጦርነቱ ቀጠለ። በትግራይ እነ ደጃዝማች ዓባይ ካሣ፣ እነ ደጃዝማች ገብረሕይወት መሸሻ የጠላትን እንቅስቃሴ ለመግታት ጉድጓድ በመማስ አደጋ በመጣል የሚችሉትን ሁሉ እያደረጉ ቀጠሉ።
ራስ ሙሉጌታ ይገዙ በአጠቃላይ የሰሜን ጦር አዛዥ ሆኑ። ራስ እምሩ የጎጃምና የጎንደርን፣ ራስ ካሣ የወሎን፣ ራስ ስዩም የትግሬን ጦር እንዲመሩ ሲደረግ፣ የደቡብ ምስራቅን ግንባር ራስ ደስታ፣ የሐረርን ግንባር ደጃዝማች ነሲቡ ዘአማኑኤል እንዲመሩት ተደረገ።
ሃያ አምስት ሺህ ጦር  በሽሬ ግንባር ይዘው የተሰለፉት ራስ እምሩ፤ በሹም ዋሻ ጦርነት ጠላትን ድባቅ መምታት ቢችሉም፣ በደረሰባቸው የቦምብና የመርዝ ጋዝ ድብደባ፣ ሰራዊታቸው በማለቁ፣ 300 እራሳቸውን ሆነው ወደ ኋላ ለመመለስ ተገደዱ።
በተምቤን የጦር ግንባር በራስ ሙሉጌታ የሚመራው የኢትዮጵያ ጦር፤ በአምባላጌና በበለሳ ዙሪያ አራት ቀን ሙሉ ተዋግቶ ለማሸነፍ ችሏል። በዚህ ጦርነት የራስ ካሳና የራስ ስዩም ጦርም ከፍ ያለ አስተዋፅኦ ማድረጉ ይጠቀሳል። አምባራደም አካባቢ በተደረገ ሌላ ውጊያ ግን የራስ ሙሉጌታ ጦር ክፉኛ ተጎዳ። ወደ ኋላ ማፈግፈግ ግድ ሆነበት፤ ወደ ኮረም እየተጓዙ እያለ መንገድ ላይ ራስ ሙሉጌታ ተገደሉ።
በሐረር ግንባር የተመደበው በደጃዝማች ነሲቡ ዘ አማኑኤል የተመራው ጦር፣ የሰራው ሥራ እምብዛም ነው። በራስ  ደስታ ዳምጠው መሪነት በቦረና ግንባር የተሰለፈው የኢትዮጵያ ጦር ግን ራስ ደስታ ዳምጠው እስከተገደሉበት ጊዜ ድረስ ከፍ ያለ አገርን የመከላከል ሥራ ሠርቷል።
ወደ ሰሜን እንመለስ። በሰሜን የመጨረሻው የመከላከል ጦርነት ማይጨው ላይ የተካሄደው መጋቢት 22 ቀን 1928 ዓ.ም ነው። በዚህ ጦርነት “ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ” በተባለው መፅሐፋቸው፣ ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ስላሴ እንደገለጹት፤ በሳቸው ዋና ጦር አዛዥነት በራስ ካሣ፣ በራስ ከበደ መንገሻ፣ በራስ ስዩምና በራስ ጌታቸው የሚመራ ሃምሳ አንድ ሺህ ጦር ተሰልፎ ነበር። ጦሩ በመጀመሪያው ዙር አምስት ያህል ምሽጎች  አስለቅቆ ወደፊት እያጠቃ ነበር። ለጠላት ያደሩ የራያ ሰዎች ከጀርባ ባደረሱበት ጥቃት፣ ከላይ በቦምብ እየተደበደበ፣ በመርዝ ጋዝ እየተለበለበ፣ ከታች በመትረየስ እየታጨደ ያገኘውን ድል ተነጥቆ ተሸናፊ ሆነ።
ከዚህ በኋላ የቀጠለው አምስት ዓመት የወሰደው የአርበኝነት ትግል ነው። አርበኛው አምስት ዓመት ሙሉ  የተዋጋው ከጣሊያኖች ጋር  ብቻ አይደለም። ጠላት ፊት ለፊት አሰልፎ የጥይት ማረፊያ ካደረጋቸው ዘጠኝ መቶ ሃያ ሺህ ባንዳ ኢትዮጵያውያን ጋርም ነው።
ባንዳ ሆነው ለጠላት እያገለገሉ ያሉ ኢትዮጵያዊያንን መግደሉ እየመረራቸው በሄደ ጊዜ፣ አርበኞች ለምሳሌ ደጃዝማች በላይ ዘለቀ “ጥዝጥዝ” የሚባል የውጊያ ስልት አዘጋጅተው ጦራቸው ቀዳሚውን የጣሊያን ጦር ማጥቃቱን ትቶ ከጀርባ ያለውን ደጀኑን የነጩን ጦር እንዲመታ ማድረጋቸው፣ ራስ አሞራው ውብነህ ደግሞ “ጥቁር የገደለ እንደ ገደለ አይቆጠርም” ሲሉ በማወጅ፣ ነጭ ነጩ እየተመረጠ እየተመረጠ እንዲመታ ማድረጋቸው መወሳት አለበት- የትግሉ አንድ መልክ ነውና።
የሚያዚያ 27 የድል ቀን የአገርን ነፃነት ላለማስደፈር ከተደረገው የመከላከል ትግል ጀምሮ የአምስቱን ዓመት መራራ መስዋዕትነት ጨምሮ የተገኘ ድል ነው። አባቶቻችን በዚህ ሁሉገብ የጦር ግንባር ያፈሰሱት ደም፣ የከሰከሱት አጥንት የአንድ ትልቅ ተራራ ያህል በህሊናችን ገዝፎ ሊታይ ይገባዋል። ልክ እንደ ጉዞ አድዋ ሁሉ ሚያዚያ 27 የድል ቀንም የሚቆረቆርለትና በየዓመቱ በአዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 27 አደባባይ ላይ እየተገኘ የሚያከብረው፣ የሚጠበቀውና የሚያስጠብቀው ወጣት ትውልድ ያስፈልገዋል።
ተጋድሎው የተደረገው በመላዋ ኢትዮጵያ መሆኑ አይዘነጋም። ድል አድራጊውም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። አንድ የተወሰነ የድል ቦታ የለውም። ንጉሡን አጅቦ በድል አድራጊነት ወደ አዲስ አበባ የገባው የጎጃምና የራስ አበበ ጦር፣ የአርበኛ ልጆችና የልጅ ልጆች፣ በአሉን በላቀ ክብርና ድምቀት ለማክበር ጀማሪዎች መሆን ይችላሉ ብዬ አምናለሁ። የዘንድሮውን 80ኛውን የድል በአል፣ የተለየ ድምቀት ሰጥተውት ሲያከብሩት ባይ ለእኔ መታደል ነው።
ማነህ ማነሽ የአርበኛ ልጅ፣ ወዴት ነህ ወዴት ነሽ? እያልኩ ነው።

Read 2079 times