Saturday, 20 March 2021 12:28

ጆቫኒ ሪኮና ጊታሩ

Written by  አበራ ሣህሌ
Rate this item
(0 votes)

  ባለፈው ሰሞን ፋና ቲቪ የአንጋፋውን ጊታር ተጫዋች ጆቫኒ ሪኮን የሙዚቃ ሕይወት የቃኘ ዝግጅት አቅርቦ ነበር። ከድምፃውያን ጀርባ ሆነው ሙዚቃውን የሚመሩት አቀናባሪዎች፤ ግጥምና ዜማ ደራሲዎች፤ አዋሃጆች፤ የድምፅ መሀንዲሶችና የመሳሰሉት እንዴት እየተቀናጁ ትልቁን ሥዕል እንደሚያወጡ ያሳያል።
ወደ ጆቫኒ ስንመጣ በተለይ እሱ ይታወቅበታል የሚባለው የቤዝ ጊታር አጨዋወት፣ ሮሃ ባንድ ሲያቀርባቸው በነበሩ ሥራዎች ላይ ሁነኛ ሥፍራ እንደነበራቸው ስንሰማ ቆይተናል። ዝግጅቱ የሙዚቃ ሃያሲንም በማካተቱ ዝም ብለን የምንሰማውን ሙዚቃ መልኩን እንድናውቀው አድርጓል። ቤዝ የተባለው ጊታር የሚያወጣውን ድምፅ በበቂ ማሳየቱን እርግጠኛ ባልሆንም፣ አጠቃላይ ዝግጅቱ ግን አስተማሪና አዝናኝ ነበር።
ሌላው ትኩረት የሚስበው በቴሌቪዥን ቋንቋ “መውጫው” ላይ እንደ ቀልድ የተነገረው፣ 18 ኪሎ የሚመዝነው ጊታር ጉዳይ ነው። ሙዚቀኛው በአይቤክስና በሮሃ ባንድ ለረጅም አመታት የተጫወተበትንና ከ250 የማያንሱ የካሴት ሥራዎች ያስቀረፀበት መሣሪያ እንደ ቅርስ ተቀምጦ ታይቷል። ይሸጥ ቢባል ከ15 እስከ 20 ሺህ ዶላር እንደሚያወጣ ለዘብ ብሎ ነው የተናገረው።
ይህም ወደ ዊሊ ኔልሰን ጊታር ይወስደናል። የእሱ እንኳ እንደዛ ግርማ ሞገስ ሊኖረው ቀርቶ ሊከስር ቋፍ ላይ የደረሰ ሱቅ በደረቴ ሰንዱቅ ነው የሚመስለው። መልክ ያሳስታል ይባላል። ያ ጊታር ግን ከብዙ ሙዚቀኞች የተሻለ ታሪክ እንዳለው ይነገራል። ዊሊ ኔልሰን ህይወቱን ሙሉ ዘፈን ሲፅፍ፥ ሲጫወት፤ ከግብር ሰብሳቢዎች ጋር ሲናቆር፤ ሀሺሹን ሲቦልቅ አንዳንዴም ገበሬ ሲረዳ ይኸው 87 ዓመቱ!
አሁን ኮቪድ ሰበሰበው እንጂ ትሪገር የሚለው  ጊታሩን ይዞ እየዞረ ዝግጅት ሲያቀርብ ነው የኖረው። መቼም Crazy, On the Road Again,You’re Always on My Mind ማለቂያ ከሌላቸው ማለፊያ ሥራዎቹ መካከል ናቸው።
የማይክሮሶፍቱ ቢል ጌትስ በሰርጉ ዋዜማ ለባለቤቱ ሜሊንዳ ያበረከተው ስጦታ ዊሊ ኔልሰን እንዲዘፍንላቸው ማድረግ ነበር። ዊሊን ምን ገዶት። ሽንቁሩ የሰፋውን ትሪገርን ይዞ ከች! እንደፈለገ የሚገራውና ድምፅ የሚያወጣበት ይህ መሣሪያ፣ የቅርስ ሰብሳቢዎች ሲሳይ እንደሚሆን ግልፅ ነው።
ጆቫኒ ጊታሩን ስም አውጥቶለት እንደሁ ባናውቅም፣ “ወፍ እንዳገሩ ይጮሃል” እንደሚባለው፣ ሮሃ የገነነበት የ70ዎቹና 80ዎቹ የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ፣ ከካሴቶች ፎቶ በተጨማሪ ሁነኛ ማስታወሻ አግኝቷል። 

Read 1150 times